የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አመራር አቶ ዳዊት አስራደ ትናንት ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ በ5,000 ብር ዋስ እንዲፈታ ዋስትና የተፈቀደለት ቢሆንም ገንዘቡን ካስያዘ በኋላ ዋስትናው እንደተነሳ ተነግሮት በእስር ላይ እንዲቆይ ተደርጓል፡፡ በትናንትናው ችሎት ፖሊስ ተከሳሾቹ ምስክሮችን ያባብሉብኛል በሚል ምስክሮችና መረጃዎችን አሰባስቦ እስኪያቀርብ ጊዜ ድረስ 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቆ የነበር ቢሆንም አቶ ዳዊት አስራደ፣ ሌላው የቀድሞው አንድነት ስራ አስፈፃሚ አባል እና የማኀበራዊ ጉዳይ ኃላፊ የነበረው አቶ አለነ ማፀንቱና ወይዘሪት ሜሮን አለማየሁ የ5,000 ብር ደሞዝ ያለው የሰው ዋስ ወይንም ገንዘብ አስይዘው ከእስር እንዲወጡ ፈቅዶ ነበር፡፡
ይሁንና የአቶ ዳዊት አስራደ ቤተሰቦች መፍቻ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ (ሶስተኛ) ሲሄዱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ (ሶስተኛ) ፖሊስ አቶ ዳዊትን ለቄራ ፖሊስ ጣቢያ ማስረከቡን እንደገለጸላቸው ጠበቃው አቶ ገበየሁ ይርዳው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የቄራ ፖሊስ ጣቢያም ከአሁን ቀደም አቶ ዳዊት አስራደ በተመሳሳይ ክስ ተፈቅዶለት የነበረውን ዋስትና ማንሳቱን በመግለጽ እንዳሰረው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ በተፈቀደለት ዋስትና መሰረት 5000 ብር ያስያዘውን አቶ አለነ ማህፀንቱን ፖሊስ መጀመሪያ ወደ ማታ እፈታዋለሁ፣ እንዲሁም ከቆይታ በኋላ ይግባኝ እጠይቃለሁ ብሎ እስር ላይ ቢያቆየውም አሁንም ድረስ ይግባኝ ሳይጠይቅ በእስር ላይ እንደሚገኝ ጠበቃው ገልፀዋል፡፡
መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ሰበብ የታሰረው አቶ ዳዊት አስራዳ በተመሳሳይ ክስ ለሶስተኛ ጊዜ የዋስትና ገንዘብ እያስያዘ እንደገና በእስር ላይ የቆየ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ 25 ሺህ፣ በቀጣይነትም 6 ሺህ፣ እንዲሁም ሰኔ 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ሌላ 5 ሺህ ብር በአጠቃላይ 36 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ እንደገና ታስሯል፡፡ አቶ ዳዊት አስራደና ወይዘሪት ሜሮን አለማየሁ ሚያዝያ 14 መንግስት ላይ በተነሳው ተቃውሞ ሰበብ በአንድ ጉዳይ ሁለት ክስ ተመስርቶባቸው በሁለት ፍርድ ቤቶች ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡ በቄራና ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያም በፈረቃ ሲታሰሩ መቆየታቸውን የነገረ ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡