በደብረማርቆስ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ እና በትግራይ ሑመራ የዓረና/መድረክ አባል ተገደሉ

በምስራቅ ጎጃም የሰማያዊ ፓርቲ ፀሐፊ እና ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ በደብረማርቆስ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ የነበረው ወጣት ሳሙኤል አወቀ ዓለም ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ማታ ላይ በሁለት ግለሰቦች በተፈፀመበት ከፍተኛ ድብደባ ሆስፒታል ቢገባም ህይወቱ ሊትርፍ አልቻለም፡፡ ወጣቱ ቀደም ሲል ሚያዝያ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በመንግሥት ደህንነቶችና ፖሊስ አባላት ድብደባ እንደደረሰበት ከነጉዳቱ ለህዝብ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

ወጣት ሳሙኤል አወቀ ሚያዝያ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በተደበደበበት ወቅት

ወጣት ሳሙኤል አወቀ ሚያዝያ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በተደበደበበት ወቅት

ከሚያዝያው ድብበደባ በኋላም በተደጋጋሚ የደብረማርቆስ ደህንነት አባላት፣ የከተማው የፖሊስ አዛዥን ጨምሮ የብአዴን/ኢህአዴግ ካድሬዎች ዛቻና ማስፈራሪያ ይፈፅሙበት እንደነበርና ከፖለቲካው እንቅስቃሴ እንዲወጣ አሊያም ሀገር ለቆ እንዲሄድ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እንደሰጡት በራሱ የማኀበራዊ ሚዲያ ገፆቹ ላይ ይገልፅ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ወጣቱ ይሰጠው የነበረውን ማስፈራሪያና ዛቻም እንደማይቀበልና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉንም እንደሚቀጥል በተደጋጋሚ መግለፁን ከራሱ የማኀበራዊ ገፅ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተለይ በግንቦት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚደርስበት ዛቻና ማስፈራሪያ ተጠናክሮ መቀጠሉን እና ከሐሰት ክስ እስከ ግድያ የሚደርስ እርምጃ ሊወስዱበት እንደታሰበ ራሱ በፌስ ቡክ ገፁ የሚከተለውን ገልፆ ነበር፡-
ውድ የደብረማርቆስ ከተማ ኗሪዎች ፤ ሰማያዊ ፓርቲን የመረጣችሁ ከ25,0000 በላይ መራጮች(ኮረጆውን) እርሱት እና በተጨማሪም በ31 ዩኒቨርስቲ የምትገኙ ከ14,000 በላይ ሰማያዊ ፓርቲን የመረጣችሁ ሌሎች ደጋፊዎች እና የኢሕአዴግ አባላትም የማያፍረው ብአዴን / ኢሕአዴግ ድምፅ መቀማቱ ሳያንስ በ21/08/2007 ዓም አፍነው ደብድበው ከሞት መትረፌ ቆጭቷቸው እሰር ቤት ለመወርወር ያለመከሰስ መብቴን እንኳን ተዳፍረው የሀሰት ክሰ እየፈጠሩ ነው!!!” በስልኬ እደተደወለም ያለፍላጎቴ ደሕንነት እያስገደደኝ ይገኛል!!!!! ተገደልሁም ታሠርሁም ፤ ታፈንኩም ነፃነት አይቀርም እና ለማሰረጃነት የደሕንነቶችን ስም፤ ፎቶግራፍ ፤ እና አድራሻ እንዲሁም በሐሠት ምሰክርነት እና ከሳሽነት የተደራጁ አካላት እና ዋና ተወካዮች የደብረማርቆስ ከተማ 04 ቀበሌ አመራሮች እና ፖሊስ ለታሪክ አሰመዘግባለሁ፡፡ ማንኛውም የምከፍለው ዋጋ ለሀገሬ እና ለነፃነት ነው ከታሠርሁም ሕሊናዬ አይታሰርም ከገደሉኝም ትግሌን አደራ በተለይ የኔ ትውልድ አደራ !!!!” አገራችን የወያኔ ዘረኞች ብቻ መፈንጫ መሆን የለባትም፡፡ ትግላችን የነፃነት ጉዟችን ጎርባጣ መድረሻችን ነፃነት ታሪካችን ዘላለማዊ ነው!!!! (ከሳሙኤል አወቀ ዓለም – የሰማያዊ ፓርቲ የደብረ ማርቆስ የሕዝብ ተወካዮች እጩ ተወዳዳሪ)

ወጣት ሳሙኤል አወቀ

ወጣት ሳሙኤል አወቀ

የ27 ዓመቱ የህግ ባለሙያና የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበረው ወጣት ሳሙኤል የቀብር ስነ ስርዓት ሰኔ 9 ቀን 2007 ዓ.ም የትግል አጋሮቹ፣ ጓደኞቹና ዘመዶቹ በተገኙበት በምስራቅ ጎጃም ዞን በጎንቻ ሲሶነሴ ወረዳ ሰቀላ ቀበሌ ግንደወይን አርባይቱ እንሰሳ ቤተ ክርስቲያን ከቀኑ 11፡30 ላይ ተፈፅሟል፡፡ በዕለቱ ማታ ከቀብር መልስ ወደ ደብረማርቆስ ይመለሱ የነበሩ ወዳጆቹና ዘመዶቹ ታግተው እንደነበር የነገር ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡ የወጣት ሳሜኤል አወቀ አሟሟትን በተመለከተ እስካሁን ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ምንም ዓይነት ምላሽ የለም፡፡
በተያያዘ ዜና የዓረና መድረክ አባል አቶ ታደሰ አብርሃ በትግራይ ክልል በቃፍታ ሑመራ ማይካድራ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ሰኔ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ ሶስት ሰዎች አንቀዋቸው ሞተዋል ብለው ቢሄዱም ህይወታቸው እስከ ሌሊቱ 9፡15 ድረስ እንደነበርና ከዛ በኋላ ህይወታቸው እንዳለፈ የዓረና ፓርቲ መረጃ አመልክቷል፡፡ከዚህ በፊት አቶ ታደሰ ከዓረና/መድረክ ፓርቲ አባልነትና ተሳትፎ እንዲያቆሙ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ከደህነነቶችና ከህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮች ይደርሳቸው እንደነበርና ለዚህም አማላጅ ይላክባቸው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

አቶ ታደሰ አብርሃ

አቶ ታደሰ አብርሃ

የ48 ዓመቱ አቶ ታደሰ አብርሃ በፖለቲካው ንቁ ተሳትፎ ያላቸው መሆኑን እና እስካሁን ይህ እስከተዘገበበት ድረስ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታንቀው በተገደሉበት ወቅት በኪሳቸው የነበረው 300 ብር እንዳልተወሰደና ግድያው ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ተጠቁሟል፡፡ የአቶ ታደሰ አብርሃን ገዳዮችና አሟሟታቸውን በተመለከተ አስከሬናቸው በሑመራ ሆስፒታል ምርመራ እንዲደረግ ቢሞከርም የአካባቢው ፖሊሶችና የኢህአዴግ አመራሮች መከልከላቸውም ታውቋል፡፡ በሶስት ቀናት ልዩነት የሰማያዊ እና የዐረና/መድረክ አመራሮች ተገድለዋል፡፡
ክምርጫ 2007 ዓ.ም. ጋር በተያያዘ በታህሳስ 2007 ዓ.ም. የዓረና/መድረክ አመራር የነበሩት ልጅዓለም ኻልዓዩ ማንነታቸው እስካሁን ባልታወቁ ሰዎች አዲስ አበባ ላይ ሲገደሉ በምርጫው ወቅት የኦፌኮ/መድረክ አባል በአርሲ ኮፈሌ ና በደቡብ እንዲሁ አንድ መገደላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ከምርጫ 2007 ዓ.ም. ጋር በተያያዘ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት ግድያ እስካሁን ባይቆምም፤እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ ከመንግሥት የተሰጠ ምንም ምላሽ የለም፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: