በጋቦን ለሚዘጋጀው የ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 10 (J) ውስጥ የሚገኘውና በዮሐንስ ሳህሌ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን እሁድ ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሌሶቶ አቻው ጋር በባህር ዳር ስታዲየም ባደረገው ጨዋታ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ በጫወታው የሌሶቶ ብሔራዊ ቡድን ቀድሞ ጎል ያስገባ ሲሆን፤ ለኢትዮጵያ አቻ የምታደርገውን ውጤት የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች የሆነው ጋቶች ፓኖም አስቆጥሯል፡፡
በመጨረሻም ለግብፁ አል-ሃሊ ክለብ የሚጫወተው ሳላዲን ሰይድ ለኢትዮጵያ የማሸነፊያዋን ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር በስታዲየሙ የነበረውን ታዳሚ እና በቴሌቪዥን መስኮት ጨወታውን ሲከታተል የነበረውን ህዝብ በደስታ አስፈንጥዟል፡፡ በጫወታውም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 3 ነጥብና 1 ንፁህ ጎል ይዞ ወጥቷል፡፡ ከምድቡ አልጄሪያ ሲሼየልስን 4 ለ 0 በማሸነፍ በ3 ነጥብ እና በ4 ንፁህ ጎል ምድቡን እየመራች ስትገኝ፤ ኢትዮጵያ 3 ነጥብና 1 ንፁህ ጎል ይዛ ከምድቡ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በቀጣይም የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ ጫወታውን በሲሽየልስ ቪክቶሪያ ስታዲየም ከሲሽየልስ እግር ኳስ ቡድን አቻው ጋር ያደርጋል፡፡