ባለፈው ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ምርጫን ተክትሎ የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ባለፈው ሰኔ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰኣት ላይ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) አመራር አካል የነበሩት አቶ ብርሃኑ ኤረቦ መገደላቸውን መድረክ አስታውቋል፡፡ አቶ ብርሃኑ በደቡብ ክልል ሀዲያ ዞን በሚገኘው ሶሮ ወረዳ በዳና ቶራ ቀበሌ የፓርቲው የኮሚቴ አመራር አባልና በምርጫው ቅስቀሳም ላይ ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸውም ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በወቅቱ ግድያውን የፈፀሙት ብርሃኑ ደቦጭ እና ታዲዮስ ጡምቦ የተባሉ ፖሊሶች እንደሀኑ እና ከዛ በፊትም እነኚህ ፖሊሶች የመድረክ አመራሮች እና አባላቱን ሲያስፈራሩና ሲዝቱባቸው እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡ በተለይ አቶ ብርሃኑ ኤረቦ በሁለቱ ፖሊሶች መኖሪያ ቤታቸው ደጅ ተይዘው ከተደበደቡና ከተገደሉ በኋላ አስከሬናቸው ባካባቢው ባለ ወንዝ ተጥሎ እንደተገኘ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ ኤረቦ የተገደሉበት ሶሮ ወረዳ በምርጫ ዋዜማ መምህር ጌታቸው የተባሉ የመድረክ ዕጩ በኢህአዴግ በደረሰባቸው ጫና እና አስተዳደራዊ በደል በወረዳው አስተዳደር ፊት ራሳቸውን አቃጥለው ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ ወረዳው የኢህአዴግ ተወካይ እና የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሆኑት ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም የተወዳደሩበት ወረዳ መሆኑ ታውቋል፡፡
መድረክ ከግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ አቶ ብርሃኑ ኤረቦን ጨምሮ የተገደሉት የክልል አመራሮቹ ቁጥር አራት የደረሰ ሲሆን፤ እነኚህም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሚዳ ቀኝ ወረዳ አቶ ጊዲሳ ጨመዳ፣ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን ቆራ ወረዳ አቶ ገቢ ጥቤ፣ ከትግራይ ክልል ምዕራብ ትግራይ ዞን ማይካድራ ከተማ አቶ ታደሰ አብርሃ እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በምርጫው ወቅት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ የመድረክ አባላትና ደጋፊዎች በተለይም በደቡብ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ በርካታ ሰዎች እንደታሰሩ፣በጥይት ተደብድበው እንደቆሰሉ እና ቤቶቻቸው እንደተቃጠለ ከፓርቲው የተገኘ መረጃ አመልክቷል፡፡ በተመሳሳይም በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረማርቆስ ከተማ የሰማያዊ ፓርቲ አመራርና የህዝብ ተወካዮች ዕጩ የነበረው ወጣት ሳሙኤል አወቀም ተደብድቦ መገደሉ ይታወቃል፡፡ መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ አባሎቻቸው የተገደሉት በኢህአዴግ መሆኑን እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡