ድሬዳዋ ከነማ የ2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ አሸናፊ ሆነ
የ2007 ዓ.ም. በድሬዳዋ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ ውድድር ፍፃሜ ዛሬ ነሐሴ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከነማ እግር ኳስ ቡድን አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በፍፃሜ ውድድሩ ሆሳዕና ከነማ ከድሬዳዋ ከነማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ፤ ድሬዳዋ ከነማ ሆሳዕናን 3፡1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የ2007 ዓ.ም. ብሔራዊ ሊጉ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡
በኢትዮጵ ስፖርት ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ድሬዳዋ ከነማን ለዋንጫ በማብቃት ወደ ፕሪሚየር ሊግ ዳግም የመለሱት መሰረት ማኒ ሆሳዕና ከነማን 3፡1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለድል አብቅተዋታል፡፡
ድሬዳዋ ከነማ ለፍፃሜ የደረሰው የምዕራብ ኢትዮጵያ ወኪል ሆኖ ጫፍ የደረሰውን ጅማ አባ ቡና ክለብን 2፡0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነበር፡፡
ቀደም ሲል የእግር ካስ ተጫዋች የነበረውና የስፖርት ሳይንስ ባለሙያና መምህር ግርማ ታደሰ (መንቾ) የሚሰለጥነው የሆሳዕና ከነማ እግር ኳስ ክለብ አላባ ከነማን 3፡0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን ተቀላቅሏል፡፡
የብሔራዊ ሊጉ የ2007 ዓ.ም. በተደረገው የደረጃ ጨዋታ አላባ ከነማ ጅማ አባ ቡናን 4፡2 በሆነ የፍፃሜ መለያ ምት በማሸነፍ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡
አላባ ከነማ ከሆሳዕና ከነማ ለሚያደርገው የፍፃሜ ውድድር ድጋፍ ለማድረግ አርብ ነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ማታ ወደ ድሬዳዋ ይጓዙ ከነበሩት የአላባ ከነማ ደጋፊዎች መካከል በምዕራብ ሐረርጌ አሰበ ተፈሪ/ጭሮ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ 4ቱ ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ 12ቱ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው 12ቱ ደጋፊዎች ወደተሻለ ህክምና ሪፈር ስለተደረጉ እርዳታ ማስተባበር ስራ መጀመሩ ተጠቁሟል፡፡
የብሔራዊ ሊጉ ሻምፒዮና ድሬዳዋ ከነማ እና ሆሳዕና ከነማ በያዝነው 2007 ዓ.ም. በፕርምየር ሊጉ መጨረሻ ላይ ከሚገኙት መካከል 16 ነጥብ ብቻ በማምጣት የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወልዲያ ከነማ እና በውድድር ዓመቱ 27 ነጥብ በማምጣት 13ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ሙግር ሲሚንቶን ተክተው በመጪው 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ ውድድር ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ምንጭ፡- ሶከር ኢትዮጵያ