የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንደሌሉ ገለፀ

• “የስርዓቱን ሽፍትነት ያመላክታል” 3ኛ ተከሳሽ አቶ ደናሁን ቤዛ

• “የሚቀርብልን ምግብ ለእንሰሳትም መቅረብ የማይገባው ነው” 2ኛ ተከሳሽ አቶ አሸናፊ አካሉ

አንዳርጋቸው ፅጌ

አንዳርጋቸው ፅጌ

በዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ -5ኛ መዝገብ ለተከሰሱት አቶ አሸናፊ አካሉ (2ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ደናሁን ቤዛ (3ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን (4ኛ ተከሳሽ) እና አቶ አንሙት የኔዋስ (5ኛ ተከሳሽ) በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደሌሉ ማረሚያ ቤቱ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛው ወንጀል ችሎት በላከው ደብዳቤ ገልፆአል፡፡ 19ኛ ወንጀል ችሎት ሀምሌ 29 ቀን 2007 ዓ.ም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ለምን እንዳላቀረበ እንዲያብራራ፣ እንዲሁም ለምስክርነት እንዲያቀርብ ለዛሬ ለጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበር ቢሆንም ማረሚያ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ቃሊቲ እንደሌሉ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡

ተከሳሾቹ ማረሚያ ቤቱ ሲያጉላላቸው ቆይቶ አሁን የለም ማለቱ ትክክል እንዳልሆነ የገለፁ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽ አቶ አሸናፊ አካሉ ማረሚያ ቤቱ ምላሽ የሰጠው በአራተኛው ትዕዛዝ መሆኑን ጠቅሶ የፍርድ ሂደታቸውን ከሚገባው በላይ እያጓተተ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ገልፆአል፡፡ ‹‹መከላከል ከጀመርን አንድ አመት ከስድስት ወር ሆነ፡፡ በግዞት ነው ያለነው፡፡ የሚቀርብልን ምግብ ለእንሰሳትም መቅረብ የማይገባው ነው›› ያለው አቶ አሸናፊ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ ‹‹ፌዝ ነው›› ብሎታል፡፡

3ኛ ተከሳሽ አቶ ደናሁን ቤዛ በበኩሉ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት ሲጠቅሱ አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የሞትና የእድሜ ልክ ፍርደኛ እንደሆኑ በመጠቆም ተቃውሞ አሰምቶ እንደነበር፣ የእድሜ ልክና የሞት ፍርደኛ ቃሊቲ እንደሚታሰር ገልፆ ማረሚያ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው እንደሌሉ መግለፁ ‹‹የስርዓቱን ሽፍትነት ያመላክታል›› ብሏል፡፡ ‹‹የእድሜ ልክ ወይንም የሞት ፍርደኛ የት ነው የሚታሰረው?›› ሲልም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
3ቱ ተከሳሾች የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉና ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ አንዳርጋቸውን እንደያዙ በቴሊቪዥን መግለፃቸውን አስታውሰው አሁንም ለሁለቱ አካላት ደብዳቤ እንደሚፅፉ ለፍርድ ቤቱ አሳውቀው የነበር ቢሆንም ከ6ኛ-9ኛ ያሉት ተከሳሾች ማረሚያ ቤቱ በፈጠረው ችግር የአቶ አንዳርጋቸውን ምስክርነት ለመስማት የፍርድ ሂደታቸው እየተጓተተባቸው በመሆኑ የአቶ አንዳርጋቸው ምስክርነት ቀርቶ ብይን እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ሆኖም ግን 4ኛ ተከሳሽ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን ‹‹ከአንዳርጋቸው ጋር ተገናኝተህ መመሪያ ተቀብለሃል ስለተባልኩ አቶ አንዳርጋቸው መጥቶ መመስከር አለበት›› ሲል አሁንም አቶ አንዳርጋቸው እንዲቀርቡለት ጥያቄውን አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም 4ኛ ተከሳሽ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንዲቀርቡለት የሚያቀርበውን አቤቱታ ተመልክቶ ይገኙበታል ተብሎ ለታሰበው ተቋም ትዕዛዝ ለመስጠት ለጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ መሰጠቱን ነገረ-ኢትዮጵያ ዘገባ አመልክቷል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: