ያሬድ ሹመቴ
በምስጋናው ታደሰ የተደረሰውን “ሚካኤል ንጉሰ ወሎ ወትግሬ” የተሰኘውን አዲስ መጽሐፍ ለመመረቅ ጥቅምት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በደሴ አይጠየፍ አዳራሽ የተገኙ ምሁራን ማራኪ ሀሳቦቻቸውን በመድረኩ አቅርበዋል። ከአቅራቢዎቹ መሀል ለዛሬ የዶክተር ዳኛቸውን ውብ ገለፃ ለንባብ እንዲመች አድርጌ በማቀናበር እነሆ በዝርዝር አቅርቤላችኋለሁ።(ያሬድ ሹመቴ)
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ “እንግዲህ ንግግሬን የምጀምረው እንደ ጥሩ “ወሎዬ” በግጥም ነው። ገጣሚ ስላልሆኩ የኔን ሀሳብ የሚገልጸውን የቀኝ አዝማች ምስጋናው አዱኛን የተወሰነ ስንኝ ተውሼ ልጀምር።
‘በጣሙን ጨነቀኝ ልቤ ተበትኖ፥
እንጀራዬ ሸዋ ቤቴ ጎንደር ሁኖ።’
የዚህ ስንኝ መንፈስ የኔን አመለካከት ይገልጽልኛል ብዬ ስለማምን የሳቸውን ትከሻ ተንተርሼ እጀምራለሁ።
‘በጣሙን ጨነቀኝ ልቤ ተበትኖ፥
ውሎዬ ሸዋ ላይ ልቤ ወሎ ሁኖ።’
ብዬ እጀምራለሁ።
አልፎ አልፎ ከምስጋናው ጋር ስለዚህ መጽሐፍ በስልክ ስናወራ እኔ “ራስ ማይክ” ብዬ ስጠራው እሱ ደግሞ “የሰገሌው” ብሎ ይጠራኛል። ሁለቱም ምክንያት አላቸው። እሱ ስለ ራስ (የኃላው) ንጉስ ሚካኤል ስለጻፈ፥ ራስ ገብረየስ የተባሉ የኔ ቅድመ አያት ከዚች ቦታ [አይጠየፍ] ተነስተው ከራስ ሚካኤል ጋር አብረው ሰገሌ ዘምተው [በኃላ በራስ ካሳ ስር እስረኛ ሁነው ቢመለሱም] ወሎየነቴ ሰገሌን ያልፋል ለማለት ነው እንጂ እንዲያው በዚህ ሳልፍ እግረ መንገዴን ወሎዬ ነኝ አላልኩም ለማለት ነው።
ወሎዬ ነኝ ስል፥ አደራችሁን፥ ሰሜን ወሎ ነኝ አላልኩም። ደቡብ ወሎ አላልኩም። አርጎባም አላልኩም። ከሚሴ ነኝም አላልኩም። ሚሌም ነኝ አላልኩም። በደፈናው ወሎዬ ነኝ ነው ያልኩት።
እንግዲህ እንጀምር፡-
ትልቁ የጀርመን ፈላስፋ ሄግል አንድ ቦታ ላይ ስለ ታሪክ እንዲህ ይላል። ‘አፍሪካ በደፈናው ታሪክ የላትም። ይህንንም ስል ምክንያቴ ስለማትጽፍ ነው’ ይላል። በሱ አነጋገር ‘እንዲያውም ትንሽ ታሪክ ላይ የደረሱት አረቦቹ ናቸው። እነሱ ይጽፋሉና’ ይላል። እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደምንጽፍ ሄግል አያውቅም። የምስጋናው መጽሐፍ ለዚህ መልሱ ነው። የንጉስ ሚካኤልና የወሎ ታሪክ ባይፃፍ ኖሮ ተረት ተረት ሆኖ ነበር የሚቀረው።
ሁላችንም ቤት ውስጥ [ይህ ታሪክ] የአፍ ብቻ ታሪክ ሆኖ ተቀምጦ ኖሯል። “ካልተጻፈ ታሪክ የለም።” መጻፍ መዘገብ ካልቻለ በአፍ ያለው ጠፍቶ ተረት ተረት ሆኖ ይቀራል። ታሪክ ከጽሁፍ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ መፃፍ አለበት። ለዚህ ደግሞ ምስጋናው ተገቢ መልስ በመስጠቱ ባለውለታችን ነው የሚል እምነት አለኝ።
ሌላው ከክርስቶስ ልደት 600 ዓመት በፊት የነበረው ታላቁ ግሪካዊው የታሪክ ቀመር መስራች ሱሲዲየስ ምን ይላል? ‘ታሪክን ለመፃፍ የሚነሳ ሰው ቢያንስ ቢያንስ አርባ አመት ቢሞላው ይመረጣል’ ይላል። ‘ፀሀፊው እድሜው የጠና ካልሆነ እንዲሁ የሆነውን ያልሆነውን እየጻፈ ህዝብ ያበጣብጣል።’ ሲል ያክላል።
በአንድ በኩል እውነቱን ነው። ባለፉት ከ25 እስከ 30 ዓመታት ውስጥ የወጡትን “የታሪክ ድርሳናት” ስንመለከት መርዶ አቅራቢዎች ናቸው። ‘በእንዲህ ያለ ጊዜ እንዲህ እና እንዲያ ተደርገሀል፥ በእንዲህ ያለ ቦታ እንዲህ ተደርጎብሀል’ እየተባለ ይፃፋል። ታሪክ የተወሳሰበ ዲሲፕሊን ነው። ከመርዶ ነገራ በእጥፉ ይለያል።
በተጨማሪም ታሪክ ከመርዶ ነገራ አልፎ የርዕዮተ ዓለም እና የፖለቲካ አሽከር በሚሆንበት ጊዜ ብዙ ጣጣ ይመጣል። ርዕዮተ አለሙ ይቀድምና ታሪክ የበታችነትን ቦታ ትይዛለች። ይሄን ልጅ (ምስጋናው) ከዚህ አንፃር ስናየው 40 ዓመት ገና አልሞላውም። እንዲያውም አንድ ሰው ለአንድ ጓደኛዬ ’40 አመት ያልሞላው ሰው ታሪክ መፃፍ የለበትም ብሏል ዳኛቸው። እድሜው ያልደረሰውን ምስጋናው የፃፈውን መጽሀፍ ለመመረቅ ለምን ሄደ?’ ብሎ ጠይቋል። ስለ ታሪክ አረዳድ፥ ስለታሪክ ምርምር እና ስለ ታሪክ ትንተና እስከ ከፍተኛ ትምህርት ደርሶ የተማረው ምስጋናው፥ ትምህርቱ ባበረከተለት እውቀት የእድሜውን ማነስ ተሻግሮታል ብዬ አምናለው። እውቀት የእድሜን ክፍተት ይሞላልና።
የዚህ መጽሀፍ ንባብ ሲጀመር ገና ከጠዋቱ ጥያቄዎች ተጀምረዋል። አንዱ ‘የኔን አያት በደንብ አልፃፋቸውም’ ሲል ሌላው ደግሞ ‘የኔ ቅድም አያት ሊቀ መኳስ እከሌን አሳንሶ ጽፏቸዋል’ [እንዲህ እንዲያ] ወዘተርፈ ይላል። ለዚህ ደግሞ አጭሩ መልስ፥ የታሪክ ጸሀፊ ሊዘግበው በተነሳው ርዕስ ዙሪያ ሁሉንም ምንም ሳይተው አጠቃላይ ዘገባ ማቅረብ በፍፁም አይቻለውም። በመሆኑም የታሪክ ዘገባ የሚከናወነው ወሳኝ የሚላቸውን ጉዳዮች በመምረጥ እንጂ ሁሉንም በማካተት ሊፃፍ አይችልም።
[ሌላው ጉዳይ] ታሪክን ከአንድ ከማይላወስ እና ከማይነቃነቅ መድረክ ላይ ሆነን የምንረዳው እውነታ አይደለም። ታሪክ ምን ግዜም ተለዋዋጭ እና ፈሳሽ መሆኑን ማጤን ተገቢ ነው። ለምሳሌ የመንግስቱ ነዋይን ግርግር ደርግ ከመምጣቱ በፊት ያጠና ሰው የወታደር መፈንቅለ መንግስትን የሚያይበት አተያይ አለው። ከነመንግስቱ ነዋይ በኋላ የወታደር መንግስት 17 ዓመት በስልጣንከቆየ በኋል የመንግስቱ ነዋይን ታሪክ የሚያጠና ሰው አተያዩ በጭራሽ እንደ መጀመሪያው አይሆንም። ስለዚህ ታሪክን ከተለዋዋጭነቱ ሁኔታ አንጻር ማየት የግድ ይላል።
በሌላ መልኩ ደግሞ ዋናው የቀደመ ታሪክን ለመረዳት፥ የጀርመን ፈላስፋዎች እንደሚሉት አሁን ባለንበት በኛ ዘመን እና ባለፈው ዘመን መካከል የአተያይ አድማሳት ዑደትን ማግኘት ተገቢ ነው። (fusion of horizon)በመሆኑም 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን 19ኛውን ክፍለ ዘመን ለመረዳት ሀሳባችንን መንፈስና ቀልባችንን ወደ ዘመኑ መላክ ተገቢ ነው። ያለፈውን እሴት ወግ እና መቼት በሚገባ ካላጠናን፥ የኛን ዘመን የአመለካከት ዘይቤ ብቻ ይዘን ያንኛውን ዘመን ልንረዳው አንችልም። በመንፈስ ልናጠናው ወደ ፈለግነው ዘመን እስካልተጠጋን ድረስ ያ ዘመን ለኛ ምን ግዜም ባይተዋር ሆኖ ይቀጥላል።
ከዚህ አኳያ ስንመለከት የምስጋናው ታደሰ መጽሐፍ ከመቶ አመታት በፊት የተካሄደውን የታሪክ ሂደት ከውጭ ሆኖ ሳይሆን በጊዜው እንዴት ያስቡ እንደ ነበርና የአመለካከት አድማሳቸውን በተገቢ አውድ በማስቀመጥ አቅርቦታል።
ወደ ሌላ ነጥብ ስናልፍ፥ ስለ መሪዎቻችን በምናወሳበት ጊዜ በአንድ ወጥ ትረካ መሪዎቹን አናገኛቸውም። እንደ ምሳሌም መምህር አለማየሁ ሞገስ ‘መልክዓ ኢትዮጵያ’ ላይ ከሰበሰቧቸው ስነ ቃሎች መሀል አፄ ቴውድሮስ ሲሞቱ የተገጠመላቸውን ሙሾ ላንሳላችሁ።
“ከመላክ ከሰይጣን እግዜር የሰራው…
….ቆንጥረው ቆንጥረው ሁሉን ያካበቱ
የመጨረሻው ቀን ግስላ ሆኑና ታነቁና ሞቱ’
‘ቆንጥረው ቆንጥረው ሁሉን ያካበቱ’ የሚለውን ያዙልኝ።
ሁሉም መሪዎቻችን ቆንጥረው ቆንጥረው ሁሉን ያካበቱ ናቸውና። በአንድ ቁንጠራ አንፍረዳቸው። ሚካኤል ስንል የዓድዋውን ሚካኤል ማስታወስ ሊኖርብን ይገባል። ሚካኤል ስንል ይህንን ወሎ የተባለውን ሀገር ያቆሙልንን ልናወሳ ይገባል። ሚካኤል ስንል ደግሞም ከአፄ ዮሀንስ ጋር ሆነው በኃይማኖት ጉዳይ ችግር የፈጠሩትን ልናነሳ እንችላለን። ይሄንን መቀበል ይኖርብናል። አንዷን ብቻ ይዘን ሚካኤል ይሄ ነው ለማለት በጣም አስቸጋሪ ይሆንብናል።
አፄ ቴውድሮስ ቆንጥረው ቆንጥረው ሁሉን ያካበቱ እንደተባሉት ማለት ነው። እዚህ መሀል ጎንደሬዎች ካላችሁ እንዳትቀየሙ። ስለሳቸው ከጀግንነት ውጪ ያወራ ሰው ሊሰዋ ይችላል ተብሏል አሉ። (ከፍተኛ ሳቅ)
ወደ ሌላ ወሳኝ ጉዳይ ስናመራ፥ ከወሎ ባህል ያፈነገጠውን ሙስሊሞችን ክርስቲያን የማድረግ ዘመቻ – የአፄ ዮሐንስ ፖሊሲን እናገኛለን። ምስጋናው በመጽሀፉ ምንም የደበቀው ነገር የለም። እንዲያውም ‘አራት እና አምስት አመታት ለወሎ ሙስሊሞች የጭንቅ አመታት ነበሩ’ ይላል። ትልልቅ ሸሆች ተጋድለው መስዋዕትነት መክፈላቸውንም ይተነትናል።
እኔ ንጉስ ሚካኤል ከአፄ ዮሐንስ ጋር አብረው ስህተት ሰርተዋል ነው የምለው። በወሎ ሙስሊሞች ላይ ትልቅ ጫና እና ሰቆቃ ደርሶባቸዋል። ከፊሉ ለስደት ሲዳረግ ከፊሉ ተቃውሞ ጀሀድ አውጆ ለሀይማኖቱ ተጋድሎ ተሰውቷል። ቀሪው ደግሞ ክርስትናን የተቀበለ መስሎ ህይወቱን አትርፏል። ምንም የሚያስደብቅ ነገር የለም። መሪዎች በሁሉ ነገር ልክ ናቸው ማለት አንችልም።
በምስጋናው መጽሐፍ ውስጥ ሙስሊሞቹ በጉልበት እንዲጠመቁና የክርስቲያን ስጋ እንዲመገቡ ሲገደዱ ቅሬታቸውን በሚያንፀባርቅ ስነ ቃል ስሜታቸውን ገልፀዋል እንዲህ ሲሉ ገልፀዋል።
“ታላቅ ታናሽ በላን ከርካ አደባባይ
አለ ልብ ስጋ ይጣፍጣል ወይ”
እንደዚሁም ሸህ ሁሴን ጅብሪል፡-
“ለጥቂት ቀን ብዬ አልበላም ነጃሳ
ወንዝ ለወንዝ ሄጄ እበላለሁ አሳ″
በሌላ በኩል ደግሞ ‘ሰው ያላመነበትን እንዲቀበል ማስገደል ልክ አይደልም’ ሲሉ ሊቁ ክርስቲያን መምህር አካለ ወልድ ይህን ዘመቻ አለመውደዳቸውን ገልፀዋል።
ይህ ሁሉ መዓት ከወሎ ህዝብ ከራሱ የመጣ አለመሆኑንም ማረጋገጥ ከፈለግን፥ አፄ ዮሐንስ አልፈው አፄ ምኒልክ ሲነግሱ፥ የክርስትና ሀይማኖትን በኃይል የመጫን ፖሊሲ ሲያበቃ፥ በወሎ ሙስሊም እና ክርስቲያን መሀል የነበረው የቀደመ ፍቅር መልሶ ቀጥሏል።
ንጉስ ሚካኤልን በኃይማኖት ጉዳይ የነበራቸውን ክፉ ጥላ ትንሽ ይቅር ለማለት የምንችለው የአፄ ዮሐንስ ስርዓት ሲያከትም ይኸው ተግባርም በዚያው በማክተሙ ነው። እንዲያውም ልጃቸው አቤቶ እያሱ ኢትዮጵያን የማስተዳደር ስልጣን ሲያገኙ፥ “ሙስሊምና ክርስቲያኑ እኩል ሊታይ ይገባል” ባሉ ጊዜ ንጉስ ሚካኤል አልተቃወሟቸውም ። ይሄ እሳቸውን ትንሽ ይቅር ለማለት ያስችለናል።
ከማመዶቹ ስርዐት ጋር ተፋልመው ከአፄ ዮሐንስ እና አፄ ምኒልክ ዘመን ጋር ተፋልመው ወሎ የፖለቲካ ወሳኝ ማዕከልነትን ቦታ እንድትይዝ ሲያደርጓት ደግሞ ታያላችሁ። አፄ ምኒልክ እንዳረፉ የአቤቶ እያሱን አልጋ ወራሽነት ፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ሲያውጁ ‘ሸዋ ተስማምቷል፥ ወሎ ተስማምቷል’ ብለው ነው የሚጀምሩት። ይህ አዋጅ ከአጀማመሩ የወሎን የፖለቲካ ማዕከላዊነት ያሳያል። በነገራችን ላይ አሁን በያዝነው ዘመን ሸዋ ተስማማ ወሎ ተስማማ ምንም ለውጥ ያለው አይመስለኝም። (ከፍተኛ ሳቅ) ነገሮች ተለዋውጠዋል።
ሌላው የኔ ልብ የሚመታው ሰገሌ ላይ ነው። ሰገሌን የሚመለከት ያለኝ ምክረ ሐሳብ (thesis) ፥ ንጉስ ሚካኤልን “ክርስትና ዘውድ ጫነላቸው በአንፃሩ ደግሞ የክርስትና እምነታቸው ዘውዳቸውን ነጠቃቸው” ነው እኔ የምለው። ክርስቲያን ባይሆኑ ኖሮ አይነግሱም ነበር። ደግሞ ደንበኛ አማኝ ክርስቲያን ባይሆኑ ኖሮ ሰገሌ ላይ አይሸነፉም ነበር። “የፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ደብዳቤ አታለላቸው” የሚለው የልጆች ተረት ተረት ነው ለኔ። መስቀል ተልኮ ትልልቅ ቀሳውስት አባቶች ካህናት ተልከው እንዴት እምቢ ይበሉ? አማኝ ናቸዋ።
እዚህ ላይ የኒኮሎ ማኪያቬሊን አስተምህሮት ማስታወስ ጠቃሚ ይሆናል። ለማኪያቬሊ ሁለት አይነት የሞራል አድማስ አለ። አንደኛው “የክርስቲያን ሀይማኖታዊ ‘ሞራሊቲ′ (ግብረ ገብ)” ይለዋል። ሁለተኛውን “ማህበረሰባዊ የፖለቲካ ሞራሊቲ″ ይለዋል። በመሆኑም ፖለቲካል አለም ውስጥ መጠቀም ያለብን የማህበረሰባዊ የፖለቲካ ሞራሊቲን እንጂ የክርስቲያን ሀይማኖታዊ ሞራሊቲ አይደለም” ይላል።
ለመሆኑ በሁለቱ የሞራሊቲ መርሆች መካከል ልዩነቱ ምንድን ነው?
ለማኪያቬሊ የክርስቲያን ስነ ምግባራት እንደ ርህራሄ፥ ለቃል መታመን፥ መሀላ፥ መማለድ እና ወዘተርፈ ሲሆኑ። በአንፃሩ የፖለቲካ ሞራሊቲ ማለት የወጠንከው ግቡ ላይ ለመድረስ ማናቸውንም አማራጮች የሞራል መስፈርት ጥሶ ያለ ገደብ መጠቀም ማለት ነው። ለምሳሌ፡- ሀይማኖትን እንደ መሸምገኛ መጠቀም፥ የማያከብሩትን ቃል መግባት፥ በውሸት መማል፥ ወዳጅነትን እንደ ማዘናጊያ ማቅረብ እና ወዘተርፈ።
ወደ ሰገሌ ስንመጣ ሸዋ የፖለቲካ ሞራሊቲ ይዞ መጣ። ወሎ የክርስቲያን ሞራሊቲ ይዞ ቀረበ። የምስጋናው መጽሐፍ እንደሚያስተምረን፥ ንጉስ ሚካኤል፥ ከሸዋ ቀድሞ የመጣውን የራስ ልዑል ሰገድን ጦር ቶራ መስክ ላይ ከደመሰሱ በኋላ ገስግሰው ወደ አዲስ አበባ ሳይገቡ ለምን እንደ ቀሩ እና የሸዋው ኃይል ከየጠቅላይ ግዛቱ ጦሩን እስኪያሰባስብ ድረስ ለምን ሰገሌ ላይ እንደቆዩ ብዙ ጊዜ የሚሰጠው መልስ የሚከተለው ነው።
“ፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ በተለመደው ብልሀታቸው ከንጉስ ሚካኤል ጋራ እንደሆኑ እና አቤቶ እያሱን እንዳልከዱ በመግለጽ ለጊዜው አሉበት ቦታ ሆነው እንዲቆዩላቸው መልዕክት ልከው ስላታለሏቸው ነው።” ይባላል። ይሔ ለኔ ተረት ተረት ነው።
የአሸናፊዎቹ ተረት ተረት የሆነው ደብዳቤ ተጽፏል ወይ? አዎ ተጽፏል። ግን ከልባቸው አምነው የተታለሉት ለመስቀሉ ነበር። የክርስትናን እውነታ ፀንተው ስለያዙ ተታለሉ። ‘ክርስቲያ አይዋሽም። ክርስቲያን ቃሉን ይጠብቃል’ ከሚል እምነታቸው ተነስተው ዘውድ የሰጣቸው ክርስትና በእምነታቸው ምክንያት ዘውዱን መልሶ ነጠቃቸው።
ንጉስ ሚካኤል በእመነታቸው ፀኑ። ሀብቴ አባ መላ ግን “መስቀልም አውጥተን ታቦትም አውጥተን ይሄን ሰው ማሸነፍ አለብን” አሉ። ይሄ ማለት ከላይ ለማሳየት እንደሞከርነው ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ የማኪያቬሊን የፖለቲካ ሞራሊቲ ይዘው ሲመጡ፥ እኚህ ደግሞ የክርስቲያን ሞራሊቲ ይዘው ስለቀረቡ ለኃብተ ጊዮርጊስ “ክርስቲያናዊ” ጥሪ ታምነው የፖለቲካዊ ሞራሊቲ ሰለባ ሆኑ።
ዕምነቱን እንደ መሰሪያ የተጠቀሙት ፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ብልህ ብልጥ ሲባሉ፥ በሀይማኖታቸው መርህ የፀኑት ንጉስ ሚካኤል ግን ገራገር ተባሉ። ይኸው እስካሁን ወሎ ገራገሩ እየተባለ ይዘፈናል። (ሳቅ) ወይ ሀብቴ አባ መላ… ይሄ መቼስ የሚገርም ነው። (ሳቅ)
በመጨረሻም፡-
አደራ እምለው፥ ከወሎ ባህል ያፈነገጠና አስከፊ የሆነው የእምነት ጫና እና ግፊት ህዝቡ ተሻግሮ እንዳለፈው ሁሉ፥ የወሎን ህብረ ብሔራዊነት ተፃፈ ከተባለው ህገ መንግስት እና ፌዴሬሽን በፊት በወሎ የኖረውን የሀይማኖት መደጋገፍ እና ተቻችሎ በፍቅር የመኖርን ባህል አንግሶ መቀጠል ይገባናል ስል ንግግሬን እጨርሳለሁ። አመሰግናለሁ።” (ታላቅ ጭብጨባ)
ዶክተር ዳኛቸው ጋር የቀረቡ ሌሎች ጥናቶችን በሌላ ጽሁፍ እመለስባቸዋለሁ። በእለቱ ከተሳታፊዎች ጥያቄዋች እና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
አንድ መንፈሳዊ አባት በንግግራቸው ንጉስ ሚካኤል በእምነታቸው ጥልቀት አማካኝነት መሸነፋቸው የሀይማኖት ሰማዕት እንዳደረጋቸው በመግለጽ ዘውትር ስመ ክርስትናቸውን በቤተ ክርስቲያን እየተነሳ ፀሎተ ፍትሀት ይደረግላቸዋል” ሲሉ የምሁሩን ሀሳብ አጠናክረዋል።
በተሳታፊዎች “ታሪክን ወደ ኋላ ሂዶ መዘገብ ስለምን በመንግስት በኩል አስፈሪ ሊሆን ቻለ?” የሚል እና የንጉስ ሚካኤልን ሀውልት ማቆም የተመለከቱ ጥያቄዋች ቀርቦ፥ ዶክተር ዳኛቸው ሲመልሱ “የንጉስ ሚካኤልን ሀውልት በሚመለከት፥ ሲታሰብ የሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ለሀይማኖታቸው ሲሉ የወደቁ ኢማሞች አሉና ለነሱም ሀውልት ሊቆም ይገባል። ምን አልባት በእስልምና ሀይማኖት ሀውልት የማይፈቀድ ከሆነ በስማቸው የጥናት ማዕከላት ሊገነቡ ይችላል። የራሳችን ታሪክ አካል ስለሆነ ተቻችለን ተሳስበን መዘከር ይገባናል።
ታሪኩ ለምን አልወረደም ላልሽው፥ እኔ እምልሽ ታሪክ በጣም ከባድ ነገር ነው። አንድ አንድ ጊዜ ታሪክ የፖለቲካ አሽከር የምትሆንበት ጊዜ አለ። የፖለቲካ ሀይሉ ጠምዝዞ ይመራዋል። በአፄ ኃይለ ስላሴ ጊዜ ስለ ልጅ እያሱ መፃፍ በጣም አስቸጋሪ ነበር። በደርግ ጊዜ ስለ አፄ ኃይለ ስላሴ መፃፍ አስቸጋሪ ነበር። አሁን ደግሞ አንድ አንድ ሁኔታዎች መፃፍ አስቸጋሪ ነው። ከዚህ አልተላቀቅንም።
እንዲያውም “ሀቅ ሀቁን ለህፃናት” የሚል የፕሮፖጋንዳ መጽሀፍ ተለቋል አሁን። እሚገርም ነው መቼም። አስቸጋሪ ነው። አረ ተመስገን ነው። አይጠየፍ ሁነን እንዲህ ያለ ውይይት ማድረጋችንም ተመስገን ነው። (በከፍተኛ ሳቅ እና ጭንጨባ ተቋጨ)
ምንጭ፡- ቋጠሮ ድረ-ገፅ