አዲስ አበባን ከሌሎች አጎራባች ከተሞች በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር በሚል በመንግሥት ይፋ ባደረገው አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ከትናንት ጀምሮ በድጋሚ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡
በተለይ በምዕራብ ሸዋ አምቦ፣ ጊኒጪ እና ምዕራብ ወለጋ ተቃውሞው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በተቃውሞው ከተሰለፉት መካከል በመንግሥት በተወሰደ ርምጃ በምዕራብ ሸዋ ድሬ ኢንጪኒ አካባቢ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉም መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በዋናነት ተቃውሞን የቀሰቀሰው አዲሱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን ያከተተ በመሆኑ እና የዞኑን እና የክልሉን ጥቅም እንዲሁም ገበሬዎችን ያለምንም በቂ ካሳና ቦታ በማፈናቀል ለጎዳና ህይወት ይዳርጋል የሚሉ ሐሳቦች እንደሚገኙበት የተጠቆሙ ሲሆን፤ ይህንን ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ ኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት አባል ከሆነው ከኦህዴድ አመራር አባላት ከመፅደቁ ውጭ ወደ ህዝብ ያልወረደና ለምክክርም እንዳልቀረበ ታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት የዚህ ማስተር ፕላን ተቋውሞው በ2006 ዓ.ም. በመንግሥት በተወሰደ እርምጃ በርካታ ተማሪዎች እና የተቃውሞ ታዳሚዎች ግድያ ከቆመ በኋላ ድጋሚ ማገርሸቱ ተሰምቷል፡፡
በአንዳንድ ከተሞች የመኪና መንገዶች የተዘጉ ሲሆን፤ በተቃውሞው የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችም መካተታቸው ታውቋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ምንም የተሰጠ ማብራሪያም ሆነ አስተያየት የለም፡፡