በጎንደር ህዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በእስር ቤት ላይ በደረሰ ቃጠሎ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተነገረ፡፡ መንግሥት ከቃጠሎው ወቅት አንድ ሰው መግደሉን ሲያምን ሌሎቹ 16 ሰዎች ህይወት የጠፋው በቃጠሎው ወቅት ከ እስር ቤቱ ለማምለጥ ሲጋፉ ነው ብሏል፡፡
የአማራ ክልል ፖሊስ ለመንግስት ሚድያ በሰጠው መግለጫው በህዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎንደር ወህኒ ቤት ከቀኑ 7፡30 ሰዓት አካባቢ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ እስረኞች ከቃጠሎው ለመውጣት በተደረገው ግፊያ የ16 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ አንድ ሰው ሊያመልጥ ሲል ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መገደሉን አምኗል፡፡
እንደ ዓይን እማኞች ከሆነ ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቁጥር ከ42 በላይ እንደሚሆን እና መንግሥት ቁጥሩን ዝቅ በማድረግ በእጁ የጠፉትን ቁጥር ወደ አንድ ብቻ ማሳነሱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ እንደ ዓይን እማኞች ገለፃ ከሆነ በቃጠሎው ወቅት መንግሥት በእስረኞች ላይ ጠከታታይ ተኩስ ከፍቶ እንደነበርና የእስረኞችንም ህይወት ለማትረፍ ማንም ወደ አቅራቢያው እንዳይጠጋ የጥብቃ ኃይሎች እና ፖሊሶች ማንም የውጭ ሰው እንዳይጠጋ ሲያስፈራሩ እንደነበር ጠቁመው፤ ከሞቱት መካከል አብዛኛው በመንግሥት እጅ የተገደሉ እንጂ ከእስር ቤት ከእሳት ለማምለጥና ለመውጣት ሲጋፉ እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡
ከሞቱት በተጨማሪ በቃጠሎው በርካታ እስረኞች ጉዳት እንደደረሰባቸውና በጎንደር ሆስፒታል የህክምና እርዳታም እየተደረገላቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ የቃጠሎውን መንስኤና የተጎዱትንም ሆነ የሞቱን በተመለከተ እስካሁን በገለልተኛ አካል የተጣራ ነገር አለመኖሩ ታውቋል፡፡
በተለይ በሰሜን ጎንደር ዞን ከቃጠሎው በፊት ባሉት ቀናት የቅማንት ማኀረሰብ ባነሱት የመብት ጥያቄ ፖሊስ በወሰደው የኃይል እርምጃ እስካሁን በገለልተኛ አካልም ሆነ በመንግሥት ተጣርቶ ይፋ ባይደርግም በርካታ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውና የተወሰኑትም ምስሎቻቸውም በማኀበራዊ ሚዲያ ይፋ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
የወህኒ ቤቱ ኃላፊ በቃጠሎውም ሆነ በመንግሥት ኃይሎች እርምጃ የሞተ ሰው የለም በሚል ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡ ሲሆን፤ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ 16ቱ በቃጠሎው ወቅት በተፈጠረ መገፋፋት ሲሞቱ አንዱ ግን ሊያመልጥ ሲል በወህኒ ቤቱ ጥበቃ አባላት መገደሉን በማመን እስካሁን 17 ሰዎች መሞታቸውን አምነዋል፡፡ በተለይ በዞኑ ሰሜን ጎንደር መንግሥት በህዝቡ ላይ እየወሰደ ስላለው የኃይል እርምጃ እና በጎንደር ወህኒ ቤት በቃጠሎው እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር መደበቅና መቀነስ የተበሳጩ የጎንደር ዩኒቨርስቲ በተለይ ማራኪ እየተባለ በሚጠራው ግቢ የተማሪዎች ተቃውሞ መቀስቀሱን ተሰምቷል፡፡ በአሁን ወቅትም ተቃውሞው ወደሌሎች የዩኒቨርስቲው ግቢ እና ወደ ሌሎች የክልሉ ተቋማት ሊስፋፋ ይችላል በሚል ስጋት ዩኒቨርስቲው በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ተከቦ ጥብቅ ቁጥር እየተደረገበት መሆኑንም የአዲስ ሚዲያ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡