በተለይ ከህዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ምዕራብ ሸዋ ጊኒጪ የተጀመረው የተማሪዎች የአዲስ አበባ እና የፊንፊኔ ልዩ ዞን ኦሮሚያ ክልል የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ትግበራን በመቃወም እስከ ታህሳሥ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. 76 ሰዎች በመንግሥት በተወሰደ ሃይል እርምጃ መገደላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ መድረክ በበኩሉ መግለጫውን እስኪሰጥ በረደሰው መደረጃ መሰረት በመንግሥት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 32 ደረስው እንደነበር አስታውቋል፡፡ የሟቾቹ ቁጥር ዛሬም የጨመረ መሆኑን መረጃዎች የጠቆሙ ሲሆን፤ የሟጮች ቁጥር ከ82 በላይ መድረሱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ከተገደሉት መካከልም ከ10ዓመት ህፃን የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እስከ 78 ዓመት አዛውንትና የልጆች አባት እንደሚገኙበት መረጃዎች የጠቆሙ ሲሆን፤ በርካታ ሰዎችም መቆሰላቸውን እና መታሰራቸውም ታውቋል፡፡
መድረክ የመንግሥት እርምጃን በማውገዝ ታህሳሥ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. መግለጫ፤ ከሁለት ሳምናታት በላይ በዘለቀው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ተቃውሞ 32 ሰዎች በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ መድረክ የተገደሉትን ሰዎች ስም ዝርዝር እና አካባቢም በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
በክልሉ በተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ ዛሬ ረቡዕ ታህሳሥ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ እንደቀጠና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችም የተገደሉ እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ በተለይ የተቃውሞ ሰልፉ ዛሬም ከቀጠለባቸው ከተሞቸ መካከል በምዕራብ ሐረርጌ አሰቦት፣ በምበአርሲ አሰላ፣ በምዕራብ ሸዋ ኢጃጂ፣በኢሉባቦር መቱ፣ በምዕራብ ወለጋ ነጆ እና ቢላ፣ በምስራቀረ ጎጃም ነቀምት እንዲሁም በቡራዩ ጨምሮ በተለያዩ ከተሞችና ተቋማት ተቃውሞው ተጠናክሮ መቀጠሉ ታውቋል፡፡ ዛሬ በነጆ በነበረው ተቃውሞም 4 ሰዎች መገደላቸውንም መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ የዛሬዎቹን ግድያዎች ጨምሮ ሶስተኛ ሳምንት ባስቆጠረው ህዝባዊ ተቃውሞ በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ የኃይል እርምጃ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ82 በላይ መድረሱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡በክልሉ ባሉ ከተሞች ባሉ የተለያዩ ትምህርት ተቋማት ትምህርት መቋረጡ ታውቋል፡፡
ህዝባዊው ተቃውሞው ከክልሉ ተወላጆች በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ከሀገር ውጭ ባሉ በርካታ ሰዎች የአጋርነትና ድጋፍ እንደተቸረው እየተገለፀ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት በተለይ በክልሉ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ የአካባቢው የኢህአዴግ አመራሮችና ከየት እንደመጡ ባልታወቁ የስርዓቱ አካላት ባካባቢው ያሉ አማራና ኦሮሞን ለማጋጨት ተደጋጋሚ ሙከራ ማድጋቸውን እና በዚህም 4 የአካባቢው የአማራ ተወላጆች ሲገደሉ፣ ቤቶቻቸው የተቃጠሉና ንብረቶቻቸው ባልታወቁ ሰዎች እንዲዘረፍ በማድረግ በርካቶች መፈናቀላቸውን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡ ተቃውሞውን ክህዝቡ ጥያቄ በተቃራኒ ወደ እርስ በርስ ብሔር ግጭት ለማድረግ የተሞከረውንም ድርጊት የአካባቢው የኦሮሞ ማኀበረሰብ አዛውንቶችና ወጣቶች እንዲቆም ማድረጋቸውን እና በድርጊቱም የተበሳጩ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የርስ በርስ የብሔር ግጭት ለመፍጠር ሲሰሩ ከነበሩ የገዥው ስርዓት የአካባቢው የኦህዴድ/ኢህአዴግ አመራር አካላት መካከል አንዱ ወዲያው መገደሉንና ሌሎቹ ሸስተው ከአካባቢው ማምለጣቸውን የአዲስ ሚዲያ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ የተፈናቀለው ህዝብም ወደነበረበት አካባቢ እንዲመለስ የአካባው አዛውንቶችና ወጣቶች እየሰሩ እንደነበርም መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በሚኒስተሩ አቶ ጌታቸው ረዳ አማካኝነት በሰጠው መግለጫ በኦሮሚያ ከተሞች በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ የመንግሥት አካላት ላይ ጉዳት መድረሱን በመግለፅ መንግሥት የኃይል እርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሚኒስትሩ በታቀውሞው በመንግሥት አካላት ላይ ደረሰ ስላሉት ጉዳይ በዝርዝር የገለፀቱት ነገር ባይኖርም፤ በተቃውሞ ሰልፉ ስለተገደሉ ሰዎች ግን ያሉት ነገር የለም፡፡ በትናትነው ዕለት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ የፌደራሉ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል የመንግሥት የኃይል እርምጃ እንደሚቀጥል ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው የሚታወስ ቢሆንም፤ የህዝቡ ተቃውሞ ግን ዛሬም በተለያዩ ከተሞች ተጠናክሮ መቀጠሉ ታውቋል፡፡
በተለይ መንግሥት በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ እያደረጉ ባሉ ሰዎች ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃ ከሀገር ውስጥ መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ በመቃወምና በማውገዝ መግለጫ ማውጣታቸው አይዘነጋም፡፡ በተመሳሳይም ቢሮአቸውን በውጭ ያደረጉ እንደ ኦነግ እና አርበኞች ግንቦት ሰባትን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የመንግሥትን ድርጊት አውግዘዋል፡፡