የእኔና አየር መንገዳችን ክርክር – የኢ-ፍትሓዊነት ማሳያ?!

በአቤል ዋበላ

Abel-Wabella

ያኔ ይደብረኝ ነበር፡፡ መሥሪያ ቤቱ ይደብረኛል፡፡ አለቆቼ ይደብሩኛል፤ የሚጠገ’ኑት አውሮጵላኖች ሽታ ይደብረኛል፡፡ አቧራ የጠገቡት የጥገና መሳሪያዎቼ ይደብሩኛል፡፡ ለምን ይህንን ስህተት ሠራሁ እያልኩኝ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ለምን በኮሌጅ የተማርኩትን የመሀንዲስነት ሙያ ትቼ ስለምን የአውሮጵላን ጥገና ሙያ ውስጥ ገባሁኝ እያልኩኝ ራሴን እጠይቃለው፡፡ ከኮሌጅ እንደወጣሁኝ ሥራ የጀመርኩት በቢሾፍቱ ከተማ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ የተወሰኑ ወራት ጫንጮ የሚገኝ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠርቻለው፡፡ ጥግ ጥግ ከመዞር ገላግሎ አዲስ አበባን እንድከትምባት ዕድሉን ያመቻቸልኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ያኔ የትውልድ ከተማዬ ውስጥ፣ አዲስ አበባ መሆን እፈልግ ነበር፡፡ አራት ኪሎ ከቤተ መንግሥቱም፣ ከቤተ ክህነቱም መራቅ አልፈልግም ነበር፡፡ ምክንያቴ ደግሞ የማወቅ የመማር ነበር፡፡ ጫንጮ ብርዳማ ናት፡፡ እንደ አየር ንብረቷ የዐሳብ ገበያዋም ለእኔ ፍላጎት የሚያመረቃ አልነበረም፡፡ በወቅቱ በስስት የምትነበበውን አዲስ ነገር ጋዜጣን ለማግኘት እንኳን ወደ መዲናዋ የሚመላለሱ ሹፌሮችን መለማመጥ ግዴታዬ ነበር፡፡

ህወሓት መራሹ ስርዓት እንዳይሆን-እንዳይሆን ካደረጋቸው ነገሮች አንዱ የሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ የዚህ የተሳከረ ፖሊሲ ግንባር ቀደም ሰለባ ከሆኑት መካከል የቴክኖሎጂ ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡ የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች የተማረ የሰው ኃይል ፍላጎት መጠንና ዓይነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በገፍ ከሚያስመርቁት ተማሪ ጋር ሊጣጣም ባለመቻሉ በቴክኖሎጂ ምሩቃን እና ቀጣሪዎቻቸው መካከል የተዛባ ግንኙነት በግልጽ ይታያል፡፡ ከተማሪዎች መካከል በኮሌጅ በብዙ ትጋት የቀሰሙትን ወደ ንድፈ ሐሳብ የሚያደላ ትምህርት በተግባር የሚያውሉበት ዕድል የሚያገኙት እጅግ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ አብዛኛው ግን የዕለት እንጀራውን ለማብሰል በተገኘው የሥራ መስክ መሰማራት ዕድል ፈንታው ነው፡፡ አንዳንድ ቀጣሪዎች ይህንን ዕድል ተጠቅመው ለሥራ መደቡ ከሚያስፈልገው በላይ የሰለጠነ (overqualified) ምሩቅን በዝቅተኛ ክፍያ ይቀጥራሉ፡፡ ‘ስለአፈር እና ድንጋይ ምንነት አጥንተው በሲቪል ምህንድስና የተመረቁ ልጆች ኮብል ስቶን ለመጥረብ መርቴሎ ጨበጡ’ ተብሎ በከተማው መነጋገሪያ ከመሆኑ በፊት ብዙ ምሩቃን ከሠለጠኑበት የቴክኖሎጂ ዕውቀት እጅግ በጣም ጥቂቱን ብቻ በሚሻ የሥራ መደብ ተሰማርተው ነበር፡፡ ከነዚህ overqualified የሆኑ ምሩቃንን ባልተገባ መልኩ ከሚቀጥሩ ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይገኝበታል፡፡ አየር መንገዱ በርካታ ባለዲግሪዎችን ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ብቻ በሚገኝ ዕውቀት በሚሠሩ የሥራ መደቦች ላይ ቀጥሮ ያሠራ ነበር፡፡ አሁንም ይህ ተቀይሯል ብዬ አልገምትም፡፡
እኔም አዲስ አበባ መሆንን አጥብቄ ፈለግሁኝ፡፡ማስታወቂያ ሲወጣ ጠብቄ አመለከትኩኝ፡፡ አየር መንገዱም ወግ ወጉን ይችልበታል፡፡ የጽሑፍ፣ የቃልና የህክምና የመሳሰሉ ፈተናዎችን አሳልፎ የአውሮጵላን ጥገና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱን እንድቀላቀል ፈቀደልኝ፡፡ በትምህርት ቤቱ የሚሰጠውን የዐሥራ አንድ ወራት ሥልጠና ተከታትዬ አየር መንገዱን ለሰባት ዓመታት እንዳገለግል ይህን ባልፈጽም ግን ከሰባ ሺሕ በጥቂቱ ከፍ የሚል የኢትዮጵያ ብር ለመክፈል ተስማምቼ ፈረምኩኝ፡፡ ሥልጠናው ተጀመረ፡፡ ሁሉም ነገር የዓይን አዋጅ፤ ጽዱው የትምህርት ቤቱ ግቢ፣ የደንብ ልብስ ለብሰው አጀብ ሠርተው የሚጓዙ ተማሪዎች፣ ቆነጃጅቱ እጩ የበረራ አስተናጋጆች . . . ምኑ ይወራል ሁሉም ነገር አዲስ ሆነብኝ፡፡ ስለትምህርት ቤቱና አየር መንገዱ ገለጻ ተደረገልን፡፡ ዎርልድ ክላስ ኩባንያ እንደተቀላቀልን ተደሰኮረልን፡፡ ጀብድ የሚወደው ልቤ የምር ነገር የተገኘ መስሎት ቋመጠ፡፡ ትምህርት/ሥልጠና ተጀመረ፡፡
Deserve
በሥልጠናው የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት የተማርነው አንድ ክብደት ያለውን ነገር ከመሬት ከፍ በማድረግ አየር ላይ ማንቀሳቀስና መቆጣጠር እንዴት እንደሚቻል የሚያስረዳው የኤሮዳይናሚክስ (aerodynamics) ትምህርት ነበር፡፡ በጣም የሚያስደስትና የሰው ልጅን አእምሮ ምጥቀት እንድናደንቅ የሚያስገድድ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ የወሰድናቸው ትምህርቶች ግን የኔን ቀልብ የሚስቡ ሆነው አልተገኙም፡፡ በአብዛኛው ከጥገና ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ዕወቀቶችን የሚያስጨብጡ ተደጋጋሚና ውስብስብነት የሌላቸው ነበሩ፡፡ ይህ ደግሞ አስቸጋሪ የምህንድስና ችግሮችን ከነመፍትሔዎቻቸው ለቃረመ አእምሮ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ከእኔ ጋር አቪየሽን ትምህርት ቤት ከነበሩ ሀያ አምስት ተማሪዎች መካከል ካልተዘነጋኝ ሀያ ሶስቱ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምህንድስና የተመረቁ በመሆናቸው ስለጥገናው ትምህርት ያላቸው ግንዛቤ ከኔ ብዙም የሚርቅ አልነበረም፡፡ ከአንዳንድ እድሜያቸው ከገፋ መምህራን በስተቀር መምህራኑ የኛን ሥነ ልቦና ስለሚረዱ ብዙም አላስጨነቁንም፡፡ እኛም ጥሩ ታዛቢዎች ነበርን፡፡ ዳግም ሥራ ፍለጋ መውጣትን በመስጋት የትምህርት ቤቱ መምህራንና አስተዳደርን ላለማስቆጣት ተጠንቅቄ በምርቃት መርሐ ግብሩ ላይ ባልገኝም ትምህሩቱን አጠናቅቄ በአውሮጵላን ስትራክቸር ጥገና ክፍል ተመድብኩኝ፡፡
ወደሥራ ገበታ ስሄድ በሁለት ጉዳዮች ላይ የራሴን ግምት ወስጄ ነበር፡፡ ከመጀመሪያውና ልክ ከሆነው ግምቴ ልጀምር፡፡ ከልጅነት ጀምሮ መጽሐፍ ከማንበብና ኳስ ከመጫወት በዘለለ የአካልና የአእምሮ ቅልጥፍናን በሚጠይቁ ሥራዎች ደካማ ነበርኩኝ፡፡ እናታችንን በመርዳት የቤት ወስጥ ሥራዎች የሚያከናውኑት ታላላቅ እህቶቼ ነበሩ፡፡ አሁን ሳስበው በሚያሳፍረኝ ሁኔታ ያኔ ግቢያችን የቧንቧ ውሃ በሌለበት ጊዜ ከቦኖ ውሃ በባሊ ሲቀዱ እንኳ አላግዛቸውም ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ የአውሮጵላን ጥገና ባለሙያነት አካላዊ ብቃትና ዲሲፕሊን እንዲኖረኝ ያደርገኛል ብዬ አስብ ነበር፡፡ ይህ ግምቴ ልክ ነበር፡፡ በብዙ መልኩ ተለውጫለው፡፡ በትዕግስት መካኒካል ችግሮችን የመፍታት ክህሎት አዳብሪያለሁ፡፡ ምን አልባት አንድ ባለሙያ የሆነ ሰው አሁን ነገሮች የምሠራበት አኳኋን ላይጥመው ይችላል፡፡ እኔ ግን የነበርኩበትን አውቃለውና በአሁኑ ቅልጥፍናዬ ደስተኛ ነኝ፡፡
ሁለተኛው ግምቴ የሥራው ከባቢ ባለሙያነት የሚበከበርበትና ከስልጠናው ደግሞ የተሻለ ሳቢ ይሆናል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ይህ ግምቴ ፈጽሞ ከእውነታው እጅግ የራቀ ነበር፡፡ በአለቆችና የበታች ሠራተኞች መሐል ያለው ግንኙነት ያለሁት ያ ስመ ገናናው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው ወይስ ሌላ ቦታ ያሰኛል፡፡ ይህን ጤናማ ያልሆነ የሥራ ግንኙነት ተከትሎ ሠራተኛውም በሥራው የሚለግም፣ አለቆቹን ሲያይ ብቻ ሠራተኛ ለመምሰል የሚሞክር ሀሜተኛና ብሶት የሚያበዛ ነው፡፡ አለቆቹም ከበታች ሠራተኛ የተሻለ ስብዕና ስለሌላቸው ጎበዝ ሠራተኛን ሳይሆን ወሬ የሚያቀብልን የሚወዱ፣ በጥቅማጥቅም እየደለሉ የራሳቸውን አንጃ የሚያደራጁ፣ ሰራተኛ የተመቸው ሲመስላቸው የሚከፋቸው፣ ትልቅ የሚመስሉ ነገር ግን የህጻናት ተግባር ሲፈጽሙ የሚገኙ ናቸው፡፡ በእርግጥ ይህ ገለጻ የማይመለከታቸው ጥቂት ደህና ሰዎችን እንዳያሰከፋብኝ እሰጋለሁ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በዚያ ስፍራ ጥሩ ለመሆን ሲሞክሩ ከእኔ በላይ ችግር ገጥሟቸዋል ብዬ ስለማምን መግለጽ የፈለግኹትን ዐሳብ ይርረዱኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡ በዚህ በተበከለ የሥራ ከባቢ ከሠለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ያነሰ ብዙ የአእምሮ ጉልበት የማይጠይቅ ሥራን መከወን ከባድና ስለ አስቸጋሪነቱ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች የሚስማቡበት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ አብዮተኛው ልቤን ምቾት ሊሰጠው አልቻለም፡፡ ይህን ቅሬታዬን በአንድ በዲፓርትመንት ደረጃ በተደረገ ስብሰባ ላይ አነሳኹት፡፡በዚያ ቀን በአለቆቼ ጥርስ ውስጥ ገባሁኝ፡፡ በቅንነት መሥሪያ ቤቱን ሀገራችንን የምናገለግልበት፣ ለብዙ ዓመት በሥራ ላይ ከነበሩ አንጋፋ ሠራተኞች ልምድ የምንቀስምበትና የምንማርበት፣ እኛም የምንጠቀምበት ምቹ ስፍራ እናድርገው ባልኩኝ ጠላት አፈራኹኝ፡፡ ከዚያ እኔም ደበረኝ ከአየር መንገዱም ጋር ሆድና ጀርባ ሆንን፡፡ አየር መንገድ ትቼ የምወጣበትን ቀን መናፈቅ ጀመርኩኝ፡፡
በዚህ በደበረኝ ወቅት ነበር አየር መንገዱ ሥራ ላይ ለሚገኙ ሠራተኞቹ ከዘመኑ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ጋር በየጊዜው እንዲተዋወቁ (Recurrent) ሲል ያዘጋጀውን ሥልጠና እንድወስድ የታዘዝኩት፡፡ አለቆቼ ለእኔ አስበው ሳይሆን የፎርማሊቲ ጉዳይ ሆኖባቸው ይህንን ሥልጠና እንድከታተል ፈቀዱ፡፡ እኔም ከዚያ ከማልወደው የሥራ አከባቢ ገለል ማለትን ፈልጌ ስለነበር በደስታ ወደ ሥልጠናው አመራኹኝ፡፡ በሥልጠናው ከዚህ በፊት እንዳሠለጠኑኝ መምህራን ከዚህ በፊት የማውቀውን ነገር በተሰላቸ መንገድ የሚደግም ሰው አልገጠመኝም፡፡ ሰውየው ዓለም ዐቀፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በሚገባ የተረዳ ነው፡፡ በዚህ ውድድር በበዛበት መድረክ አየር መንገዱ ውጤታማ እንዲሆን እያንዳንዱ ሠራተኛ በተመደበበት የሥራ መደብ ምን እንደሚጠበቅበት በመተንተን ያስረዳል፡፡ የኢንዱስትሪውን ፓለቲካ፣ የተቆጣጣሪ ድርጅቶችን ጸባይ፣ እንደ አይካዎ ያሉ አለም አቀፍ የአቪዬሽን ማኅበራት ፍላጎቶች፣ አየር መንገዱ ያሉበትን ተግዳሮቶች፣ ኢንዱስትሪው በዘመኑ የደረሰበትን ዕውቀት በከፍታ(experts with excellence)የሚያውቁ ሠራተኞች እንዴት ለአየር መንገዱ ጉልበት እንደሚሆኑ ነገር ግን አየር መንገዳችን የነጠረ (refine) ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት እንዳለበት ተጨባጭ በሆነ መልኩ አስረዳን፡፡ ያን ጊዜ ከእንቅልፌ እንደመባነን አልኩኝ፡፡ ተዳፍኖ የነበረውን ሀገሬን በባለሙያነት የማገልገል ስሜቴን ቆሰቆሰው፡፡ ወደቢሮው ሄጄ ላመሰግነው ብቋምጥም አየር መንገዱን ከተቀላቀልኩኝ ጀምሮ ያዳበርኩት የባይተዋርነት ስሜት ቀፍድዶ ያዘኝ፡፡ ለራሴ ግን ያለሁበትን ሁኔታ ለመቀየር ቃል ገባኹኝ፡፡
የምህንድስና ክፍል ክፍት የሥራ ቦታ ሲያወጣ ተወዳድሬ ለማለፍ በቦሌም በባሌም መንገድ ጥረት አደረግኹኝ፡፡ ዕድል ዘግይታም ቢሆን ከእኔ ጋር ሆነች፡፡ አስፈላጊውን ፈተና እና ቃለ መጠይቅ በማለፌ በአየር መንገዱ የአውሮጵላን ጥገና እና ዕድሳት ክፍል የጥገና መሳሪያዎች አስተዳደር እና ምህንድስና ክፍል በመሀንዲስት እንዳገለግል ተመደብኩኝ፡፡ በአጋጣሚ የቅርብ አለቃዬም የሚሠራውን የሚያውቅ፣ ትጉሕና የሚመራው ክፍል የሚጠበቅበትን ሚና በአግባቡ የተረዳ ነበር፡፡በርካታ ሥራዎችን ለመከወን ዕቅድ ያዝን፡፡ እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሮዬ ይናፍቀኝ ጀመር፡፡ ጠዋት ቀድሞ መግባት፣ ማታ ደግሞ አርፍዶ መውጣት እና በእረፍት ቀኔም ወደቢሮ መሄድ ልማዴ ሆነ፡፡ የተወሰኑ ወራት ደስ ብሎኝ ሠራሁ፡፡ አለቃዬም ስገምት በሥራችን ከሞላ ጎደል ደስተኛ የነበረ ይመስለኛል፡፡
በዕለተ ዓርብ ሚያዝያ 17/2006 ዓ.ም. ከ ቀኑ 10፡30 አከባቢ ነው፡፡ የተለመደ ሥራዬን ለማከናወን ኮምፒዩተሬ ላይ አፍጥጫለው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ደኅንነት ከሁለት የማላውቃቸው ሰዎች ጋር ወደቢሮ ገብተው “አቤል ዋበላ . . . አንዴ ውጭ ፈልገንህ ነው” ሲሉ ጠሩኝ፡፡ ሕገ-መንግሥቱን እና ሕገ-መንገሥታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በመሞከር ተጠርጥሬ በፌደራል ፓሊስ ቁጥጥር ስር መዋሌ ነው፡፡ ዞን ዘጠኝ ላይ ከሚጽፉ አምስት ጦማሪዎች እና ሌሎች ሦስት ጋዜጠኞች ጋር በአባሪነት የፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ገባን፡፡ በሂደት ፓሊስ ጥርጣሬውን ወደ ሽብር አሳደገው፡፡ ጭራሽ ይግረማችሁ ብሎ በፌደራል ዐቃቤ ሕግ ታግዞ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ክስ መሠረተ፡፡ ክሱ እንኳን ለዳኞቹ እና ለእኛ ለተከሳሾቹ አይደለም ለራሱ ለዐቃቢ ሕጉም የሚገባ ስላልሆነ በጠበቆቻችን አማካኝነት የክስ መቃወሚያችንን አቀረብን፡፡ ዳኞቹ ፈራ ተባ እያሉ የተወሰነ ነጥቦች ብቻ እንዲያስተካከል አድርገው አሻሽል ያሉት ነጥብ ሳይሻሻል ክሱ እንዲቀጥል ወሰኑ፡፡ እኛም በፀረ-ሽብር አዋጁ አንቀጽ ፫/፪ “የኅብረተሰቡን ወይም የኅብረተሰቡን ክፍል ደኅንነት ወይም ጤና ለከፍተኛ አደጋ” ለማጋለጥ “በመሞከር፣ በማሴር፣ በማነሳሳት” በሚል ተከሰን ፍርዳችንን መጠባበቅ ያዝን፡፡ ከዚያም ዐቃቤ ህግም አስቂኝ የሆነውን የሰውና የሰነድ ማስረጃውን አቀረበ፡፡ ይህ ሂደት አንድ ዓመት ከስድስት ወር ገደማ ፈጅቶ ጥቅምት 05/2008 ዓ.ም. መከላከል ሳያስፈልገን በነጻ ተለቀቅን፡፡
ከፍርድ ቤት በቀጥታ ለአየር መንገዱ የተጻፈ በነጻ መለቀቄን የሚገልጽ ማስረጃ ጥቅምት 10/2008 ዓ.ም. ተቀብዬ ድርጅቱ በነጻ መሰናበቴን ተመልክቶ ወደ ሥራ እንዲመልሰኝ ጥቅምት 15/2008 ዓ.ም. አመለከትኩኝ፡፡ ውሳኔ ላይ አልደረስንም በሚል ሲያመላልሱኝ ከቆዩ በኋላ ሕዳር 16/2007 ዓ.ም. ከዓመት በፊት በኖቨምበር 4/2015(ጥቅምት 25/2007 ዓ.ም.) የተጻፈ ከሥራ መታገዴን የሚገልጽ የስንብት ደብዳቤ ሰጡኝ፡፡ ደብዳቤው የሥራ ውሌ እንዲቋረጥ ምክንያት የሆነው ለስድስት እና ከዚያ በላይ ለተከታታይ ወራት በእስር ምክንያት ከሥራ ገበታዬ መቅረት መሆኑን ጠቅሶ ይህ ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢ.አ.መ. መሠረታዊ የሠራተኞች ማኅበር 10ኛ የኅብረት ስምምነት አባሪ 1 ክፍል አንድ ተ.ቁ 6(111) እና የአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377(2003) አንቀጽ 27(1)(ተ) አንድ ላይ በመሆን የሥራ ቅጥር ውል ወዲያው እንዲቋረጥ ያደርጋል ይላል፡፡
በሕግ ከኅብረት ሥምምነቶች በላይ ተቀባይነት ያለው የአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ አንቀጽ ፳፯ ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ስለማቋረጥ በቁጥር (፩) “በኅብረት ስምምነት ካልተጠቀሰ በሌላ አኳኋን ካልተወሰነ በስተቀር የሥራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጥ የሚቻለው በሚከተሉት ሁኔታዎች ብቻ ነው፡፡” ይልና ከፊደል ተራ ሀ-ቀ ከእስራት ጋር ያልተያያዙ የሥራ ውልን የሚያቋርጡ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ይዘረዝራል፡፡ በፊደል ተራ (በ) ደግሞ “በሠራተኛው ላይ ፴ ቀናት ለሚበልጥ ጊዜ የእስራት ፍርድ ተወስኖበት ከሥራ ሲቀር” ይላል፡፡ እኔ በሕግ አንድም ቀን እንድታሰር ‹የጥፋተኝነት ብይን› ስላልተላለፈብኝ አይመለከተኝም፡፡ በድርጅቱ የተጠቀሰው በፊደል ተራ (ተ) “ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውል ለማቋረጥ ያስችላሉ ተብለው በኅብረት ስምምነት የተወሰኑ ሌሎች ጥፋቶች መፈጸም” የሚለው ነው፡፡ በዚህ መሠረት አዋጁ ሥልጣኑን ለኅብረት ስምምነቱ ስለሚሰጥ ያንን መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡
የኅብረት ስምምነቱ አባሪ 1 ክፍል አንድ “ያለማስጠንቀቂያ ከሥራ የሚያሰናብቱ ከፍተኛ የሥነ-ስርዓት ግድፈቶች/ጥፋቶች እና የሥነ-ስርዓት እርምጃዎች” ይልና ከ ተ.ቁ 1-30 ያሉ ከወሲብ ትንኮሳ አንስቶ በድርጅቱ ቅጽር ግቢ ውስጥ ጠብና አምባጓሮ እስከመጫር የሚደርሱ የጥፋት ዓይነቶችን ይዘረዝራል፡፡እኔን የሚመለከተው 6(111) “ወንጀል ፈጽሞ የ6 ወር እስራት ወይም ከዚያ በላይ እስራት ተፈርዶበት በፍርዱ መሠረት የሚታሰር መሆኑ ሲታወቅ ወይም በማንኛውም ምክንያት ሳይፈረድበት 6 ወር ወይም ከዚያ በላይ ታስሮ የቆየ ” የሚለው ነው፡፡ እዚህ ጋር ነው እንግዲህ ሕገ-መንግሥታዊ መብቴ የተጣሰው፡፡ አዋጁ ለኅብረት ስምምነቱ ሥልጣን ቢሰጥም አሠሪዎች የሠራተኛ ማኅበራትን እየጠመዘዙ የዜጎችን ሕገ-መንግሥታዊ መብት በሚጥስ መልኩ የፈለጉትን ነገር በኅብረት ስምምነት እያሰፈሩ ሠራተኛውን እንዲድበሉ አይፈቅድም፡፡ የኅብረት ስምምነቱ ሕገ-መንግሥቱንና ሌሎች የሀገሪቱን ሕጎች የማይጥስ፣ በመንፈሱ ፍትሓዊ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በሕገ-መንግሥቱ በግልጽ አንድ ሰው በፍርድ ቤት እስካልተወሰነበት ድረስ እንደ ነጻ ሰው እንደሚቆጠር በአንቀጽ 20 ላይ ሰፍሯል፡፡ በመጠ’ርጠሬ ምክንያት ብቻ የሥራ ውሌን ማቋረጥ ሕገ-መንግሥታዊ ታዛዥነትን ያፈረሰ ነው፡፡ ‹በማንኛውም ምክንያት ሳይፈረድበት 6 ወር እና ከዚያ በላይ የቆየ› የሚለው የሀገራችንን የፍርድ ቤቶች ‹ፍትሕን ከሰጡ አዘግይተው የመስጠት› ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው፡፡
ይህንን የመብት ጥሰት ከሕግ ባለሙያው አመሐ መኮንን ጋር ተማክሬ ሕዳር 24/2008 ዓ.ም. በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ደረጃ ፍ/ቤት ቦሌ ምድብ ሥራ ክርክር ችሎት ወደ ሥር እንድመለስ ወይም ድርጅቱ ወደሥራ የምልመለስበት በቂ ምክንያት አለ ሚባል ከሆነ ከሕግ ውጭ ለተቋረጠው የሥራ ውል በሕጉ መሠረት አስፈላጊውን ክፍያ እንዲፈጽም በመጠየቅ ክስ መስርቻለሁ፡፡ ይህን ክሴን ተከትሎ መሥሪያ ቤቱ በደረሰው መጥሪያ መሠረት በታኅሣሥ 22/2008 ዓ.ም. የጽሑፍ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በዚህ መልሱም የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ እንዲሉ ድርጅቱ ስህተቱን ለማረም ዝግጁነት እንደሌለው አሳይቷል፡፡ የሚገርመው በማይመለከተው ጉዳይ ላይ በመግባት የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በእኔ እና ጓደኞቼ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የጠየቀውን ይግባኝ በማንሳት ከሳሽ ገና ለገና ተከሳሽ በድጋሚ ሊታሰር ይችላል በሚል ወደ ሥራ ልመልሰው ልገደድ አይገባኝም ብሏል፡፡ ሰሚት የሚገኘው ፍርድ ቤትም ክርክሩን ለመስማት ለየካቲት 24/2008 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ቀጠሮ ይዟል፡፡

ጉዳዩ በዚህ ቢያበቃ መልካም ነበር፡፡ ድርጅቱ በሕገ-ወጥ መንገድ የሥራ ውሌን አቋርጦ ሳለ ድርጅቱ የሚሰጠውን ሥልጠና ስወስድ ቃል የገባኹት የሰባት ዓመት አገልግሎት በግሌ ያልተወጣኹኝ በማስመሰል ሰባ ሺ የኢትዮጵያ ብር ከነወለዱ እንድከፍለው ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የካ ምድብ ችሎት ክስ መስርቶብኛል፡፡ ይህ የሚያሳየው ድርጅቱ ምን ያህል ኢ-ፍትሓዊነት ቀለባቸው በሆኑ ሰዎች እንደሚመራ ነው፡፡ ከሥራ ለምን ቀረው? በእስራት ምክንያት እስራቱ የማን ስህተት ነው? የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዳረጋገጠው የፖሊስ ሐሰተኛ ክስ ነው:: የሥራ ውሌን ማን አቋረጠው? የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሥራ ገበታ ለምን ቀረህ በማለት በመጨረሻም የገባኸውን ቃል አልፈጸምክም በሚል የከሰሰኝ ራሱ አየር መንገድ ሆኖ አዙሪት ውስጥ ገብቼያለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም የልደታውን፣ የአራዳውን፣ የስድስት ኪሎውን ፍርድ ቤት ነበር የማውቀው አሁን ደግሞ የካ ፍርድ ቤት በታህሳስ 26/2008 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 እንድቀርብ ታዝዣለው፡፡ የምቆመው ብቻዬን ከመሰላቸው ተሳስተዋል፡፡ የምቆመው እንደ አየር መንገዱ ከሕግ በላይ በሆኑ አሠሪዎች በደል ከደረሰባቸው ሠራተኞች ጋር ነው፡፡ የምቆመው ኢ-ፍትሓዊነት በሀገራችን እንዲወገድ ከሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ጋር ነው፡፡ ከዚህ በፊት አየር መንገዱ ብዙ ሠራተኞችን በድሎ በዝምታ እንደታለፈው(የጽሑፉ ዓላማ ይሄ አይደለም እንጂ ስለበደሉ ብዙ ማለት ይቻላል) ከእኔ ዝምታን ቢፈልግ አያገኛትም፡፡ ከእስር እንደወጣኹኝ አንዳንድ ወዳጆቼን ሥራ እንዴት ነው ብዬ ጠይቄ ነበር የብዙዎቹ ምላሽ “ቀንበሩ ከበዷል” የሚል ነው፡፡ ይህንን መሰል ዘመናዊ ባርነቶች እንዲወገዱ ምኞቴ ነው፡፡ እኔ ግን ፍትሕ ባላገኝ እንኳን ለታሪክ ተመዝግቦ እንዲቀመጥ ስል ይህን እናገራለሁ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: