ህወሓት እና የእነ ሓጎስ ፖለቲካ

ተክሌ በቀለ
(የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዘዳንት)

Tekle Bekele

በተቃውሞ እንቅስቃሴዉ ዉስጥ አንድ ያልተፈታ መምታታት ይታያል፡፡ ህዝብንና ድርጅትን መለየት አለመቻል፡፡ አንዳንዴ እንደስልትም ሆን ተብሎ ይሰራበታል፡፡ ግን አክሳሪ ስልት እንደሆነ ትምህርት ሊወሰድ አልተቻለም፡፡ ህወሓት በትግራይ ህዝብ ውስጥ የተፈጠረ ድርጅት ሲሆን ህዝቡ ብዙ ታሪክ እየሰራ ለብዙ ዘመናት እንደኖረ የምንስማማ ይመስለኛል፡፡ ለወደፊቱም ይኖራል፡፡ እነ ሓጎስ ድርጅቱ ውስጥ በአባልነትና በደጋፊነት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በህዝቡ መሃል እየተረገጡም ሊኖሩ ይቻላሉ፡፡ በተቃዋሚው ጎራም ይኖራሉ፡፡ ከሃገር እንዲወጡና እንዳይመለሱ የተደረጉም ይኖራሉ፡፡ ተሰፋ ቆርጠው አንገት ደፍተዉ የተቀመጡም ይኖራሉ፡፡ እነሓጎስ ብዙ ናቸው፡፡ እነ ሓጎስን ከህወሓት ጋር ስንቀላቅላቸው ለደህንነታቸው ይሰጋሉ፡፡ እናም ልዩነታቸውን ረስተው አብረው ይቆማሉ፡፡ በዚህኛው ወገን ያለው ደጋፊም አቅም ያጣል፡፡የወገኖቹን ደህንነት ይፈልጋልና ነው፡፡

የህወሓቶቹን እነ ሃጎስ ያገኘን(ለማሸማቀቅም ይሁን ለማስፈራራት) መስሎን ቀላቅለን ስናያቸው በተቃራኒ ያሉትን ሓጎሶች(ለምሳሌ የዓረና አመራሮችና አባላትን) ሁሉ አቅም እያሳጣናቸዉ ነው፡፡ መሰረታቸውን እያናጋነው ነው፡፡ በህዝባቸው ፊት በህወሓት እንዲቀጠቀጡ ዱላ እያቀበልን ነዉ፡፡ ሲሆን እንሰልጥንና የሁሉም ሓጎሶች ምርጫ ህወሓት ከሆነ ሌሎቻችን እኛን ራሳችንን ነጻ እናውጣና ያገሪቱ ህግ በሚፈቅደዉ መሰረት አብረናቸዉ ለመስራት ዝግጁ እንሁን፡፡ እነሱን ከነሓጎስ ጋር ለማጥፋት ከመስራት እዛው ራሳቸዉን እንዲያስተዳድሩ ራስን ማሳመን ዋጋው ይቀላል፡፡ ሁሉን አቀፍ ድርድር (inclusive negotiation) እኮ አንዱ እፊታችን የሚኖር አማራጭ ይመስለኛል፡፡ ራሳችንን ነጻ ለማዉጣት ከህወሓት ጋር ያሉትን ድጋፍ መጠበቅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ግን እስኪ ሌሎቻችን በወጉ እንስማማ፡፡ መንግሰትን የሚያክል ግዙፍ ተቋም ለመለወጥና አገር ለመምራት የተናጠል አመጽ ብቻውን በቂ አይመስለኝም፡፡ ህዝብን እንወክላለን የሚሉ ቡድኖች ቢስማሙ፤ቅስቀሳና አስተምህሮቶች ሁሉ ባንድነት ቢቆሙ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አመጽ ለመቀስቀስ መስራት አይጠበቅም፡፡ ለዚህ ኢህኣዴግ ራሱ ተግቶ እየሰራ ነው፡፡ የተቃውሞው ጎራ አንድነቱን ጠብቆ አማራጭነቱን ከሳየ ህዝባዊ አመጽ ከሆነ ቦታ በሆነ ምክንያት ተነስቶ ስርዓት እንደሚለውጥ በዓለም ላይ በቂ ተሞክሮ አለ፡፡ እኛ የተለየን አንሆንም፡፡

ሳጠቃልለው፤ እነ ሓጎስን ከህወሓት አለመለየት ለትግሉ መዳከምና ለመከራችን መራዘም አስተዋጽኦ ማበርከት ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በተናጠልም ቢሆን እየተከፈለ ያለውን ውድ መስዋዕትነት ማራከስ ነው፡፡ እነ ሓጎስን በሙሉ ከራሱ ጋር መቀላቀልና የተቀላቀሉ ማስመሰል የሚፈልገዉ ህወሓት ብቻ ነው፡፡ ህዝብና ድርጅት የመለየት ጥበብ ይኑረን፡፡ ልቦናችን ካላሰበው ካፋችን አይጣምና ልቦና ይስጠን፡፡ ተገቢ ቃላትን መጠቀም ለትግሉ ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡ ህወሓትና ወያኔም አንድ አይደሉም! ለዚህም ነው ገዥው ቡድን ህዝባዊ ጥያቄዎችን ሁሉ ረብሻ እያስመሰለ የሚያቀርበውና ህይወት እየበላ እንዲቀጥል እድል እተሰጠው ያለው፡፡ በእውነት ያማል!!!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: