ብስራት ወልደሚካኤል
የዛሬ 42 ዓመት በየካቲት 11 ቀን 1966 ዓ.ም. በቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ዘመን በሊትር የ10 ሳንቲም የነዳጅ ጭማሪን (50 በመቶ ጭማሪን)ተከትሎ የታክሲ ባለንብረቶች እና ሾፌሮች የታሪፍ ማሻሻያ ጭማሪ ቢጠይቁ ተቀባይነት በማጣታቸው የታክሲ አድማ ተደርጎ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ዕለት የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር በጠራው አድማ የሀገሪቱ መምህራን በሙሉ ስራ አቁመው ነበር፡፡ ይህም እየተቀጣጠለ ከአዲስ አበባ ወደ ሌሎች ከተሞች ሳይዳረስ በሚል የወቅቱ መንግሥት የነዳጅ ጭማሪውን መሰረዙን ይፋ አደረገ፡፡
ይሁን እንጂ ተቃውሞው እንደሰደድ እሳት ተቀጣጠለ፤ከዛም መፍትሄ ይሆናል በሚል የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃብተወለድ ልክ የዛሬ 42 ዓመት የካቲት 21 ቀን 1966 ዓ.ም. ከስልጣናቸው እንዲሰናበቱ ተደረ፡፡ ይሄም መፍትሄ አልሆነም፤ይልቅ የመምህራን ማኀበርና የታክሲ የተቃውሞ አድማ ወደ ወታደሩ ዞረ፤ከዛም ንጉሱንም ዘውዳዊ ስርዓቱን ላይመለስ እስከነ አካቴው አሰናበተው፡፡ ልብ በሉ ይህ ሁሉ ልክ የዛሬ 42 ዓመት የነበረ የአዲስ አበባ ታክሲ አድማ ምን እንዳስከተለ፡፡ ይሄ ሁሉ 4ኛ ወሩን ያስቆጠረውና እስካሁንም የቀጠለውን የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ በተጨማሪ መሆኑ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በጎንደርም ተቃውሞዎች እያገረሹ መንገድ እስከመዝጋት እንደደረሱ እየተሰማ ነው፡፡
ዛሬ ከ42 ዓመት በኋላ በዘመነ ኢህአዴግ የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የመንግሥትን አዲስ መመሪያ በመቃወም የተደረገው የታክሲ አድማ በጠዋቱ ጀምሯል፡፡ ይህ እስከተፃፈበት ድረስም የአዲስ አበባው የታክሲ አድማ እንደቀጠለ ነው፡፡ አድማውም ለ ሁለት ተከታታይ ቀናት እንደሚደረገ የታቀደ ቢሆንም፤ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ግን አድማው ሊቀጥል እንደሚችል ነው፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ የአዲስ መመሪያ ዋና ሰለባዎች የታክሲ ሾፌሮች በመሆናቸው ነው፡፡
እስካሁን ባለው አድማም በከተማው የመንግሥት የመስሪያ ቤት የትራንስፖርት አገልግሎት አውቶቡስ፣ የግለሰቦች የጭነት ተሸከርካሪዎች (በግድ ተሳፋሪ እንዲጭኑ እየጠደረጉ) ከሚሰጡት አገልግሎት በስተቀር የተለመዱት የሚኒባስ ታክሲዎች አድማ መትተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ህዝብ ብዛትና ከተጠቃሚው ብዛት እንዲሁም ቀድሞም ከነበረው የትራንስፖርት እጥረት አንፃር የታክሲዎች አድማ የሚያስከትለው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡መንግሥት በስሩ ባሉ መገናኛ ብዙኃን በጠዋት ዜና እወጃው የአዲሱን የአዲስ አበባ ትራንሰፖርት ደንብ መመሪያ ትግበራ ለ3 ወራት ማራዘሙን ቢገልፅም፤የታክሲዎች አድማ ግን ቀኑን ሙሉ ቀጥሎ ውሏል፡፡
ምንም እንኳ ሀገር አቀፍ ምርጫ ከተደረገ 100 ቀናት ቢያልፉትም፤ የዛ “ምርጫ” ኢህአዴግ 100% የህዝብ ድምፅ “በምርጫ” አሸንፊያለው የሚለው መዝሙር ሳያባራ በየአቅጣጫው ጠንከር ያለ ተቃውሞ መምጣቱ ምናልባትም አማራጭ ሐሳብ ያለመኖርና እንዲኖር ያለመፈለጉ ያመጣው መዘዝም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በርግጥ የዛ ተዓምረኛው “ የ100% ምርጫ” ውጤት መዘዝ ገና ብዙ ክስተቶችን በመላው ሀገሪቱ ሊያስተናግድ እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡
የዛሬው የአዲስ አበባ የታክሲ ተቃውሞ አድማ ወደ ሌሎች የግልና መንግሥታዊ ተቋማት አድማሱን አስፍቶ የዛሬ 42 ዓመቱን ታሪክ ይደግመው ይሆን?
በተለይ ከዓለም ገበያና ሀገሪቱ ነዳጅ ከገዛችበት 365 % (ነዳጁ ከተገዛበት ወደ 4 እጥፍ) ክፍያ የተጫነበት ተጠቃሚው ህዝብ ትክክለኛ መረጃ ቢኖረው ከታክሲ አድማው ይልቅ የተሳፋሪው አለመቅደሙ አስገራሚ ቢሆንም፤የዛሬው የታክሲዎች አድማ ሌላም ቁጣ ይቀሰቅስ ይሆን ወይስ እንደተለመደው በማስፈራሪያ አሊያም ደንብ ቁጥር 208/2003 ተከትሎ ወጥቷል የተባለው አዲሱ መመሪያ ተሰርዟል በሚል ወደስራቸው ይመለሱ ይሆን?
ሁሉንም ጊዜ ያሳየናል፡፡