•ሥርዓተ ቀብራቸው በአሰላ ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ተፈጽሟል
•በታኅሣሥ 1966 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቻንስለር ኾነው ተሹመው ነበር
•ከአምስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍት በኋላ ለስድስት ወራት በዐቃቤ መንበርነት አገልግለዋል
* * *
•“በሔዱበት ኹሉ ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታቸውን ይጠብቃሉ፡፡ የሚኖሩት ግን ተዋርደው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት እያሳፈረን ነው፡፡ በእውነት አባትህን ጠይቅ ይነግርሃል፤ ነው፡፡ አፍሪካውያን በሙሉ በቅኝ ግዛት ሲገዙ ኢትዮጵያውያን ለቅኝ ገዥዎች እጃቸውን ያልሰጡት በምን ምክንያት ነው ብለው የዛሬ ክርስቲያኖች በሙሉ ማጥናት አለባቸው፡፡” /ብፁዕ አቡነ ናትናኤል/
* * *
ነገ ቤተ ክርስቲያን ይከፍታልብሎ ያሳደገኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤ የአቅሜን ያኽል ተምሬአለኹ፤ ቤተ ክርስቲያን አሳድጋኛለች፤ ባለውለታዬ ነች፤ ውለታዋን አኹንም አልከፈልኩም፤ እስከሞት ቢኾን ውለታዋን ተሸክሜ ወደ መቃብር ከመግባት በስተቀር ውለታዋን አልከፈልኩም፤ ይኼን የምናገረው ከልቤ ነው፤ ኹሉም ውለታ አለበት፤ የቤተ ክርስቲያኑን ውለታ መመለስ አለበት(ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ ፲፱፻፳፫ – ፳፻፰ ዓ.ም)
“ነቢዩ ኤርሚያስ፥ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን አይለቅም፤ ይላል፤ ይህ ሊጠና ይገባል፡፡ እንባችንን እግዚአብሔር እስኪያብስልን ድረስ እኛ አባቶች ስንጸልይ የምናለቅሰው፥ ለነገዪቱ ኢትዮጵያና ለነገው ትውልድ ነው፤ በተለይ አኹን ያለው ትውልድ ያሳዝነኛል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ መለያየት ምን እንዳስከተለ ተረድቶት ይኾን? ከዚኽ ትውልድ መማር አለበት፡፡ እኛስ ይህን ዓለም እንሰናበተዋለን፤ ጥፋት እንዳይፈጸም፤ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊነቷን ደርዟን እንዳታጣ በእውነት እያለቀስኩ ነው፡፡” – ለሀገርና ለትውልድ በብዙ ከሚጨነቅ ልባዊ ስሜት የመነጨው የዚኽ ረቂቅና ጥልቅ ንግግር ባለቤት፥ ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በላይ የአርሲ ሀገረ ስብከትን በተመሰገነ አባታዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት የመሩት ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ናትናኤል ናቸው፡፡
ብፁዕነታቸው፥“ኢትዮጵያውያን ኹልጊዜ ኢትዮጵያዊ መኾን አለብን፤ የኢትዮጵያን ጠባይ ይዘን መጓዝ አለብን፤” እንዳሉት፣ በሥጋዊ ዝምድና ሳያምኑ፤ “ውለታዋ አለብኝ” ያሏትን ሀገርና ቤተ ክርስቲያን ንቃት በተመላበት ኹለገብነትና በብቃት ለማገልገል እንደጣሩ ተጋድሏቸውን ፈጽመዋል – ብፁዕነታቸው ትላንት፣ የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡30 ገደማ ከዚኽ ዓለም ድካም ዐርፈዋል፡፡
በአሰላ መኖርያ ቤታቸው በቅርብ በሚረዷቸው ወዳጆቻቸው እንደተከበቡ በሰላመ እግዚአብሔር ያረፉት ብፁዕነታቸው፣ ከኩላሊትና ስኳር ሕመም ጋር በተያያዘ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል፤ ከሕመማቸው አገግመው በመልካም ጤንነት ላይ እንደነበሩ የተነገረ ሲኾን፣ ከዕረፍታቸው ሦስትና አራት ቀናት በፊት ምግብ መወሰድ አቁመው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
በፊት ስማቸው ሊቀ ሥልጣናት አባ መዓዛ ቅዱሳን ገብረ ሕይወት የሚባሉት ብፁዕነታቸው፣ በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. ከተሾሙት 13 ኤጴስ ቆጶሳት አንዱ ሲኾኑ ምድብ ሀገረ ስብከታቸውም በቀድሞው አጠራር ትግራይ ክፍለ ሀገር ነበር፡፡ ብፁዕነታቸው፣ ከዐሥር ዓመት በፊት ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አብርሃም ቤት ዓምድ በሰጡት ቃለ ምልልስ፥“በመንግሥት ሥራ የባህል ሚኒስቴር(በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መርሐ ልሳን በሚባለው የቋንቋዎች ጥናት ክፍል) ሲቪል ሰርቫንት ኾኜ እየሠራኹ በመናኙ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመን ለጵጵስና ታጨኹ፡፡ እኔ ጵጵስና ለመሾም ፍላጎቱ አልነበረኝም፡፡ ያኔ የነበረኝ ዓላማ በመጽሐፍ መምህርነቴ ጉባኤ አስፍቼ እንዳስተምር ነበር የምፈልገው፡፡ ምንኵስናን ተቀብዬ እንኳ ለጵጵስና ጉጉቱም ፍላጎቱም አልነበረኝም፤” ብለዋል፤ ለመምህርነት ሞያ ከፍተኛ ፍቅር እንደነበራቸው ሲያስረዱ፡፡
“አንድ ዕድል አገኘኹና ቅድስት ሥላሴ መምህራን ማሠልጠኛ ገባኹ፤” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ በማሠልጠኛው ሳሉ፣ በአባ ሐና ጅማ አቅራቢነትና በቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ፈቃድ በተፈሪ መኰንን ት/ቤት የግብረ ገብ መምህር ኾነው ተቀጥረዋል፡፡ በመምህርነት የመጡ “ኢየሱሳውያን ሚሲዮናውያን” በት/ቤቱ ሥር ሰደው ከጠንካራ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ጋር ግጭት በመፍጠራቸው የተቀጠሩት ብፁዕነታቸው፣ ከ1949 እስከ 1954 ዓ.ም. ድረስ አስተምረዋል፡፡ በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም አንጋፋውን የተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤት ከመሠረቱት አባቶች አንዱ ለመኾን የበቁትም በዚኹ ሥራቸው ላይ ሳሉ ነው፡፡ በወቅቱ ለምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳምም ቋሚ ሰባኬ ወንጌልም ነበሩ፡፡
“የዚያን ጊዜ ገና አልመነኰስኩም፤ ልጅ ነበርኩ፤ ሐዲሳቱንም በቃሌ ስለማውቅ እንደ ብርቅ ድንቅ ኾኜ ነበር የምቆጠረው፤ እውነትም መዓዛ ይሉኝ ነበር፤ መዓዛ የሚለው ስም የወጣልኝ ቅኔ ቤት እያለኹ ነው፡፡ እናቴ ያወጣችልኝ ስም ካሳዬ ነው፡፡ የዚያን ጊዜ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት የዛሬው ስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ነበር፤ የአልጋ ወራሹም ግቢ እዚያው ምስካየ ኅዙናን አጠገብ፣ የልዑል መኰንን ቤትም በአቅራቢያው ነበር፤ ደጀ ጠኚውም በአጠቃላይ የሚመጣው ምስካየ ኅዙናን ነበር፤ ብዙ ሕዝብ ስለሚመጣ ለስብከቱም የተመቸ ነበር::”
አንደበተ ርቱዕና ጥልቅ አሳቢው ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ቤተ ክርስቲያናችን በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ በነበራት ፕሮግራም ያስተምሩ ነበር፤ በሕይወት ዘመናቸው ካከናወኗቸው ተግባራት ለምእመናን በሬዲዮ ስብከተ ወንጌልን በማስተላለፍ የሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ – “ቤተ ክርስቲያናችን በሬዲዮው ለ12 ሰዓት ትምህርት ትሰጥ ነበር፡፡ እኔ በሳምንት አንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እና ማኅበራዊ ኑሮ በቤተ ክርስቲያን በሚል የማስተላልፈው ዝግጅት ነበረኝ፤ ሬዲዮ ጣቢያውን ደርግ እስከወረሰው ድረስ የሰጠኹት አገልግሎት በሕይወቴ የተደሰትኩበት ነው፡፡”
ዛሬ በየአድባራቱ የተስፋፉት ዘመናዊ ት/ቤቶች ትልም፣ በብፁዕነታቸው ሐሳብ አመንጪነት የተቋቋመው የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ት/ቤት ነው፡፡ ሐሳቡን እንዴት እንዳመጡት ሲናገሩ፣ “በወቅቱ በውጭ ሀገር የሚሰጠውን የትምህርት ዘዴና ዘመናዊ ት/ቤትን ከቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ የማቋቋም ብልሃት ቀስሜ ስለመጣኹ የምስካየ ኅዙናን ት/ቤት እንዲቋቋም ሐሳብ አቅርቤ የተምሮ ማስተማር እና የመድኃኔዓለም ጽዋ ማኅበርተኞች እንዲገናኙ አደረግኹ፤” ብለዋል፡፡
በአብነት ትምህርቱ፣ በትውልድ አጥቢያቸው ምሥራቅ ትግራይ ክለተ አውላሎ አውራጃ አውዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር አለቃ መብራህቱ ካስተማሯቸው ፊደል ጀምሮ፤ ወደ ጎንደር/በጌምድር/ ተሻግረው፣ በወሎ/ላስታም እየተዘዋወሩ ድጓውን ጾመ ድጓውን፤ ቅኔውን ከነአገባቡ ልቅም አድርገው ከተለያዩ መምህራን ቀጽለው፣ ወደ አዲስ አበባም ዘልቀው በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም በሐዲስ ኪዳንና በፍትሐ ነገሥት መምህርነት ተመርቀዋል፡፡ ማዕርገ ክህነት የተቀበሉበት ኹኔታም ከትምህርት ዝግጅታቸው ጋር የተጣጣመ ነበር፡፡
“ክህነት የተቀበልኩት ምዕራፍና ጾመ ድጓ ኹለት ጊዜ ዘልቄ፣ ቅኔ ዘይእዜ ከቆጠርኩ በኋላ ነው፤” የሚሉት ብፁዕነታቸው፣ ዲቁና የተቀበሉት በ1938 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ሲኾን እርሱም ከጎንደር አዲስ አበባ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ድረስ በእግራቸው በመምጣት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም፤ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በጾመ ፍልሰታ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ይዘውኝ ሔደው ውዳሴ ማርያም እና ቅዳሴ ማርያም እየተረጎምኩ እዚያው ከርሜ ቅስና፣ ምንኵስና፣ ቁምስና በ1954 ዓ.ም. ከቅዱስነታቸው ተቀብያለኹ፤” ሲሉ ክህነቱን በተገቢው የትምህርት ዝግጅት መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደዚኹም ኹሉ በዘመናዊው ትምህርት ዐሥረኛ ክፍል ሲደርሱ፣ በንጉሡ ጥያቄና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ አስፈጻሚነት ወደ ኢየሩሳሌም አንግሊካን ሴንት ጆርጅ ኮሌጅ ከሌሎች ወንድሞቻቸው ጋር ተልከው ለኹለት ዓመት ተኩል የቤተ ክርስቲያን ታሪክና አስተዳደር ተምረው ዲፕሎማ ይዘው ተመልሰዋል፡፡ ዲፕሎማቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር አቅርበውና አስገምግመው ዕውቅና እንዲሰጣቸውና ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነትም እንዲተላለፍ በማድረጋቸው፣ “ለቤተ ክርስቲያኗ ትምህርት ዋጋ እንዲሰጠው በር ከፍቼ ነበር” ይላሉ፤ ብፁዕነታቸው፡፡
ከዚኽ በኋላ ብፁዕነታቸው፣ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በካህናት አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ ኾነው በ1958 ዓ.ም. ቢሾሙም ወደ ምስካየ ኅዙናን ገዳምም በበጎ ፈቃድ እየተመላለሱ ማስተማራቸውን አላቋረጡም ነበር፤ ይህም ከብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ የስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ጋር ተደማምሮ በ1961 ዓ.ም. በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ወደ እንግሊዝ ኦክስፎርድ ኦስሄትሮፕ ኮሌጅ ለከፍተኛ ትምህርት ተልከዋል፡፡ ትምህርታቸውን ለአራት ዓመታት ተከታትለው በ/Bachelor of Divinity Basic Philosophy Super mental and Developmental Psychology/ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተው ተመልሰዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ አቅራቢነት በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ በታኅሣሥ 1966 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቻንስለር ኾነው እንዲያገለግሉ በወቅቱ የጽሕፈት ሚኒስቴር ተሹመው የነበረ ቢኾንም ከተማሪው እንቅስቃሴና ከአብዮቱ ለውጥ ጋር ተያይዞ “ርእዮተ ዓለሙ አይፈቅድም” በመባሉ ወደ ቤተ ክህነቱ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡
ቀደም ሲል የነበሩት የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት ለውጡን ተከትሎ በመታሰራቸው በቦታቸው የተተኩት ብፁዕነታቸው፣ የሐዋርያዊ ድርጅት ሓላፊና የሰበታ ቤተ ደናግል የበላይ ሓላፊ እንዲኾኑ በጽሕፈት ሚኒስቴር ቢሾሙም የለውጡ ማዕበል በሥራቸው ለመቀጠል አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል – በስብከታቸው፣ “ደርግ አረማዊ ነው ብሏል” በሚል ተከሠው ጉዳያቸው እስከ ጦር ፍ/ቤት ደርሶ ለአንድ ዓመት ከሥራ ውጭ መደረጋቸውን ያስታውሳሉ፤ “በእኔ ላይ በሐሰት የሚመሠክር በመጥፋቱ ተለቀቅኹ፤ እኔ ያስተማርኩት ለሰላም እንጸልይ እያልኩ ነበር፤ ልታሰር የሚገባኝ በሥራ ፈትነቴ እንጂ በትምህርቴ አልነበረም፤” የሚሉት ብፁዕነታቸው፣ በሐዋርያዊ ተልእኮ መፈተን አይቀሬ መኾኑንና ይህም ከሐዋርያት በረከት እንደሚያሳትፍ ይመክራሉ፡፡
ሰው ችግር አይገጥመውም አይባልም፤ ፈተናም አይጠፋም፡፡ ጠንካራ ማርክሲስቶች ነበሩ፡፡ እነርሱም ቤተ ክርስቲያንን ለመጣል ይታገሉ ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን እንዳትወድቅ፤ ሕዝቡም ሃይማኖቱም እንዲጠበቅ ትግል ውስጥ ነበርን፡፡ ይህ ደግሞ ለእኔ ሐዋርያዊ ግዴታዬ ስለነበር እንደ ችግር አላየውም፤ ምክንያቱም ቅዱሳን ሐዋርያት ከደረሰባቸው ጽዋ መካፈል ስለነበረብኝ ነው፡፡
ለቤተ ክርስቲያን የፖሊቲካ ጫወታ እንደማይጠቅማት አሠልሰው የሚናገሩት ብፁዕነታቸው፣ በየጊዜው በመንበሩ የሚቀመጡ አባቶችን ለመቃወም ሲባል በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከፖሊቲካ ጋር ኾኖ የመታገል መንፈስ መቀየር እንዳለበት ያሳስባሉ፡- “አቡነ ቴዎፍሎስ በነበሩበት ወቅት በግል ቅራኔ የነበራቸው ሰዎች እርሳቸውን እንጎዳለን ብለው ቤተ ክርስቲያኗን ይቃወሙ ነበር፡፡ አቡነ መርቆሬዎስም በነበሩበት ወቅት እንዲኹ ይታገሏቸው ነበር፡፡ እንደዚኹ ኹሉ ሕዝቡ በአባቶች ላይ ቅሬታ ኖሮት አባቶችን ሲቃወም በአንድ ላይ አብራ የምትመታው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ስለዚኽ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን መንፈስ መቀየር አለበት፡፡”
ከአባታቸው ከአቶ ገብረ ሕይወት ፀዓዱ ከእናታቸው ከወ/ሮ ወለተ ክርስቶስ ቢሻው በ1923 ዓ.ም. የተወለዱት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ከትውልድ አገራቸው ለትምህርት የወጡት ገና የ13 ዓመት ብላቴና ሳሉ ነበር፡፡ “ኢትዮጵያዊነቴን እንጂ ስለ ትግራይ ብዙ የማውቀው ነገር የለም፤ የትግራይ ጓደኛ አልነበረኝም፤” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ የትምህርት ቤት ሕይወታቸውም ይህንኑ ሀገራዊ ስሜት እንዳጠናከረላቸው ይመሰክራሉ፡- “የትምህርት ቤት ሕይወት ምናኔ ነው፤ የመጣነው ተማሪዎች የተማሪ ቤት ጓደኝነት እንጂ የእርስ በርስ የሥጋ ዝምድና የለንም፤ ኹለቱ ጓደኞቼ ቤጌምድሮች ናቸው፤ አንዱ የላስታ ላሊበላ ልጅ ነው፤ እኔ የተወለድኩት ትግራይ ነው፤ ኹላችንም ከተለያየ ቦታ ብንመጣም እንደ አንድ እናትና አባት ልጆች፣ እንደ ወንድማማቾች ነው የምንተያየው፤ እርስ በርሳችን ልዩ ፍቅር ነበረን፡፡ እንደ ጊዜው ኹኔታ ምግባችንን ሰብስበን አንድ ላይ እንቆርሳለን፤ በአንድነት እንማራለን፡፡ በበሽታ እናስታምማለን፤ ሲድኑ ወደሚያገግሙበት ቦታ እንወስዳለን፤ ሲሞቱ እንቀብራለን፡፡”
ብፁዕነታቸው ዐቃቤ መንበር በነበሩበት ወቅት ከግብጹ ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ ጋር ይታያሉ
ብፁዕነታቸው፣ ኤጲስ ቆጶስነት በተሾሙበት በትግራይ ሀገረ ስብከት ለስድስት ዓመታት በሰጡት ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ መተዳደርያ ይዞታቸውን ተነጥቀው ለነበሩት ጥንታውያን ገዳማት ትኩረት በመስጠት በችግር እንዳይፈቱ ከልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ርዳታ እየተቀበሉ ሥራ ጀምረው ነበር፡፡ “ሶሻሊስት ነን ብላችኋል፤ ማኅበራዊ ኑሮ ያለው በገዳማት ነው፡፡ ገበሬው በነዚያ ቢታቀፍ ይጠቀማልና የገዳማቱን መሬት አትውሰዱባቸው፡፡ ለአካባቢው የልማት ኣርኣያ ይኾናሉ፡፡ እያንዳንዱን ገዳም እንደ አንድ ገበሬ ማኅበር ቁጠሩት፡፡ መሬቱ ለካህናቱ፣ ለመነኰሳቱ ይኹን፤ ሕዝቡን ገንዘብ እንዳይጠይቁት፡፡ ለዘለቄታው ራሳቸውን የሚችሉበት የልማት ሥራ ያስፈልጋቸዋል፤” ብለው ከኮሚሽኑ ስለተቀበሉት ርዳታ አፈጻጸም ከትግራይ ግብርና ቢሮ ጋር ተፈራርመው ሥራ ቢጀምሩም በክፍለ ሀገሩ እየገፋ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ዕቅዶቻቸውን ሳይተግብሩ ቀርተዋል፡፡
“ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መፋጠን ካለኝ ቀናዒነት የተነሣ የማይኾን ነገር ሳይ እናገራለኹ፤ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ኾኖ ዕድሜዬን ለማራዘም ወደ አርሲ ሀገረ ስብከት አመጣኝ፤” ይላሉ፤ በ1975 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ ወደ አርሲ ተዛወረው ስለመመደባቸው ሲናገሩ፡፡ ምደባቸውን በአኰቴት ቢቀበሉትም ችግሩ ግን በሌላ ገጽታው በአርሲም ቆይቷቸው ነበር፤ እንዲኽ ያስረዱታል፡-
“ያኔ ከትግራይ ወደ አርሲ የመጣኹት በእውነት እግዚአብሔር ባወቀ ነው እንጂ በጥናት አልነበረም፤ መመደቤንም በአኰቴት ተቀብዬዋለኹ እንጂ በጣም ችግር ነበር፤ ምክንያቱም ገና የደርግ መዋቅር የሚዘረጋበት ወቅት ነበር፤ የወዛደር ዓለም፤ የአብዮት ምሥረታ የሚባሉ በርካታ እንቅስቃሴዎች የተጀመሩት ባሌ እና አርሲ ላይ ይመስል ነበር፤ እንደ ቀልድ ፕሮፓጋንዳ፥ ሌኒን የተወለደው ጭላሎ ተራራ ላይ ነው፤ ይባል ነበር፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች በአየዳራሹ ይሰበሰቡ ነበር፤ በርእሰ ከተማው አሰላ በነበረ የኅብረት አዳራሽ ለአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እንኳ እንድንሰበሰብ አይፈቀድም ነበር፡፡ በወቅቱ የሰንበት ት/ቤት አባላት ይገረፉ ነበር፤ በዚያን ወቅት ወጣቶች ከፍተኛ ችግር ነበረባቸው፤ ወጣቶቹ እንዳይገረፉ ሰበካ ጉባኤም እንዲቋቋም ከፍተኛ ትግል እናደርግ ነበር፤ የዘመኑ ሰዎች ግን ወጣቱንም እኔንም ያስሩን ነበር፤ እስር ቤት አልገባኹም እንጂ በቁም እስር እስከ ግማሽ ቀን እንዳልንቀሳቀስ ተደርጌአለኹ፡፡ መታወቂያኽ የቀበሌ አይደለም፤ የቤተ ክህነት ነው እያሉ ብዙ እንግልት ደርሶብኛል፡፡
ለዚኽ ዘዴው ጉባኤ ማድረግ ነበር፡፡ ጉባኤ ለማካሔድ ገንዘብ ከልማት ኮሚሽን አገኘን፡፡ የመምሪያ ሓላፊዎችን ሰብስበን አዳራሽ ከማዘጋጃ ቤት ተከራይተን በ1976 ዓ.ም. ጉባኤ አደረግን፡፡ ጉባኤ ማድረጋችን በመላው ሀገሪቱ ተሰማና ሃይማኖት ተፈቀደ፤ ተባለ፡፡ በእግዚአብሔር አጋዥነትም በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ከምእመናን ጋር በመተባበር ለማሳነፅ ችለናል፡፡ አርሲ ተመድቤ ስመጣ የነበሩት 215 አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ነበሩ፤ አኹን ግን(ቃለ ምልልሱ በተካሔደበት በ1998ዓ.ም.) 436 አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ አድርጌአለኹ፤ እኔ ከመጣኹ ከ200 በላይ አዲስ አብያተ ክርስቲያናት ታንፀዋል ማለት ነው፡፡”
ብፁዕነታቸው፣ ከሀገረ ስብከቱ አሰላ ከተማ 60 ኪ.ሜ ርቆ በሚገኘው የዝዋይ ሐይቅ ደሴቶች ላይ በታሪክ የሚዘከር ሥራ ሠርተዋል፡፡ በቀደሙት ብፁዓን አባቶች ተጀምሮ ፍጻሜ ያላገኘውን የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በ1978 ዓ.ም. ተጀምሮ በ1986 ዓ.ም. ሥራው ተጠናቆ በቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ ተመርቋል፤ የተገነባበትን ድንጋይ፣ ከቦታው 68 ኪ.ሜ ርቀት ቁሉልታ ከሚባል ቦታ በማመላለስ እንደተሠራ ብፁዕነታቸው ጠቅሰዋል፤ የአብርሃምንና የአርባእቱ እንስሳ አብያተ ክርስቲያናትንም በበጎ አድራጊ አካላትና ምእመናን ድጋፍ አሠርተዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ በአሰላ ምእመናን ዘንድ በልዩ ኹኔታ የሚታወሱት፣ ከከተማው ወጣ ብሎ የመንግሥት ሹማምንት ቤተ መንግሥት የነበረውን ቦታ ተከራክረው በማስመለስ የቤተ ክርስቲያን ይዞታና ንብረት እንዲኾን ማድረጋቸው ነው፡፡ ቦታውንም፣ ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም እና የሕፃናት ማሳደጊያ ብለው ሰይመው ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆች ሰብስበው አስተምረውበታል፤ መነኰሳትንም በአባታዊ ጥሪ ሰብስበው ማደርያ አሠርተው ሥርዓተ ገዳምን አስፈጽመውበታል፡፡
ቦታውን በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ድጋፍ ከተረከብኩ በኋላ በወቅቱ በነበረው የሃይማኖት ቅራኔ መልሰው ወስደውት ነበር፤ የክፍለ ሀገሩ ኢሠፓ ተጠሪ ስለሺ መንገሻ ወደ ትግራይ ተቀይሮ ሲሔድ አስተዳደሩ እንደገና ተረከብ አለኝ፡፡ በእጅጉ አደከመኝ፡፡ ቦታው ዘረፋ ሲፈጸምበት ስለቆየ ከጥቅም ውጭ ኾኗል፡፡ ባለቤት አጥቶ ደኑ ይወድማል በማለት መንፈሴ ይታወክ ነበር፡፡ ዳግመኛ ከተረከብኩ በኋላ፣ ቤቱን በምን እሠራዋለኹ እያልኩ እጨነቅ ነበር፡፡
ተፈሪ መኰንን ት/ቤት ያስተማርኩት ልጄ የቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወት ልጅ ዶ/ር ዳዊት ዘውዴ ቀይ መስቀል ሓላፊ ኾኖ ይሠራ ስለነበር እርሱን ጠይቄ መንገዱ ጥገና ተደረገለት፡፡ ከዚያ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ጠርቼ ቦታውን እንዲጎበኙ አደረግኹ፡፡ ቅዱስነታቸው ብር 390‚000 ርዳታ ሰጥተውኝ ቦታውን በአዲስ መልክ አሠርቻለኹ፡፡ በውስጡ 120 የሙት ልጆችን አሳድጌበታለኹ፡፡ እኒኽ ልጆች አብዛኛዎቹ ኢንጅነሮች፣ ሜዲካል ዶክተሮች ኾነዋል፡፡ ታላላቅ ባለሞያዎች አድገውበታል፤ አኹንም እያደጉበት ይገኛሉ፡፡
ቦታው የቤተ ክርስቲያን ኾኖ እንዲቀጥል ዘወትር መንፈሴ ይጨነቃል፡፡ ስለዚኽ በጭላሎ ተራራ ሥር የሚኖሩ ሰዎች ከከተማው ርቀው በበሽታ ስለሚሠቃዩ ከአውሮፓ ኅብረት ርዳታ ጠይቄ በጤና ጥበቃ ደረጃ ለልጆቹም ኾነ በገዳሙ ለሚያድጉት ለአካባቢው ኅብረተሰብ የሚያገለግል ጤና ጣቢያ/ክሊኒክ አቋቁሜ ከ25‚000 በላይ ለኾነ ነዋሪ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በርግጥ ክሊኒኩ የመድኃኒት እጥረት አለበት፡፡ ለማሟላት መድኃኒት አምራች ድርጅቶችን እየለመንኩ ነው፡፡
የቦታው የደን ሀብት እና የዱር እንስሳት እንዳይጠፉ ከአውሮፓ ኅብረት ባገኘኹት ርዳታ ዙሪያውን በሽቦ አሳጥሬ የጥበቃ ሠራተኛ ተቀጥሯል፡፡ የጎኑ ስፋት 16 ሜትር የኾነ የዛፎች አባት አለ፡፡ የዛፎቹ ዕድገትና ደኑ ጥብቅ ኾኖ እንዲዘልቅ እንዲኹም የዱር እንስሳቱ ክብካቤ እንደ ጥንቱ አስተማማኝ የሚኾነው ቤተ ክርስቲያን ጠባቂ ስትኾን ነው፡፡ ባለሞያዎች፣ በርሓማነት የተስፋፋው ደኖቻችን ስለተመነጠሩ ነው፤ ይላሉ፡፡ ስለዚኽ የደን ባለአደራ ቤተ ክርስቲያን ስለኾነች ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳምን የተከልኩበት ምክንያቱ፣ ደኑ ሳይመነጠር ቦታው ጠፍ ሳይኾን እንዲዘልቅ በማሰብ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሰጧትን አደራ ጠባቂ ስለኾነች ከእኔ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ትረከባዋለች ብዬ እየደከምኩ ነው፡፡
ብፁዕነታቸው፣ ወላጆቻቸውን በሞት ተነጥቀው አሳዳጊ አልባ ለኾኑ ሕፃናት የመመገቢያና የማደርያ ሕንፃ ካስገነቡ በኋላ በመንፈሳዊ ሕይወት ተኮትኩተው እንዲያድጉ የጻድቁን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አሳንፀዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ለዐሥራ ኹለት መናኞች የሚኾን ቤትም አሠርተዋል፡፡ ለቤተ ክርስቲያኑ መንቀሳቀሳሻ ከራሳቸው ብር 50 ሺሕ እና ከበጎ አድራጊ ምእመን ተውጣጥቶም እየተገለገለ ነው፡፡ “ዘይመጽእ እም ድኅሬየ ያጸንዕ እምኔዬ” እንደተባለ፣ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ሰው ድካሜን አይቶ ከዚኽም አስፍቶ እንደሚሠራው እምነት አለኝ፤ ይላሉ ብፁዕነታቸው፡፡
በበቆጂ የደብረ ቁስቋም የሴቶች አንድነት ገዳምን የመሠረቱት ብፁዕነታቸው፣ የሴት መነኰሳዪያት ት/ቤት ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንዳሉም በቃለ ምልልሱ ወቅት ጠቁመው ነበር፡፡ “ት/ቤቱን ልከፍት ያሰብኩት ቀድሞ በሰበታ ቤተ ደናግል የቦርድ አባልና የገዳሙ ሓላፊ ኾኜ በመሥራቴ ብዙ ልምድ ስላገኘኹ ነው፤” ሲሉ መነሻቸውን አውስተዋል፡፡ በበቆጂ ከሚገኙ እናቶች መካከል ወደ ሰበታ ቤተ ደናግል እየተላኩ ሠልጥነዋል፡፡
ከከተማው ወጣ ብሎ እንደ ሸንኮራ ዮሐንስ ያለ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የጠበል ቦታ ከልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በተገኘ 48 ሺሕ ያኽል ብር በጥሩ ኹኔታ አሠርተዋል፡፡ ለምእመናኑንም የመጠጥ ውኃ፣ ለከብቶቻቸው ገንዳና ሌሎችም የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያንም አሳንፀዋል፡፡ ሁሩታ ላይ ለፋብሪካ የሚኾን ቦታ ተገዝቶ ከደብር ቅዱስ የሚወጡ አዳጊዎች በሠርቶ ማሳያ እንዲሠማሩበት ለማድረግ ያላቸውንም ዕቅድ በወቅቱ ገልጸው ነበር፡፡
በሀገረ ስብከቱ ኮፈሌ ወረዳ ልዩ ስሙ አንሻ በሚባል ቦታ፣ ኢአማንያን ለምእመኑ ብቸኛ የኾነችውን የቅድስት ማርያምን ቤተ ክርስቲያን ባቃጠሉበት ወቅት ብፁዕነታቸው ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ምእመኑን አጽናንተዋል፤ ጥቃት አድራሾቹ በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱም በሕዝቡ ትብብር ዳግመኛ እንድትታነፅ አድርገዋል፡፡
የውስጥ ችግሮችን በሰላም በመፍታት የውጭ ተግዳሮትን ለመመከት፣ በተለይ ኦርቶዶክሳዊው ወጣት መለያየትን አቁሞና ልብ ገዝቶ አንድነቱንና ትብብሩን ማጥበቅ እንደሚኖርበት ብፁዕነታቸው ያሳስባሉ፤ “በእውነት፥ ጸሎት፣ ምሕላ፣ ትምህርት የሚያስፈልገው ነው፤” ያሉትን ጥልቅና ረቂቅ ምክራቸውንም እንደሚከተለው አስተላልፈው ነበር፡-
እርስ በርሷ የተለያየች መንግሥት ትፈርሳለች፤ አትጸናም፡፡ እርስ በእርሷ የተለያየች አገር ትፈርሳለች፤ አትጸናም፡፡ “የሰይጣን መንግሥቱ ተለያየ፤” ሲል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል፡፡ እንኳን አንድ አገር ሕዝብና መንግሥት ቀርቶ የሰይጣን መንግሥት እንደሚፈርስ መረዳት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎሳ የለውም፤ ሴሜቲክ፣ ነገደ ካም እና ነገደ ኩሽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ግዛቷ እስከ ሱዳን ነበር፡፡ ሲናር፣ ከሰላ፣ መቋድሽ(መቅደሶ ማርያም)፣ ማዳጋስካር ደሴት፣ ሕንድ ውቅያኖስ ጠረፏ ወሰኗ፤ ቀይ ባሕር ወሰኗ እንደነበር ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ መለያየትና መከፋፈል ምን እንዳስከተለ ተረድቶት ይኾን? ከዚኽ ትውልዱ መማር አለበት፡፡ እኛስ እናዝናለን፤ ይህን ዓለም እንሰናበተዋለን፤ ነገር ግን ጥፋት እንዳይፈጸም፣ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊነት ደርዟን እንዳታጣ በእውነት እያለቀስኩ ነው፡፡ ያለነው ጥቂት አባቶች ለማስተማር ብንወተረተርም ትውልዱ አይረዳም፤ ከወላጆቹ መማር የሚገባው ወጣት እንደ አባቶቹና እናቶቹ አይደለም፡፡ ወደ አውሮፓ፣ ወደ አሜሪካ፣ ወደ ዓረብ አገር ብንሔድ ኢትዮጵያዊ የሚኖረው አምሮበት አይደለም፡፡ ተዋርዶ፣ ተሳቅቆ፣ ሮጦ ነው ያለው፡፡ በሔዱበት ኹሉ ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታቸውን ይጠብቃሉ፡፡ የሚኖሩት ግን ተዋርደው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት እያሳፈረን ነው፡፡
በእውነት አባትኽን ጠይቅ፣ ይነግርሃል ነው፡፡ አፍሪካውያን በሙሉ በቅኝ ሲገዙ ኢትዮጵያውያን ለቅኝ ገዥዎች እጃቸውን ያልሰጡት በምን ምክንያት ነው? ብለው የዛሬ ክርስቲያኖች ማጥናት አለባቸው፡፡ ጣልያን ቢመጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ኾኖ ዐድዋ ላይ ድል ሲቀዳጅ የተደሰቱት ኢትዮጵያውያንና አፍሪካውያን ብቻ ሳይኾኑ የጥቁር ሕዝብ በሙሉ ተደስቷል፡፡ ለካስ ነጭ በጥቁር ይሸነፋል፤ ብለው ነፃነታቸውን ለመጠየቅ የተነሡት ከዐድዋ ድል በኋላ ከኢትዮጵያውያን አንፀባራቂ ድል ተነሥተው ነው፡፡ ወጣቱ የአባቶቹ ወኔ ሊኖረው ይገባል፡፡
ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት ነው? ወይን ወይንነቱ ጠማማነቱ ነው፡፡ ወይን በቀጥታ ለሞፈርና ለቀንበር አይኾንም፡፡ ወይን ደግነቱ ፍሬው ነው፤ ዕንጨቱ ግን ጠማማ ነው፡፡ ነብር ተፈጥሮው ግራጫ፣ ዝንጉርጉር ነው፤ ኢትዮጵያዊ ደግሞ ጀግና ነው፡፡ ነቢዩ ኤርሚያስ፣ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን አይለቅም፤ ይላል፡፡ ይህ ሊጠና ይገባል፡፡
እንባችንን እግዚአብሔር እስኪያብስልን ድረስ እኛ አባቶች ስንጸልይ የምናለቅሰው ለነገዪቱ ኢትዮጵያና ለነገው ትውልድ ነው፡፡ በተለይ አኹን ያለው ኹኔታ በጣም ያሳዝነኛል፡፡
ብፁዕነታቸው በመጨረሻም፤ ከ33 ዓመታት በፊት ከትግራይ ሀገረ ስብከት ወደ አርሲ ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ ሲዛወሩ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ያሏቸውን ለትውስታ በመጥቀስ ምክራቸውንና መልእክታቸውን ያጠቃልላሉ፡-
ከትግራይ ወደ አርሲ የተዛወርኩ ጊዜ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፥ አባታችን አልኋቸው፤ ከእግዚአብሔር አግኝተው አድርገውት ከኾነ እግዚአብሔርም እኔም ደስ ይለናል፡፡ ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠርቼ አስደስትዎታለኹ፡፡ ከሰው አግኝተውት ከኾነ እኔና እግዚአብሔር ደስ ይለናል፡፡ የአቅሜን ያኽል ደስ የሚያሰኝ ሥራ እሠራለኹ፤ ብያቸው ነበር፡፡ የአቅሜን ያኽል ተምሬአለኹ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሳድጋኛለች፡፡ ባለውለታዬ ነች፡፡ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን ውለታ አልከፈልኩም፡፡
ተማሪ ሳለኹ በእንተ ስማ ለማርያም፣ ስለ ቸሩ እግዚአብሔር እያልኩ ስማር አቅመ ደካማ፣ አካል ጉዳተኛ ኾኜ አይደለም፡፡ ነገ ቤተ ክርስቲያን ይከፍታል ብሎ ያሳደገኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ከቆሎ ት/ቤት ጎጆ ቤት ወጥቼ አዳሪ ት/ቤት ገብቼ ከዚያም ብዙ የትምህርት ዕድል ያገኘኹት፤ ከአንድም ኹለት ጊዜ ወደ ውጭ ልካ ያስተማረችኝ ለእኔ ሳይኾን ለቤተ ክርስቲያን ውለታ ነው፡፡
ኹሉም ውለታ አለበት፤ የቤተ ክርስቲያኑን ውለታ መመለስ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ውለታ አኹን አልከፈልኋትም፤ እስከ ሞት ቢኾን ውለታዋን ተሸክሜ ወደ መቃብር ከመግባት በስተቀር ውለታ አልከፈልኩም፡፡ ይህን የምናገረው ከልቤ ነው፡፡
እያንዳንዳችን ውለታችንን ለአገር፣ ለቤተ ክርስቲያን መክፈል አለብን፡፡ ኢትዮጵያውያን ኹልጊዜ ኢትዮጵያዊ መኾን አለብን፡፡ የኢትዮጵያንን ጠባይ ይዘን መጓዝ አለብን፡፡ በ1977 ዓ.ም. በረኀብ በተቀጣን ጊዜ ስሙን የማላስታውሰው የምዕራቡ ዓለም መሪ፣ ያ ኩሩ ሕዝብ፤ አገሩንና ሃይማኖቱን ያላስደፈረ ሕዝብ ነው፤ ያለው ቃል ከኅሊናዬ ዘወትር አይጠፋም፡፡ ከዚኽ ውጪ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅማት የፖሊቲካ ጫወታ አይደለም፡፡
* * *
ብፁዕነታቸው፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እንዳሏቸው፣ ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ ተዛውረው በተመደቡበት አርሲ ሀገረ ስብከት ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በላይ በብዙ የደከሙበትን ሐዋርያዊ አገልግሎት እግዚአብሔርንም ሰውንም ደስ በሚያሰኝ አኳኋን ፈጽመው በተወለዱ በ85 ዓመት ዕድሜአቸው ዐርፈዋል፤ ሥርዓተ ቀብራቸውም፤ አሳድገው ለቁምነገር ባበቁአቸው ልጆች የቀጣዩን ትውልድ ተስፋና የጥረታቸውን ፍሬ ባዩበት በደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም፣ ሐሙስ፣ የካቲት 24 ቀን ብፁዓን አባቶች፣ ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡
የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ይድረሰን፡፡ አሜን፡፡
ምንጭ፡- ሐራ ዘተዋሕዶ፣ https://haratewahido.wordpress.com/2016/03/01