በደቡብ ክልላዊ መንግሥት ከዚህ ቀደም ኮንሶ ራሱን ችሎ ልዩ ወረዳ በነበረበት ወቅት የዞን አስተዳደር ደረጃ እውቅና እንዲሰጠው ህዝቡ ቢጠይቅም፤ ከነበረበት ልዩ ወረዳ አንሶ በአዲሱ የሰገን ህዝቦች ዞን በሚል አስተዳደር ወደ ወረዳነት መውረዱን በመቃወም ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ከክልሉም ሆነ ከፌደራል መንግሥት ምላሽ ሳያገኙ ቅተዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ህዝቡ የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በኮንሶ ዋና ከተማ ካራት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል፡፡
በተቃውሞ ሰልፉ የደቡብ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይልና መከላከያ ሰራዊት በወሰዱት የኃይል እርምጃ 23 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ ህዝቡም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱትን የኃይል እርምጃ በመቃወም ዋና ከተማቸውን አቋርጦ የሚያልፈውን ከአርባ ምንጭ ጂንካ የሚወስደውን ዋና መንገድ ሙሉ ለሙሉ ዘግተው እንደነበርም ታውቋል፡፡
መንግሥት ተቃውሞን ለማስቆምና የተዘጋውን መንገድ ለማስከፈት በሚል በድጋሚ በወሰደው የኃይል እርምጃ ከዋና ከተማ ካራት በተጨማሪ በአጎራባች የገጠር ቀበሌዎች ጭምር በመዝለቅ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ የተገለፀ ሲሆን፤ በዚህም የደቤና ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሷይታ ጋራ የተባሉ ግለሰብ ወዲያው ህይወታቸው እንዳለፈና የ65 ዓመት አዛውነትንና ወጣት ተስፋዬ ማሙሽን ጨምሮ 23 ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ እስካሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ሰዎችም በከተማው ፖሊስ ጣቢያ እና በካራት ቴክኒክና ሙ ማሰልጠኛ ተቋም መታሰራቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
በመጨረሻም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተዘጋውን መንገድ በኃይል ማስከፈታቸውን የተገለፀ ሲሆን፤ ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በርካታ የክልሉ ልዩ የፖሊስ ኃይል እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአካባቢው ሰገን ወንዝ ሰፍረው እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ በተለይ በዋና ከተማዋ ካራት የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ የነበሩ ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ በከተማዋና አካባቢ የሰፈረው የመንግሥት የፀጥታ ኃይል በበቀል የህዝብ ንብረት ላይም ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ይህ እስከተዘገበበት ድረስም በአካባቢው የተለመደው የትራንሶፕርተና ማኀበራዊ አገልግሎት ከመስተጓገሉ በተጨማሪ አለመረጋጋቶች እንደሚስተዋሉ ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ በአካባቢው የነበረውን አለመረጋጋትና ተቃሞ በተመለከተ ከመንግሥት አካል የተገለፀ ነገር የለም፡፡