ቀኑ በትክክል ባይታወቅም ባለፈው ሳምንት የተከናወነ እንደሆነ የሚታመነውና በፖሊስ ቁጥጥር ስር ባልተገባ አያያዝ እርቃናቸውን ይታዩ የነበሩ በደቡብ ክልል በቤንች ማጂ ዞን የሚገኙ እና የደቡብ ኦሞ ዞን አጎራባች የሆኑት የሙርሲ ማኀበረሰብ በአካባቢው በመንግሥት ለማከናወን የታቀደውን የኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት ማስፋፊያ ባደረሰባቸው ተፅዕኖ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ የተሰጠ የመንግሥት ምላሽ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
በተለይ በክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበሩት የሙርሲ ማኀበረሰብ አባላት ኢሰብዓዊ በሆነና ለህይወታቸው በሚያሰጋ መልኩ እር በርስ በመጠላለፍ የታሰሩበት ሁኔታ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ ይንንም በተመለከተ የስርዓቱ ደጋፊዎች ምስሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈፀመ ሳይሆን ደቡብ ሱዳን በሚል ለማስተባበል ከመሞከራቸው በስተቀር ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በቁጥጥር ስር የነበሩት የሙርሲ ማኀበረሰብ እርቃናቸውን እር በርስ በአሰቃቂ ሁኔታ ካሰሯቸው መካከል የሁለቱ ፖሊስ አባላት ማንነት ከነ ምስላቸው በሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውን መለየት መቻላቸው ተጠቁሟል፡፡
ከታሰሩት ጋር ይታዩ ከነበሩት ፖሊሶች መካከል ሁለቱ ማንነታቸው የተለየ ሲሆን፤ እነሱም ኮንስታብል ደመቀ አራርሳ ወጊ የሚባል የወለንጪቲ ተወላጅ ሲሆን፤ ረዳት ኮንስታብል የኑስ ተማም ቦሬ የሚባል የዲላ ተወላጅ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ በቁጥጥር ስር የነበሩ አካላትን ጭኖ የነበረው ተሽከርካሪ ንብረትነቱ እና ፖሊሶቹ ለብሰውት የነበረው የደንብ ልብስ የደቡብ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይል እንደነበርም መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ይሁን እንጂ፤ የፖሊስን ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ በተመለከተ የረህ እስከተዘገበበት ድረስ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ የለም፡፡
በአካባቢው ከዚህ በፊት መንግሥት ያለምንም በቂ ማኀበራዊና አካባቢዊ ተፅዕኖ ግምገማ እናያለ በቂ ካሳ ከ200 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ማፈናቀሉ ከፍተኛ ትችት አስከትሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡