ከህዳር አጋማሽ 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ተጀምሮ በነበረው እና መላው ኦሮሚያ ክልልን ያዳረሰው ህዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ የደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት ልዩ የምርመራ ሪፖርት መግለጫ ይፋ ሆነ፡፡ ልዩ መግለጫው ይፋ የሆነው መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው የሰመጉ ዋና ጽህፈት ቤት ሲሆን፤ መግለጫውም የ103 ዜጎች ህይወት መጥፋቱን አስታውቋል፡፡
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ይባል የነበረውና በኋላም የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ(ሰመጉ) እየተባለ የሚጠራው ብቸኛው ሀገር በቀል መነግሥታዊ ያልሆነ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሲሆን፤ ባለፉት አራት ወራት በተጀመረውና እስካሁንም በቀጠለው የኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ የሰብዓዊ ጉዳት ቀዳሚውን ልዩ መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡ ሰመጉ በ140ኛው የተቋሙ ሪፖርት “የኦሮሚያ ክልል በ18 ዞኖች እና በ342 ወረዳዎች የተከፋፈለ ሲሆን ሰመጉ ከ9 ዞኖች ውስጥ በ33 ወረዳዎች ብቻ ባደረገው የመስክ ምርመራ ባገኘው ውጤት መሰረት 103 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 57 ሰዎች በጥይት የመቁሰል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡” ብሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተገደሉትና ከቆሰሉት በተጨማሪ በ22 ሰዎች ላይ ማሰቃየት እና ድብደባ መፈፀሙን፣ 84 ሰዎች መታሰራቸውን እንዲሁም 12 ሰዎች የደረሱበት ወይም ያሉበት አለመታወቁንም ጠቁሟል፡፡
ሰመጉ 34 ገፅ ባለው ልዩ መግለጫው እንዳስታወቀው ከሆነ፤ የደረሰው የሰብዓዊ ጉዳት ምርመራ የሚያካትተው ከህዳር 2 ቀን እስከ የካቲት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. የደረሱ የሰብዓዊ ጉዳቶች ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በተለይ በምርመራ ወቅት ድርጅቱ የጋጠሙትን ችግሮችም የጠቀሰ ሲሆን በተለይም የገንዘብ ፣ የሰው ኃይልና የምርመራ መሳሪያ እጥረት፣ በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ውጥረት የተሞላበት በመሆኑ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ቀውስ እንደልብ ተዘዋውሮ ለመስራት አለመቻል፣የመንግሥት የደህንነት እና የፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ጫና እና ክትትል ማድረጋቸው፣ ሕዝቡ ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ በመግባት ማንንም ሰው አለማመን እና መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን ዋነኞቹ መሆናቸው ጠቅሷል፡፡
በክልሉ አሁንም በተለያዩ ቦታዎች ተቃውሞች መቀጠላቸውንም በመጥቀስ፣ ማንኛውም የሰብዓዊ መብት የሚመለከተው አካል የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት እንዲያከብር፣ እንዲያስከብርና እንዲያስጠበቅ ጫና እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡
ሙሉ መግለጫውን ከዚህ ቀጥሎ ያለውን መስፈንጠሪያ (ሊንክ) በመጠቀም ያገኙታል፡- http://ehrco.org/wp-content/uploads/2016/03/The-Human-Rights-Council-HRCO-140th-Special-Report-Amharic-Scanned-March-14-2016.pdf