(አዲስ ሚዲያ)ትናንት አርብ ሚያዚያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት ጀምሮ ከሰዓት በኋላም የቀጠለው በሺህዎች የሚቆጠሩና የታጠቁ ደቡብ ሱዳን ቡማ ግዛት ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ የሙርሌ ማኀበረሰብ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት በጋምቤላ የሚገኙ ህፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 170 ኢትዮጵያውያን የኑዌር ማኀበረሰብ አባላትን መግደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ዋቢ በማድረግ ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡
ታጣቂዎቹ በብዛት የኔዌር ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት በጋምቤላ ክልል ዞን 3 ጂካው እና ኒኔኛንግ ወረዳ የካጃክ አስር የኑዌር መንደር በመሄድ ጥቃት ማድረሳቸው የተገለፀ ሲሆን፤ በተለይ የግድያ ሰለባው የሆኑት በዋናነት ህፃናት እና ሴቶች መሆናቸውንም ከጥቃቱ የተረፉ እማኞች ተናግረዋል፡፡ በጥቃቱም በርካታ ዜጎች መቆሰላቸውና እስካሁን ቁጥራቸው ያልተገለፀ በርካታ ህፃናትም ታግተው መወሰዳቸው ተጠቁሟል፡፡
እንደእማኞች ገለፃ ከሆነ፤ በጥቃቱ ወቅት በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ለጋምቤላ ክልላዊ መንግሥትና በአካባቢው በቅርብ ርቀት ለሚገኙ የፌደራል መንግሥት ፌደራል ፖሊስና መከላከያ የድረሱልን ጥሪ ቢያደርጉም ምላሽ እንዳላገኙ እና ጠዋት የጀመረው ጥቃትም እስከ ከሰዓት ድረስ መዝለቁን ያልተለመደ እንደነበርና በወቅቱ መንግሥት ምላሽ ባለመስጠቱም የብዙ ሰዎች ህይወት መጥፋቱም እንዳሳዘናቸው በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡
“በእጃችን ራሳችንን የምንከላከልበት እንኳ በቂ መሳሪያ ባለመኖሩና የመንግሥትን ምላሽ በማጣታችን ለአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች የድረሱልን ጥሪ በማሰማታችንና ትብብር ስላደረጉልን ታጣቂዎቹ እያደረሱ ያሉትን አደጋ ለመቀነስ ችለናል:: በዚህም ከደቡብ ሱዳን ታጣቂዎችም ከ51 ያላነሱ ሰዎችን ገድለናል፣ የተወሰኑ የተዘረፉ ከብቶቻችንን አስመልሰናል፤ ነገር ግን የታገቱ ህፃናት ልጆቻችንን እና የተዘረፉ ከብቶቻችንን ማስመለስ አልቻልንም “ ብለዋ፤ሌላኛው በህይወት የተረፉ አንድ አባት፡፡
ስማቸውን እንዲገለፅ ያልፈለጉና ከጥቃቱ የተረፉ ግለሰብ እንደተናገሩት ከሆነ፤ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ሰርገው በመግባት ጥቃት ያደርሱ እንደነበር ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፤ የትናንትናው ግን በወታደራዊ የደንብ ልብስ በብዛት ታጥቀው ገብተው የዚህ ዓይነት የከፋ ጉዳት ሲያደርሱ የመጀመሪያቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በትናንትናው ግድያም 170 ኢትዮጵያውያን እና 51 የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎችን ጨምሮ ወደ 221 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡
በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግሥት በበኩሉ በስሩ ባሉ ፋናቢሲ እና ኢቢሲ በመሳሰሉ መገናኛ ብዙኃን እንዳስታወቀው ከሆነ፤ በጋምቤላ ከደቡብ ሱዳን መንግሥትም ሆነ ከመንግሥት ተቃዋሚ ታጣቂዎች ምንም ንክኪ የሌላቸው “ወንበዴዎች” 140 ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን እና ከጥቃት አድራሽ ደቡብ ሱዳናውያን ደግሞ 60 ያህል ሰዎች መገደላቸውን ቢያስታውቅም፤ ይህ እስከተዘገበበት ድረስ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃም ሆነ የሰጠው መግለጫ የለም፡፡
ታጣቂዎቹ ከደቡብ ሱዳን ድረስ ድንበር ጥሰው በመግባት ለምን ኢትዮጵያውያንን እንገደሉ፣ ህፃናቱን እንዳገቱና ከብቶቻቸውን እንደዘረፉ የተገለፀ ነገር የለም፡፡
በያዝነው 2008 ዓ.ም. ባለፉት ወራት በተለያየ ጊዜ በዚሁ በጋምቤላ ክልል የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ በርካታ ዜጎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የትናንቱ ግድያ የጠፈፀመው ግን ከደቡብ ሱዳን በመጡ ታጣቂዎች እንደነበርና ይህንንም ከተገደሉ ሰዎች ማረጋገጥ እንደተቻለ ተጠቁሟል፡፡