የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና በምርጫ 2007 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ወረዳ 17 የፓርላማ እጩ ተወዳዳሪ የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 የወጣውን አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን ተላልፏል በሚል ክስ ተመስርቶበታል፡፡
ሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ክሱ በዳኞች ቢሮ በንባብ የተሰማበት አቶ ዮናታን ተስፋዬ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሽፋን በማድረግ ከህዳር 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተከሳሹ በሚጠቀምበት ድረ-ገፅ በተለይም ፌስቡክ አማካኝነት በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን “አመፅና ብጥብጥ” ለማስቀጠል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ን ዓላማ ተቀብሎ ተንቀሳቅሷል ሲል አቃቤ ህግ ክስ መስርቶበታል፡፡ የክስ ፋይሉ ሌላ ተከሳሽ ውጭ ለአቶ ዮናታን ብቻ የቀረበበት የማስረጃ ዝርዝር በማኀበራዊ ሚዲያ የለጠፋቸው ፅሑፎች ናቸው፡፡
በዚህም ተከሳሹ የቡድን (ኦነግ) ዓላማን ለማሳካት አመፅና ብጥብጥ እንዲቀጥልና ሌሎችን ለማነሳሳት አስቦ በሚጠቀምበት ድረ-ገፅ (ፌስቡክ) ቀስቃሽ ፅሑፎችን በመፃፍ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈፀም ማቀድ፣ ማዘጋጀት፣ ማሴር እና ማነሳሳት ወንጀል ክስ በአቃቤ ህግ እንደቀረበበት ታውቋል፡፡
አቶ ዮናታን ተስፋዬ በተለያዩ ቀናት በግል የፌስቡክ ገጹ ላይ ያስነበባቸው ፅሑፎች ክሱ ላይ ተካተው በማስረጃነት ቀርቦበታል፡፡
ታህሣሥ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ለጭቆና መሳሪያነት የሚያገለግሉ ማናቸውንም ቁሳቁሶች ማቃጠልና ማውደም እንዲሁም መንገድ መዝጋትን በተመለከተ፣ ታህሣሥ 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ኢህአዴግ ችግር ማዳፈን እንጂ ችግር መፍታት አይችልም በሚል የፃፈው፣ ታህሣሥ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲጀመር ምንም ዓይነት መሪ ዕቅድ (ማስተር ፕላን) የለም በሚል የፃፈው፣ ታህሣሥ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. የተቃውሞ ትግሉ ቀጥሏል በሚል የፃፈው፣ ህዳር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. እነሆ 7 መልዕክት ብሎ በፃፈው እና በሌሎችም ፅሑፎች አማካኝነት ቅስቀሳ አድርጓል ሲል አቃቤ ህግ ክስ አቅርቦበታል፡፡
ዮናታን ተስፋዬ በነጠላ መዝገብ ብቻውን ክስ የተመሰረተበት ሲሆን፤ በዕለቱ ክሱ በንባብ በተሰማበት ወቅት ዳኛ አልተሟላም በሚል ምክንያት በዳኞች ቢሮ መታየቱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የክሱን ሂደት ዬናታን ቤተሰቦችም፣ ወዳጆችና ጋዜጠኞች በችሎት መታደም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ አቶ ዮናታንም የክስ መቃወሚያውን ይዞ ለፊታችን ግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲቀርብ ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡
ምንጭ፡- EHRP.