በቦሌ ወረገኑ በሕገወጥ ግንባታ ምክንያት ነዋሪዎችና የፀጥታ ኃይሎች ተጋጭተው ጉዳት ደረሰ

ታምሩ ጽጌ

‹‹መንግሥት ያለምንም ርህራሔ በክረምት ጐዳና ላይ በተነን›› ቤት የፈረሰባቸው ነዋሪዎች

‹‹መንግሥት ዜጎቹን በማክበር ሕገወጥ ተግባራትን ይከላከላል›› የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

Addis ababa city

በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቦሌ ቡልቡላ ወረገኑ በመባል በሚታወቀውና በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እንደሚገኙበት በተገለጸው ሥፍራ፣ ከሕገወጥ ግንባታ ጋር በተገናኘ ረቡዕ ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ነዋሪዎችና የፀጥታ ኃይሎች ተጋጭተው ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተጠቆመ፡፡

በአካባቢው ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ያለምሪት ቤት የሠሩ ቁጥራቸው በርካታ (ከ20 ሺሕ በላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ) የሚሆኑ ነዋሪዎች የሚገኙ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 12 አስተዳደር የገነባቸው ቤቶች ሕገወጥ መሆናቸውን በመግለጽ በተደጋጋሚ እንዲያፈርሱ ቢነግራቸውም፣ ‹‹ወዴት እንሂድ? በድህነት አቅማችን የሠራነውን ቤት ግምት ወጥቶለትና ካርታ ተሠርቶለት ሕጋዊ እንሁን፤›› በማለት ሲከራከሩ መክረማቸውን ነዋሪዎቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአስተዳደሩና በነዋሪዎቹ መካከል መግባባት ሳይፈጠር ቆይቶ ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች የታጀበው የወረዳው አፍራሽ ግብረ ኃይል ወደ ነዋሪዎቹ መንደር በመሄዱ፣ ከነዋሪዎቹ ተቃውሞ እንደገጠመው ተገልጿል፡፡
ነዋሪዎች አንድ ላይ በመሆን በድህነት ያቋቋሙት ጎጆ መፍረስ እንደሌለበት በመግለጽ ለመከላከል ባደረጉት እንቅስቃሴ፣ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ወደ ከረረ ግጭት በመግባታቸው ሁለቱም ወገኖች መጐዳዳታቸውን የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ በርካታ ጥይት የተተኮሰ በመሆኑ ቁጥራቸው ያልተገለጹ ሰዎች እንደሞቱ የተነገረ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግን አንድም የሞተ ሰው እንደሌለ አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው እንደተናገሩት፣ በሕገወጥ መንገድ የተገነቡ 1,040 ቤቶች አሉ፡፡ ሕገወጥ በመሆናቸው እንዲፈርሱ ተደርጓል፡፡ ቤቶቹ ሲፈርሱ በአካባቢው ግርግር ለመፍጠር የሞከሩ የነበሩ ቢሆንም፣ ነገር ግን አንድም ሰው የሞተ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎችም በወቅቱ አስለቃሽ ጭስ በመርጨት የነበረውን ግርግር ለመበተን ጥረት ሲደረግ ማየታቸውን፣ የጥይት ድምፅ እንደነበርና በርከት ያሉ አምቡላንሶች ሲመላለሱ በማየታቸው፣ የሞተ ሰው ሊኖር እንደሚችል ከመገመት ባለፈ የሞተ ሰው አለማየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ጨምረው እንዳስረዱት፣ ወረዳው ሰብስቧቸው በአካባቢው ረጅም ዓመታት ለቆዩ አርሶ አደሮች ምትክ ቦታና ካሳ እንደሚሰጥ ገልጾ፣ ሌሎች ነዋሪዎች ግን በቅርቡ የመጡና በሕገወጥ መንገድ የገነቡ በመሆናቸው እንዲያፈርሱ አስጠንቅቆ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ክረምት እየገባ በመሆኑና በድህነት የቀለሷትን ጎጆ አፍርሰው የት እንደሚሄዱ ግራ በመጋባታቸው፣ መንግሥትን ለመለመን በመዘጋጀት ላይ እያሉ ባላሰቡት ቀን መጥቶ ከነንብረታቸው በግሬደር እንዳረሰባቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹እኛ ኃይል የለንም፣ ኃይል የእግዚአብሔር ነው፣ ዜጎቹን የመንከባከብና የማስተዳደር ኃላፊነትና ግዴታ ያለበት መንግሥት በጎዳና ላይ ከበተነን እኛ ኢትዮጵያውያን ነን?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የተፈጸመባቸውን በደል አይቶ ብይን እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

በአካባቢው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውንና ልጆቻቸውም ትምህርት ማቆማቸውን ጠቁመው፣ ‹‹የትምህርት ዘመኑ እስኪጠናቀቅና መጪው ክረምት እስከሚወጣ ቢታገሱን ምን ችግር ነበረው?›› በማለትም የተፈጠረባቸውን ሐዘን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1988 ዓ.ም. እስከ 1997 ዓ.ም. ግንቦት ወር ድረስ፣ በሕገወጥ መንገድ ቤት ለሠሩ ሰነድ አልባ ቦታዎች ካርታ ሠርቶ በመስጠት ሕጋዊ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ከግንቦት ወር 1997 ዓ.ም. ወዲህ የተያዙ ሕገወጥ ግንባታዎች ግን ሕገወጥ ይዞታዎች መሆናቸውን በማስታወቅ፣ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑንም አስተዳደሩ ይናገራል፡፡

በቦሌ ወረዳ 12 ወረገኑ በሚባለው አካባቢ ስለተሠሩት ቤቶች የአስተዳደሩ መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሌ እንደገለጹት፣ ግንባታዎቹ ከ2004 ዓ.ም. ወዲህ የተገነቡና ሕገወጥ ይዞታዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም አስተዳደሩ በሕገወጥ ይዞታዎች ላይ የማያወላውል ዕርምጃ እንደሚወስድ ተናግረው፣ በወረገኑ የተወሰደው ዕርምጃም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
ምንጭ፡-ሪፖርተር ጋዜጣ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: