እንደኔ ቆሻሻ ፊት ከማነስ ይሰውራችኹ!

አቤል ዋበላ

Abel-Wabella

“እያዩ ፈንገስ” ወይም “ፌስታሌን” የተሰኘውን ትያትር ብዙዎቻችኹ አይታችኹታል ብዬ ገምታለው አልያም ስለ ማኀበራዊ እና ፖለቲካ ቀመስ ትችቶቹ በወሬ በወሬ ሰምታችኃል፡፡ እኔ ዝናውን የሰማኹት እስር ቤት ሳለኹኝ ነበር፡፡ ወያኔ እግዜር የስራዋን ይስጣትና እኔ ከወህኒ እስክወጣ ድረስ መድረክ ላይ አቆየችው፡፡ በትያትር ቤት ታድሜ እንደተዋራለት ሆኖ አገኘኹት፡፡ ይህን ጥበብ ለመድረክ እንዲበቃ ያደረጉትን እና በመድረክ እንዳይታይ ለማስተጓጎል ያልሞከሩትን አመስግኛለው፡፡

የትያትሩ አንድ ገቢር ግን እስካኹን ድረስ ውስጤ ቀርቷል፡፡ የተነሳኹበትን ሐሳብ ለማስረዳት ይረዳኛልና ይህንን ክፍል እንድተርከው ይፈቀድልኝ፡፡ እያዩ ፈንገስ ውድ ንብረቶቼ የሚላቸው ዕቃዎቹን የያዘ አንድ ፌስታል እንደጠፋበት ይናገር እና ለፍለጋ ይሰማራል፡፡ በሚኖርበት ሰፈር አቅራቢያ በሚገኙ ገንዳዎች፣ ቆሻሻ መጣያ ስፍራዎች ፈልጎ ያጣዋል፡፡ የክፍለ ከተማው ቆሻሻ መጣያ ስፍራ ሄዶ ቢፈልግም እንዳላገኘው ለተመልካቹ በሞኖሎግ ያስረዳል፡፡ በመጨረሻም የአዲስ አባባ ቆሻሻ በሙሉ “ቆሼ” እንደሚጣል እንደሰማ ተናግሮ ለፍለጋ ወደ መድረክ በስተጀርባ (ወደ ቆሼ) ይሄዳል፡፡ ከዚያ ሲመለስ የተናገረው ነገር ነው የኔን ቀልብ የማረከው፡፡ እያዩ አንዲት ፌስታሉን ፍለጋ ቆሼ ቢሄድ እራሱን ተራራ ከሚያክለው ቆሻሻ ጋር አወዳድሮ ወደተመልካቹ ተንበርክኮ “ዛሬ በቆሻሻ ፊት አነስኩላችኹ፤ እንደ እኔ በቆሻሻ ፊት ከማነስ ይሰወራችኹ” ሲል ሲቃ በተመላበት ድምጽ ተናገረ፡፡

ይህንን እንደተናገረ እኔ ከዚያ ትያትር ቤት ወጣኹኝ፡፡ በሐሳብ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ማዕከላዊ፣ አዲስ አበባ የቀጠሮ እስረኛ ማረፊያ ቤት ቂሊንጦ እና ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አስራ ዘጠነኛ ወንጀል ችሎት ሄጃለው፡፡ ለአንድ አመት ከስድስት ወር በቆሻሻ ፊት ያነስኩባከቸውን ጊዜያት አስታውስኩኝ፡፡ እየታመመኩኝ ውስጤ የሚሰማኝን ነገር አውጥቼ እንዳልናገረው የመግለጽ አቅም እያነሰኝ እያለ እያዩ ፈንገስ ደረሰልኝ፡፡

በቆሻሻ ፊት ማነስ እንዲህ ነው በሀገርህ እንደሁለተኛ ዜጋ ስለምትታይ የመብት ጥያቄዎችን አታነሳም ስለዚህ ከስርዓቱ አገልጋዮች ጋር ያለህ ግንኙነት የተገደበ ነው፡፡ ነገር ግን ሰው ነንና መሰረታዊ፣ ሰብዓዊ ፍላጎቶች ይኖሩናል፡፡ እነዚህን ለማግኘት ከማንም ጋር ይሁን መነጋገር፣ እርዳታን መጠየቅ እንገደዳለን፡፡ ለምሳሌ ሳይቤሪያ እያለን ከእስረኞቹ መሀል አንድ ሰው ይታመማል፡፡ አንዳንዴ ህመሙ እንደአተት(የሆድ ህመም) የሚደርግ ይሆንና እንቸገራለን፡፡ በር ደብድበን ይህ ሰው ሽንት ቤት ደርሶ እንዲመጣ ካላደረግን ማታ መጥተው ለአስር ደቂቃ ሽንት ቤት እንድንሄድ እስኪፈቅዱልን ድረስ የማይሆን ነገር እያየን እና እያሸተትን መቆየታችን ነው፡፡ በር ስንደበድብ ሰላማዊ ዋርድያ ካጋጠመን ታማሚውን “ቶሎ ደርሰህ ተመለስ” ይለውና ለእኛ ደግሞ ትንሽ ንጹህ አየር እንዲገባ በሩን ከፈት አድርጎት ይቆማል፡፡ ሁልጊዜ ግን ሰላማዊ ሰው ላያጋጥም ይችላል፡፡ “እዛው ቁጭ ይበል” ብሎ የሚል ይኖራል፡፡ ውጤቱ የከፋ ስለሚሆን ‘አረ ባክህ እረዳን . . . እና ሌሎች ኢትዮጵያዊ የልመና ዘዴዎችን’ ተጠቅመን ልቡን ለማለስለስ እንሞክራለን፡፡ ብዙ ጊዜ አይሳካም፡፡ ከዚህ በታች ከቆሻሻ በታች ማነስ ከየት ይመጣል፡፡ ባለ ማዕረግ ከሆነ ደግሞ ኮማንደር ወይም ሳጅን ማለትም ይጠበቅብናል፡፡

ቅሊንጦም እንዲሁ በቆሻሻ ፊት ሳንስ ከርሜ ነው የወጣኹት፡፡ ታመህ ቤተሰብ መድሃኒት እንዲያስገባልህ ለመጠየቅ ወይም ለሌላ በጣም አስፈላጊ ሰብዓዊ ጉዳይ አጋጥሞህ ሱፐር ኢንቴንዳንት፣ ኦፌሰር ምናምን ብለህ ያልተከበረውን አክብረህ መጥራት ይጠበቅብሃል፡፡ ሌላው ይቅርና “ካቴናው እጄን አጥብቆ ይዞታል ትንሽ አላላልኝ” ማለት በራሱ ለስድብ እና ማንጓጠጥ ሊዳርግ ይችላል፡፡ አንዳንድ በቆሻሻ ፊት ማነስን እና ንትርኩን የጠሉ ወዳጆቼ ካቴናው እጃቸውን እየሰረሰረው ችለው ይቀመጣሉ፡፡

ፍርድ ቤት ደግሞ ሌላው መተናነሻ ቦታ ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ ጠበቃ ባላቆም፣ ባልከራከር እና የተውኔቱ አካል ባልሆን እመርጥ ነበር፡፡ ነገር ግን በጓደኛ እና ቤተሰብ ግፊት የማልሆነውን ሆኜ ነው የከረምኩት፡፡ የዐቃቤ ህግ በሬ ወለደ ክስ እና ሙያዊ ብቃት ማነስ አእምሮ ሊገምተው ከሚችለው በላይ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ያለህ ብቸኛ ምክኒያታዊ ድርጊት ከት ከት ብሎ መሳቅ ነው፡፡ ነገር ግን ችሎት በመድፈር እስከስድስት ወር እስራት ስለሚፈረድብህ ከቆሻሻ አንሰህ ሰብዓዊነትህን ለቀህ ምንም እንዳልተገረመ ሰው ለመሆን ትሞክራለህ፡፡ ለማይረባ ጉዳይ አንድ ወር ወይም ሁለት ወር ሲቀጥርህ የተከበረ ዳኛ እና ፍርድ ቤት እንደሌሉ እያወቅክ “የተከበረው ፍርድ ቤት፣ ክቡር ዳኛ ይህ ነገር ትንሽ አልዘገየም? በማረሚያ ቤት ሆነን እየተንገላታን ስለሆነ ቀኑን አጠር ቢያደርጉት” ልትል እጅህን ብታነሳ አይተው እንዳላየ ያልፉሃል፡፡ እንድትናገር ዕድሉን እንዲሰጡህ ድምጽህን ስታሰማ ስነ ስርዓት የጎደላቸው ሰዎች “ስነ ስርዓት፣ ስነ ስርዓት” ብለው ይገስጹሃል፡፡

እያዩ ተራራ በሚያክል ቆሻሻ ፊት ማነሱን ሲናገር እነዚህን እና ሌሎች በርካታ ህሊናን የመፈታተኑ ቅጽበታቶችን ነው ያስታወስኩት፡፡ ነገም ቆሼ መውረድ አልቀረልኝም፡፡ ነገ ከጓደኞቼ BefeQadu Z. Hailu, Natnail Feleke, Atnaf Brhane እና Soleyana Shimeles Gebremichael (በሌለችበት) ጋር ጠቅላይ ፍርድ ቤት እቀርባለው፡፡ ያው እያዩ ከክፍለ ከተማ ወደ ከተማ ሲሄድ የቆሻሻ ተራራው ግዝፈት እንዳስደነገጠው እኔም እንዲሁ ክው ብያለው፡፡ ክርክር ተሰምቶ ስላለቀ የመጨረሻውን ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ወይ ቂሊንጦ አለያም ፒያሳ እንገናኝ፡፡ ምንም እንኳን አረጋዊ ሁኜ ለምርቃት ባልበቃም መልካም ምኞቴን ትቼላችኹ ልሂድ፡- እንደኔ በቆሻሻ ፊት ከማነስ ይሰውራችኹ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: