አቤል ዋበላ
እውነትን ለማስረዳት የሄግሊያን ትንታኔን መሰረት ማድረግ መርጣለው፡፡ እንደ ሄግሊያን ትንታኔ እውነት በወቅታዊ ሁኔታው የተረጋጋ የሚመስል እና ለውጥን በራሱ አቅጣጫ የሚያስተካክል ነው፡፡ ከታሪክ ፣ከትምህርት እና በአስተውሎት የሚገኙ እውነቶች አሉ፡፡ እነዚህ እውነቶችን መሰረት ያደረገ የቡድንም ሆነ የግለሰብ እንቅስቃሴ በስኬት የመጠናቀቅ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ በዙርያችን ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ለእነዚህ እውነቶች ከመቆም ያግዱናል፡፡ ወይ እነርሱን የሙጢኝ ብለን የቀረን እንደሆን እኛን እሰከመጥፋት የሚያደርሱ ጉዳቶች ያስከትላሉ፡፡ ስለዚህ ህልውናችን ከሁሉም ነገር ስለሚበልጥን እያወቅን ዝም እንላለን፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ እውነቱን ብንናገር ለማኀበረሰቡም የማይጠቅም ነባራዊ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ ይሆንና በሆድ ይፍጀው እናልፈዋለን፡፡
ከዚህ ጋር አያይዤ ማንሳት የምፈለገው ሌላው ነጥብ ደግሞ በእንግሊዘኛው Political Correctness የሚባለውን ነው፡፡ ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ግርድፍ ትርጉሙ ሌሎችን ሊያስቆጣ ይቻላል በማለት እንቅስቃሴን እና ንግግርን መገደብ ወይም ለሌሎች በሚመች መልኩ ማስተካከል ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ጥሩ ፖለቲከኛ የሚባለውም እንደ እውነቱ የሚያደርግ ሳይሆን እንደጊዜው የሚናገር እና የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ይህ ለህዝቦች በሰላም፣ በእኩልነት፣ በነጻነት አብሮ መኖር እና ወንድማማችነት ሲባል የተደረገ ሲሆን ለአድራጊው ክብር የሚያጎናጽፍ እና አስተዋይነቱን የሚያስረዳ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለዕኩይ ዓላማ፣ ለፍቅረ ነዋይ፣ ለስልጣን ጥማት፣ ለእዩኝ እዩኝ ባይነት(Publicity) አልያም በማስተዋል እጦት እና በሞኛሞኝነት ሲሆን ደግሞ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡ እውነትን ስላልተከተለ የስኬት መጠኑ የተገደበ ይሆናል፡፡ ማኀበረሰቡም ከእውነት እና ከታቀደለት ስኬት ስለሚርቅ ድርብ ኪሳራ ይደርስበታል፡፡
ይህንን ሳስብ ሁልጊዜ ወደ ህሊናዬ የሚመጣው መለስ እና ኢሳያስ የሄዱበት መንገድ ነው፡፡ መለስ እና ኢሳያስ ለዕኩይ ዓላማቸው ሲሉ እውነትን ያጣመሙ እና በተንኮል ብዙዎችን ያሳቱ ናቸው፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂ በትውልድ ከመለስ ዜናዊ የበለጠ የትግራይ ተወላጅ ሆኖ ሳለ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ነፍጥ አነሳ፡፡ (የመገንጠል ጥያቄ እንዲነሳ ያደረጉ ሌሎች ታሪካዊ እውነታዎች መኖራቸውን እየካድኩኝ አለመሆኑ ይሰመርበት) የኤርትራ ህዝብ በደም፣ በ ስነ ልቦና ቅርጽ፣ በኢኮኖሚ እና በባህል ከኢትዮጵያ ተነጥሎ መኖር እንደማይችል ሳይረዳው ቀርቶ አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህንን እውነት ከአደባባይ ገሸሽ አድርጎ አትራፊ የመሰለውን ለግለሰባዊ ፍላጎቱ የተመቸውን መንገድ መረጠ፡፡ የኤርትራ እና ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የእርስ በርስ ጥገኝነት በትዕቢቱ ብቻ ሊለውጠው እንደማይችል ሲረዳ ይህንን የሚያስቀጥልበት ሸር ጎነጎነ፡፡ ለዚህም ወያኔን እንደ አሻንጉሊት በኢትዮጵያ በማንገስ እንደፈለገው እየጠመዘዘ ኤርትራን በቀጥታ ኢትዮጵያን ደግሞ በእጅ አዙር መግዛት ፈለገ፡፡ ይህ ለተወሰኑ አመታት የተሳካለት መሰለ፡፡ በመጀመሪያዎቹ የወያኔ አገዛዝ ዓመታት የኢትዮጵያ የደህንነት እና ፖሊስ የመሳሰሉ ወሳኝ የፖለቲካ ሀይል ማዕከሎች በኤርትራውያን የበላይነት ነበር የሚመሩት፡፡ በኢትዮጵያ የሚበቅሉ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ኤርትራ ከአንጋፋ አቅራቢ ሀገሮች አንዷ የሆነችበት አመታትም ነበሩ፡፡ ይህ ከእውነት ርቆ ያዋቀረው ደባ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ፈረሰበት፡፡ ለዚህም ይመስላል ከጦርነቱ ወዲህ ኢትዮጵያን የኤርትራ ዋነኛ ጠላት አድርጎ ብዙኃኑን ኤርትራዊ ለስደት ዳርጎ ካርታው ጠፍቶበት የተቀመጠው፡፡ ህዝቡም ይህንን ‘አጋሜ አምባገነን’ የሚያስወግድበት መላ ጠፍቶት እየባከነ ይገኛል፡፡
በአንጻሩ መለስ ዜናዊ መጀመሪያ አከባቢ ምንም እንኳን ከኢሳያስ አፈወርቂ የበለጠ የኤርትራ ደም ቢኖረውም በትግራይ ብሔርተኝነት እና “ትግራይ-ትግሪኝ” በምትባል ሐሳባዊ ማንነት ሲዋልል እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡ ነገር ግን እንደ ኢሳያስ አፈወርቂ ትግራይንም ሆነ ኤርትራን ከኢትዮጵያ የተነጠሉ ሀገሮች ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚበልጥ በመረዳቱ ከኢሳያስ በመንፈሱ አንድ የሆነ ነገር ግን በቅርጹ የተለየ ሴራን ሸረበ፡፡ ትግራይ ብቻዋን በመሆኗ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የምታጣውን ነገር ለማካካስ ከትግራይ ዘውግ ውጪ ያሉ ደካማዎችን በመሰብሰብ እነርሱን የሌላው ህዝብ የይስሙላ እንደራሴ በማድረግ በመላው ኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ አዛዥ ሆነ፡፡ እውነትን ትቶ በተንኮል መንገድ ስለሄደ ሁሉንም የሚያስማማው ስኬት ላይ ባይደርስም እርሱ እና ቤተሰቡ፣ በርከት ያሉ ከአንድ ዘውግ የተገኙ እና ሌሎች ጥቂት ሰዎች የሀገሪቱን ሀብት እንዲበዘብዙ መንገድ ከፈተ፡፡ እርሱን ሞት ቢወስደውም ይህ የብዝበዛ መንገድ በቅርቡ የሚዘጋ አይመስልም፡፡
ይህ የተንኮል መንገድ እና የደረሰብን ሀገራዊ ኪሳራ ብዙ ሊያስተምረን ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከአንዳንድ ሁኔታዎች ለመረዳት እንደሞከርኩት የገባን አልመሰለኝም፡፡ በውሽት እና በሸር መንግስት የሚባል ነገር ተቋቋመ ያንን ተከትለን ፈሰስን፡፡ የወንበዴ ስብስብ ፓርቲ ነኝ ሲል እንዳልሆነ እያወቅን ለፖለቲካዊ ትክክለኝነት ስንል ተቀበልነው፡፡ ይባስ ብሎ ይህ የወንበዴ ቡድን ራሱ ጠፍጥፎ ካዘጋጃቸው ሦስት ቡድኖች ጋር ሆኖ ሀገራዊ ፓርቲ ነኝ ሲል አንዴ መስመሩ ስለገባን ይህንንም ከመቀበል በቀር አማራጭ አልነበረንም፡፡ ከፕሮፌሰር አስራት ጀምሮ ብዙዎች ለዚህ ወንበዴ ቡድን እውቅና ሰጥተው ወንበዴው ባዘጋጀው ቀመር መሰረት መጫወትን መረጡ፡፡ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ያሉ ጥቂቶች ገና ስርዓቱ ሲጀመር አንስቶ ይህ ስርዓት ቅንነት እና መዋቅራዊ ርዕቱነት ይጎለዋል ቢሉም የሰማቸው አልነበረም፡፡ ለዚህ ለወንበዴ ቡድን የሚሰጥ ዕውቅና ጫፍ ላይ የደረሰው በ97 ምርጫ ነው፡፡ገና ከጫካ ያልወጣውን ቡድን ሀገር በሙሉ ተሰብስቦ የዴሞክራሲ አዋላጅ አደረገው፡፡ ያን ጊዜ በባህሪው ያልነበረውን ነገር መሸከም ስላልቻለ እውነተኛ ማንነቱ ገሀድ ወጣ፡፡ ከጠብመንጃ አፈሙዝ በቀር ሌላ ቋንቋ እንደሌለው ከህጻናት እስከ አረጋውያን በመግደል አረጋገጠ፡፡ ከዚያ ወዲህ ባሉት አመታት ማስመሰሉን ቀንሶ እንዳሻው እያሰረ፣ እያሰቃየ አንዳንዴም እየገደለ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ድፍን ሀያ አምስት የተንኮል አመታት፡፡
ከላይ በመግቢያዬ እንዳነሳኹት ለህዝብ ጥቅም በጎ ዓላማ ሲባል እያወቅን እውነትን ብንጎዳትም ከሰው የሚበልጥ ነገር በምድር ስለሌለ ይኹን ብለን ማለፉ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን እንዲህ እውነትን እየጎዳን፣ ፖለቲካዊ ትክክለኝነትን እየመረጥን ሀያ አምስት አመታትን አሳልፈን ህዝቡን ለብሔራዊ ጭቆና፣ ችጋር እና ስደት ከዳረግነው ሀገሪቱን ለመጠን አልባ ምዝበራ ከተውናት የሄድንበትን መንገድ ቆም ብለን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም የዱር እንሰሳ ስላባበልነው ብቻ ለማዳ ይሆናል ማለት ዘበት ነው፡፡ አንዳንድ የዱር እንስሳት ፈጽሞ ሰው አይለምዱም፡፡ ወያኔም እንደነዚያ አራዊት መሆኑን ባለፉት ሀያ አምስት አመታት አስመስክሯል፡፡ እስኪ እውነት ይዘን ደግሞ እንሞክረው፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃም እውነት ወደ ስኬት ለማድረስ የተሻለ ዕድል አለው፡፡
ለግለሰባዊ ፍላጎቱ የቆመ ሰው ምንም አይነት አሳማኝ ነጥቦች ብንደረድርለት ፖለቲካዊ ትክክለኝነቱን የሙጢኝ ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱ የእንጀራ ገመዱ በዚያ የታሰረ ሰለሆነ ነው፡፡ አሁን እኔ ለመሞገት እየሞከርኩኝ ያለኹት በማስተዋል እጥረት ወይም በሞኛሞኝነት እንደው በዚህ መንገድ ብንሞክር ብለው ለሚያስቡ የዋሃን ነው፡፡ ይህንን ሙከራ የሚወልደው ህዝባዊ እምቢተኝነት እና ሰላማዊ ትግልን በትክክል አለመረዳት ይመስለኛል፡፡ አንድ ሰላማዊ ተጋይ ገዢው በፈቀደለት ቦይ ብቻ የሚፈስ ከሆነ ትግሉን ይጀምረዋል እንጂ አይጨርሰውም፡፡ ሰላማዊ ትግል ግን የህዝብን እውነት መሰረት አድርጎ በተፈቀደለትም ባልተፈቀደለትም የሚጓዝ ነው፡፡ ህዝባዊ እምቢተኝነት ቀመር ያለው ሳይሆን እንደየሀገሮች ሁኔታ ባልተለመደ(unorthodox) መልኩ የሚደራጅ ነው፡፡ይህ ያልተለመደ መልክ ምዕራባዊ ቀመር አያስፈልገውም፡፡ ይህ ህዝባዊ እምቢተኝነት የሚጀምረው ጨቋኙ ስርዓት ከህዝቡ የሚፈልገውን እውቅና በመንፈግ ነው፡፡ የህዝብን እውነት የያዘ በቂ ሰው እውቅና እሰኪነፍገው ድረስ ስርዓቱ በሁለት እግሩ እንደቆመ ይቀጥላል፡፡
በሀገራችን ያለውን ጨቋኝ ስርዓት ዕድሜውን የሚያራዝመው ሲጨንቀው ሀይል (Force) ከመጠቀሙ በቀር ብዙኃኑን ኢትዮጵያዊ እና ዓለምአቀፉን ማኀበረሰብ በማታለል (fraud) ነው፡፡ ይህንን ማታለል ደግሞ መስበር የሚቻለው ዕውቅና በመንፈግ ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚባል የአራት ፓርቲዎች ስብስብ አይደለም ሕወኃት የሚባል የፖለቲካ ማኀበር ሀገሪቱን እየመራት እንዳልሆነ ለፖለቲካዊ ትክክለኝነት ብለን ካልሆነ በቀር ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ይህ ቡድን ስሙ “ወያኔ” ነው፡፡ እውቅና መንፈግ የሚጀመረው ይህንን ጭምብል በማውለቅ ነው፡፡ ማን ትዕዛዝ እያስተላለፈ የሰብዓዊ መብት ረጋጣ እንደሚፈጸም እነርሱ እጅ ገብቶ የነበረ ሰው ሁሉ ይረዳዋል፡፡ ወያኔ የሚለውን የትግርኛ ቃል እየጠቀሱ ትርጉሙ እንዲህ ነው እንዲያ ነው የሚል ሁሉ የዚህን ቡድን የተረት ጅብድ አጽዳቂዎች ናቸው፡፡ ወያኔ የሚለው ቃል የትግርኛ ትርጉሙን ተሻግሮ በሕገ ወጥ መንገድ የፖለቲካ ሀይልን ለሀያ አምስት አመታት ይዞ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ሲገፍ የቆየ ቡድን መጠሪያ ሆኗል፡፡ ስለ ነጻነት የምር ግድ የሚለው ሁሉ ከዚህ ቡድን እና መጠሪያው ‘ወያኔ’ መሻገር ይገባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ኢዮብ ባልቻ እንዳስተዋለው ‘የዘመኑ ወጣት በጭፍን የ “ያ ትውልድ”ን ታሪክ በጭፍን ከማድነቅ ወጥቶ በጥንቃቄ ወደ መመልከት እንደገባው’ የትግራይ ወጣትም ለህዝቦች በሰላም፣ በእኩልነት፣ በነጻነት አብሮ መኖር እና ወንድማማችነት ሲል ከባዶ ተረት ወደ እውነታ መምጣት ይገባዋል፡፡ የዚህ ቡድን ሰዎች ላለፉት ሀያ አምስት አመታት በሀገሪቱ ላይ የፈጸሟቸውን ተግባሮች ተመልክቶ ትምህርታቸውን ጥለው ጫካ ገብተው ያንን የትግራይ ገበሬ ብዙ የህይወት መስዋዕትነት ያስከፈሉት ለምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ይገባዋል፡፡
በመጨረሻም የወያኔ አገዛዝ እውነትን ሳይከተል ነገር ግን ሌሎቻችን በሰጠነው የፖለቲካ ትክክለኛነት ይሁንታ ሀያ አምስት አመታትን ተጉዟል፡፡ ወደ መፍትሔው ስንመጣ ወደኋላ መመለስ አለብን ማለት አይደለም፡፡ ምንም እንኳን ስርዓቱ ቅንነት ቢጎለውም በእነዚህ ዓመታት በጎም ሆነ መጥፎ ነገሮች ተከስተዋል፡፡ እነዚህ በጎ ነገሮች እና ከመጥፎዎቹ ውስጥ ደግሞ ወደኋላ ለመመለስ የሚከብዱ ነባራዊ ሁኔታዎችን ለመለየት ሰፊ ጥናት እና የሰከነ ውይይትን አድርገን ነገን ማሰብ መጀመር ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን ይህ ለወያኔ እውቅና መስጠትን አይጨምርም፡፡ ምክንያቱም ወያኔን ያለስሙ ኢህአዴግ ወይም ሕወሓት ብለን ስንጠራው ጭቆናው ለሚቀጥሉት ሀያ አምስት እና ሐምሳ አመታት እንዲቀጥል እየወሰንን ነው፡፡