የሚዲያና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በኢሕአዴግ ላይ የሰላ ትችት አቀረቡ

የማነ ናግሽ

‹‹ሙስና የሥርዓቱ ባህል እየሆነ መጥቷል›› በማለት ኢሕአዴግ ላይ የሰላ ትችት ያቀረቡት የሚዲያና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ባለፉት 25 ዓመታት ሙሉ የሚወራው ስለሙስና መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓርብ ግንቦት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. 25ኛውን ዓመት የግንቦት 20 የብር ኢዮቤልዮ በዓል አስመልክቶ ከጋዜጠኞችና ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በብሔራዊ ቴአትር በተደረገው ውይይት፣ ተሳታፊዎቹ ኢሕአዴግንና እሱን የሚመራው መንግሥትን ገምግመዋል፡፡ ድርጅቱ ሥልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ስለሙስና፣ ስለኪራይ ሰብሳቢነትና በሥልጣን ስለመባለግ ቢወራም ተመጣጣኝ ዕርምጃ ሲወሰድ አልታየም በማለት ክፉኛ ተችተዋል፡፡

ለውይይቱ መነሻ የሚሆን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አያሌው የግምገማ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፣ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት ይደበቃል፡፡ ሕዝቡ ግልጽ ሆኖለት ከተታገለው ግን እታች ተወርዶ ማቃጠል ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ይህች አገር ፈርሳ ነው እየተሠራች ያለችው፡፡ እስካሁን ያስመዘገብናቸው ድሎችም ሊፈርሱ ይችላሉ፤›› በማለት ነበር የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋን አስመልክተው በሰጡት ሐሳብ ጽሑፋቸውን የደመደሙት፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ፈተናው ትልቅ ነው ይላል፡፡ አይደለም ድልን ልናስመዘግብ ያረጋገጥነውም ሊበላብን ይችላል፣ ወደኋላ ሊወረውረንም ይችላል፤›› በማለት፡፡

ውይይቱን የመሩት የብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ ዘርአይ አስገዶም መድረኩን ለተሳታፊዎች ክፍት ሲያደርጉ አንዳንድ አድናቆቶች የቀረቡ ቢሆንም፣ በአብዛኛው የትችት ሐሳቦች ተንፀባርቀዋል፡፡

አቶ እንድርያስ ተረፈ አስተያየት ከሰጡት መካከል የመጀመርያው ናቸው፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ወደ አዲስ አበባ ሲገባ ‘ሌባ አይወድም’ ይባል ነበር፡፡ ዛሬ ግን ራሱ ኢሕአዴግ ሌብነት መገለጫው እየሆነ መጥቷል፡፡ 25 ዓመት ሙሉ የምናወራው ስለሙስና ነው፡፡ ሌብነት የሥርዓቱ ባህል እስከመሆን ደርሷል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹መኖር ከአቅም በላይ በሆነበት ዘመን ዛሬም የምናወራው ስለሙስና ነው፡፡ ከ25 ዓመት በኋላ ዛሬ ምን ተለወጠ? ምን አገኘንና በምን እንለካው?›› በማለት አክለዋል፡፡

‹‹ቤት አገኛለሁ ብዬ ኮንዶሚኒየም የተመዘገብኩት 97 ላይ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ቤቶቹ ጠፉ እየተባሉ ነው፡፡ አንድ ሕንፃ ሲጠፋ ማን ተጠየቀ? ሕንፃዎቹ እስኪጠፉ መንግሥት የት ነበር?›› ብለዋል፡፡

የኪነጥበብ ባለሙያው አቶ ኃይላይ ታደሰ በበኩላቸው የቀረበው ሪፖርት ወደ ጥንካሬው ያመዘነ መሆኑን ገልጸው ነበር ትችታቸውን ያቀረቡት፡፡ ‹‹እንደ ባለሙያዎች እምብዛም ተጠቃሚ አይደለንም፡፡ አንቀጽ 29 ላይ የተቀመጡ መብቶችን እንዳንጠቀም የሚያግዱ አፋኝ ደንቦች እየተረቀቁ ይገኛሉ፡፡ ይኼ ከሴንሰርሺፕ (ሳንሱር) ተለይቶ የሚታይ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ኃይላይ ትችታቸውን በመቀጠል፣ ‹‹ኢሕአዴግ ከአፄ ኃይለ ሥላሴና ከደርግ ጋር ራሱን እያወዳደረ ዕድገት አስመዘገብኩ ሲለኝ ያንስብኛል፣ ይወርድብኛል፤›› በማለት ድርጅቱ እንደ መንግሥት በራሱ ከያዘው ዕቅድ አንፃር፣ ከሰፊው ሕዝብ ተጠቃሚነት አንፃር መመዘን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

‹‹ስብሰባና በዓል ታበዛላችሁ፡፡ ይኼ ሁሉ የተከፈለው መስዋዕትነት በተግባር ቢለካ አንድ ሰው ሌባ ከሆነ ሌብነቱን በሕዝብ ፊት አጋልጡት፡፡ አለበለዚያ ቁርጠኝነቱ ያላችሁ አይመስለንም፡፡ ከአንድ ቦታ አንስታችሁ ሌላ ቦታ ትሾሙታላችሁ፡፡ ለእኔ ቀልድ ነው የሚመስለኝ፡፡ ተግባብቶ ለውጥ የሚያመጣ ተግባር እያካሄዳችሁ አይመስለኝም፤›› በማለት ቀጥለዋል፡፡

‹‹አንድ ለልማት ተነሽ የሆነ አካባቢ ስታፈርሱትና ስታነሱት በጣም ነው የምትጣደፉት፡፡ አጥራችሁ ስታስቀምጡ ግን ረዥም ጊዜ ነው፡፡ አራት ከንቲባዎች ሲቀያየሩ ታጥሮ የተቀመጠ ቦታ የለም ወይ?›› በማለት የፍትሕ ማጣትና ሌሎች ማሳያዎችንም አቅርበዋል፡፡
ሕዝቡ የዕድገቱ ተጠቃሚ አለመሆኑንና ከአቅሙ በላይ በኑሮ እየተሰቃየ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ‹‹ዕድገቱ ጤነኛ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ጥቂት ከጉምሩክና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር የሚመሳጠሩ ዜጎች ያገኙትና የተሠሩ ነገሮች እንደ ዕድገት ከተለኩ እኔ ትክክል አይመስለኝም፡፡ የሕዝቡ ቁጥር መጨመርና ዘመኑ የደረሰበት ቴክኖሎጂ መለኪያው ያ ከሆነ አይገባኝም፤›› በማለት መንግሥት ባልተሠሩ ነገሮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል፡፡ ‹‹ችግሮቹ ያመዝናሉ፤›› በማለት፡፡

‹‹ሥርዓቱ ውስጥ በተደራጀ በቡድን አንዱ ሌላውን የሚጠልፍበት ሁኔታ የለም? ከሕዝብ የተደበቀ ነው? አይመስለኝም፡፡ ራሳችሁን ፈትሹ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትን የፈጠራችሁት እናንተ ናችሁ፡፡ ከሕዝብ የተደበቀ ነገር የለም፡፡ የክፍለ ከተማ ሹማምንቶች ቪ-8 አይደለም የሚያሽከረክሩት? ቪ-8 የሚነዳባት አገር ናት እንዴ ይህች አገር? ታክስ አልከፈልክም ተብሎ ግን ዘብጥያ ይወርዳል፤›› በማለት አስተያየታቸውን የቀጠሉት አቶ ኃይላይ፣ ‹‹ትግሉን ረስታችሁታል፡፡ ከተከፈለው መስዋዕትነት አንፃር ያማል፡፡ ስለዚህ የዚች 25 ዓመታት ስኬት እንደ ትምክህት እንድትወስዷት አልፈቅድም፡፡ መውደቂያችሁ እሱ ነው የሚመስለኝ፡፡ በ1993 ዓ.ም. ታደስን ትላላችሁ፡፡ እሱ ህዳሴ አልነበረም፡፡ መታደስ ያለባችሁ ዛሬ ነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን ቀጠሉ፡፡

የመድረክ መሪዎችም ተሳታፊዎችም በፅሞና እያዳመጡ ነው፡፡ አቶ ኃይላይ ግን ትችታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ‹‹ለምሳሌ ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለበት አካባቢ ምን ይመስላል? ዛሬ ከማንም የተደበቀ አይደለም፤›› በማለት አንዳንድ የትግራይ ክልል አካባቢዎችን በመጥቀስ በትግል ጊዜ የተጠቀሙበት መንገድ ባለበትና አህያም ተጭና የማትሄድበት ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ የዓባይ ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኛ ሲሆን፣ ውይይቱ እንደተለመደው የፕሮግራም ማሟያ እንዳይሆን ሥጋቱን ገልጾ አስተያየቱን ጀመረ፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት የተሠሩ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ገልጾ፣ ‹‹የተሠሩ ትልልቅ ነገሮችን የሚሸፍኑ የማይረቡ ትንንሽ ስህተቶች ትሠራላችሁ፤›› ሲል በሕዝቡና በመንግሥት በኩል አሉ ያላቸውን ችግሮች ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ወረዳዎችና ቀበሌዎች እኮ ትልልቅ መንግሥታት ናቸው፤›› በማለት የተዘረጋው ሥርዓት ለሌብነትና ለስርቆት የተመቸ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በጋዜጠኛው ሌባ ለማስያዝ የሚደረግ ጥረት እንደማይሳካና ፍርድ ቤት ተሂዶም ፍትሕ እንደማይገኝ ገልጾ፣ ‹‹እንዲያው ሳስበው ዛሬ ፍትሕ ያለው በኢቢሲ የሚተላለፈው ‹‹ችሎት›› ፕሮግራም ላይ ብቻ ነው፤›› በማለት ተሰብሳቢዎችን ፈገግ አሰኝቷል፡፡ ‹‹ትልቅ ስህተት የምለው፣ የኢሕአዴግ ትልቅ ስህተት የምለው የቀበሌና የወረዳ አስተዳደሮች የፓርቲው አባል በመሆናቸው ነው፡፡ ከአንድ ቦታ በሌብነት የተባረረ ሌላ ቦታ ተቀይሮ ተሹሞ እናገኘዋለን፡፡ ደንበኛ የአሠራረቅ ልምድ ይዞ ሄዷል፡፡ እዚህ ቀበሌ ሌባ የነበረ ሰው እዚያ ሲሄድ ወንበዴ ይሆናል፡፡ ማንም የማይመልሰው ወንበዴ፡፡ ከዚህ በኋላ ያፈጠጡ ሌቦች እንዲሆኑ እያደረጋችኋቸው ነው፡፡ የፓርቲ አባል ስለሆኑ፡፡ በእኔ እምነት ይኼ ሁሉ የፓርቲ አባል አያስፈልጋችሁም፡፡ የፓርቲ ቁጥር አይደለም ሥራ የሚሠራው፡፡ አስተሳሰቡ ያልተለወጠ ሰው ለውጥ አያመጣም፤›› በማለት አንድ ምሳሌ አነሳ፡፡

‹‹በሌላ እንዳይያዝብኝ ስለፓርቲ አይደለም እያወራሁ ያለሁት፤›› በማለት ቀጥሎ ያቀረበው ምሳሌ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ቀንደኛ የቅንጅት ደጋፊ የነበረ ሰው፣ የኢሕአዴግ ደጋፊ ናቸው ብሎ ያሰባቸው ብዙ ሰዎችን ጉዳት እንዳደረሰባቸው ተናግሯል፡፡ ‹‹አሁን ብትሄዱ ወረዳውን አልነግራችሁም ራሳችሁ ድረሱበት፤›› ካለ በኋላ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ውስጥ የአንድ ወረዳ የፀጥታ ኃላፊ እንደሆነ በመግለጽ፣ ‹‹ያን ጊዜ ያላዳረሳቸውን አሁን ለማዳረስ እንዲመቸው ይሁን እኔ አልገባኝም፡፡ ይኼ ሰው በሌላ ማልያ እንዲጫወት ተፈቅዶለታል፡፡ በትክክል ሥራቸውን ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች ደግሞ ችግር ደርሶባቸው ሌላ ችግር ላይ የወደቁ አሉ፤›› በማለት እንዲህ ዓይነት ችግሮች እንዲስተካከሉ አሳስቧል፡፡

እንደ ጋዜጠኛ በ2004 ዓ.ም. ተንዳሆ መሄዱን አስታውሶ ቦታው ላይ የነበረው ሥራ የሚያስደስት እንደነበር ይናገራል፡፡ ‹‹25 ሺሕ ቶን ስኳር ማምረት ይችል ነበር፡፡ በአፍሪካ ሁለተኛ መሆን ይችል ነበር፡፡ ያኔ መጠናቀቅ ነበረበት፡፡ ዛሬም ድረስ ግን አልተጠናቀቀም፡፡ ስኳር ፋብሪካው ሲወድቅ በሒደት ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ግንድስ አላለም፡፡ በአንድ ጊዜ ግንድስ ቢል ይሰማ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ነው ዛሬ የተገነደሰው፡፡ የት ነበራችሁ? 88 ሕንፃዎች ጠፉ ሲባል የት ነበራችሁ? የተረከበውና ያስረከበውን የት ገቡ? ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው ፈርመው ያስረከቡት? ስለዚህ ችግሮቹ በአንድ ጊዜ የመጡ አይደሉም፡፡ ፀረ ሙስና ጠንካራ ነው ስትሉን ሳቄ ነው የሚመጣው፡፡ የሚከሰው የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ነው፡፡ ፀረ ሙስና ይዞ የሚለቃቸው ሰዎች አሉ እሱም ተከፋይ ነው፤›› በማለት ጋዜጠኛው ምሳሌዎችን በመደርደር ወቀሳውን ደርድሯል፡፡

ወ/ሮ ፍሬሕይወት በሰጡት ምላሽ ያቀረቡት ሪፖርት ሚዛኑ የጠበቀ መሆኑን ተናግረው፣ የቀረቡትን ቅሬታዎች ማጣራት ያስፈልግ ይሆናል በማለት አልፈዋቸዋል፡፡

የኪራይ ሰብሳቢነት ምሽግ የተባሉ ዘርፎች ተለይተው በዚያ መሠረት ዕርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ፣ እያንዳንዱ ተቋም በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የሚገመገምበት ቋሚ አሠራር መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ ላይ ያሉት ዥንጉርጉር አሠራሮች መስተካከል እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትን በተመለከተ ግን፣ ‹‹መንግሥት ሊፈጥረው አይችልም፡፡ ሕዝብን አገለግላለሁ የሚል መንግሥት ሙስናን ሊፈጥር አይችልም፤›› በማለት ተመጣጣኝ ዕርምጃ አይወሰድም የሚለውን አልተቀበሉትም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ግን መንግሥትን ጨምሮ የማይረባ ሥራ እንደሚሠራ ተቀብለዋል፡፡

‹‹ዋናውን ጉዳይ ግን መንግሥት ሕዝባዊ ነው፣ ያነሳችኋቸው ችግሮች የሉም ማለት አይቻልም፣ ጨለማ ግን አይታየኝም፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ዘርአይ በሰጡት የማጠቃለያ ሐሳብ፣ ‹‹ሥርዓቱ 100 ሺሕ፣ 200 መቶ ሺሕ መስዋዕትነት ተከፍሎበት የመጣ ነው፡፡ ሥርዓቱ በቃኝ ይኼን ሠርቼያለሁ ብሎ ከቆመ የሞተ ነው ማለት ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ የራሱን ሌቦችም እየቆረጠ የሚጥል ነው፡፡ ታጋይ የነበሩ በኃላፊነት ላይ ሆነው ሲባልጉ ቆርጦ የሚጥል ቆራጥ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንደ ኢሕአዴግ ሌባ አይደለም፡፡ አሁንም ቦታው ላይ ነው ያለው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ በጋምቤላ በተፈጸመው ጥቃትና በኤርትራ በተፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ላይ ዕርምጃ ለምን አይወሰድም ተብሎ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ አቶ ዘርዓይ፣ ‹‹የኤርትራ መንግሥት በ1993 ዓ.ም. አይደለም የገደልነው፡፡ አሁን ነው የገደልነው ጦርነት ባለመግጠም፤›› በማለት ሐሳባቸውን ደምድመዋል፡፡ ከዚህ ውጪ የመንግሥት ሚዲያን በተመለከተ በርከት ያሉ ትችቶች ቀርበዋል፡፡ ሚዲያው ራሱ ነፃና ሳይሆን የሕዝብ ሳይሆን፣ ሚዲያ ሳይያዝ ሙስናን እንዴት መታገል ይቻላል የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ሕወሓት 40ኛ ዓመቱን ሲያከብር አርቲስቶችና ጋዜጠኞች ወደ ድርጅቱ ታሪካዊ ቦታዎች እንዲሄዱ ባደረገበት ወቅት፣ ለድርጅቱ ሹማምንት ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ምንጭ፡- ሪፖርተር ጋዜጣ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: