(አዲስ ሚዲያ) ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ሊሰጥ የነበረው ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ የሆነው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ተቋረጠ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር መገለጫውን በድረ-ገፁ እንዳስታወቀው ከሆነ፤ ብሔራዊ ፈተናው እንዲቋረጥ የተደረገበት ምክንያት ከተማሪዎች መፈተኛ ቀን አስቀድሞ ኮድ 14 የእንግሊዘኛ ፈተና በመውጣቱ ነው፡፡ ሚኒስተሩን አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በመስሪያ ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ሌሎች ፈተናዎች ላለመውጣታቸው ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ባለመኖሩ ሁሉም ፈተናዎች እንዲቋረጡ መደረጉን በመጠቆም፤ ተማሪዎችን እና ወላጆቻቸውን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ እንዲቋረጥ የተደረገው የዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሌላ ፈተና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚዘጋጅ ከመግለፅ ውጭ፤ መቼ ሊሰጥ እንደተወሰነ የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የፈተናውን መቋረጥ አስመልክቶ ዛሬ አራት ኪሎ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ ፈተናው ከተማሪዎች መፈተኛ ቀን አስቀድሞ ለምን እና እንዴት ወጥቶ ሊሰራጭ እንደቻለ እና ለተፈጠረው ችግር ማን ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ከመግለፅ ተቆጥቧል፡፡
ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እንግሊዘኛ ኮድ 14 ከመፈተኛው ቀን አስቀድሞ ወጥቷል ቢሉም፤ በተመሳሳይ ትናንት እሁድ ግንቦት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. የሂሳብ ትምህርት የተፈጥሮ ሳይንስ እና ማኀበራዊ ሳይንስ የሂሳብ ትምህርት ፈተናም በተመሳሳይ መልኩ ከነ መልሶቻቸው በማኀበራዊ ሚዲያ መሰራጨታቸው ታውቋል፡፡ የአዲስ ሚዲያ ምንጮች ከሆነ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ሊጀመር የነበረው ሁሉም የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናዎች ግንቦት 11 ቀን 2008 ዓ.ም.በተለይ በኦሮሚያ ክልል ለወራት ትምህርታቸው የተስተጓጎለባቸው ተማሪዎችን ታሳቢ ሳያደርግ የፈተናውን መሰጠት በሚቃወሙና ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ከመፈተኛው ቀናት አስቀድሞ ፈተናውን አዘጋጅቶ ከሚያሰራጨው ትምህርት ሚኒስቴር፤ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ቢሮ እንደወጣ ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይም ባለፈው ሳምንት የተሰጠው የ10ኛ ክፍል ፈተናም እንደ 12ኛ ክፍሉ ባይሆንም አስቀድሞ መውጣቱና በተወሰነ መልኩ መሰራጨቱ ቢገለፅም፤ እንደ 12ኛ ክፍል ፈተና በማኀበራዊ ሚዲያ ባለመሰራጨቱ እና በገለልተኛ አካል ይፋ ባይገለፅም፤ ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ግን የ10ኛ ክፍል ፈተናም ወጥቶ መሰራጨቱን አስተባብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ከዛሬው መግለጫና የወጣው ፈተናው በማኀበራዊ ሚዲያ ከመሰራጨቱ በፊት ትናንት እሁድ ግንቦት 21 ቀን በኢቢሲ ዜና እወጃ “ፈተናው ተሰርቆ ወጥቷል የሚባለው መረጃ ሐሰት ነው፤ ስለዚህ ተማሪዎች ለዛሬው ፈተና ተረጋግተው እንዲዘጋጁ” የሚል ማሳሰቢያ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡
ለፈተናው ቀድሞ መውጣትና በማኀበራዊ ሚዲያ መሰራጨት ዋነኛ ምክንያት፤ ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለ5 ተከታታይ ወራት የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን አዲሱ የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ተቃውሞ በተለይ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል የወሰደውን የኃይል እርምጃ ተከትሎ በተፈጠረ አለመረጋጋት ፈተናው እንዲራዘም የቀረበው የተማሪዎቹና የወላጆቻቸው ጥያቄ ውድቅ በመደረጉ የተወሰደ የአፀፋ እርምጃ እንደሆነ ፈተናውን ካሰራጩት አካላት ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ከተማሪዎች መፈተኛ ቀን አስቀድሞ ወጥቶ የተሰራጨበትም ሆነ ፈተናው በሀገር አቀፍ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡