*ተከሳሹ ጥቁር ልብስ ለብሰሃል በሚል በቀጠሮው ሰዓት አለመቅረቡ ታውቋል
የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በሆነው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ የፌደራል አቃቤ ህግ ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. የመሰረተው የሽብር ክስ ግንቦት 26 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት በንባብ ተሰምቷል፡፡
ተከሳሹ ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱ ሊነበብለት የነበር ቢሆንም ከጠበቃው ጋር ሳይመካከር ክሱ እንዲነበብለት እንደማይፈልግ በመግለጹ በቀጠሮ ሰንብቶ ዛሬ ተነቦለታል፡፡ ከክስ ዝርዝሩ መረዳት እንደተቻለው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ላይ የቀረበው ክስ የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) ላይ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት መተላለፍ የሚል ሆኗል፡፡
አቃቤ ህግ በክሱ ላይ እንዳመለከተው ተከሳሹ ከ24/05/2006 ዓ.ም እስከ 13/04/2008 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ግንቦት ሰባት ከተባለ የሽብር ድርጅት አመራሮች ጋር በማህበራዊ ድረ ገጽ በተለይም ፌስቡክ እና ስልክ ግንኙነት በመፍጠር ለሽብር ቡድኑ ተልዕኮ የተለያዩ መረጃዎች በማስተላለፍና በሽብር ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል ፈጽሟል ሲል ጠቅሷል፡፡
ተከሳሹ ‹‹…በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር እየተገናኘ መረጃ በመሰብሰብ በውጭ ሀገር ለሚገኙ የሽብር ቡድኑ አመራሮች መረጃ በማስተላለፍ….›› በሽብር ድርጅት ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል፡፡
ችሎቱ ክሱን በንባብ አሰምቶ ሲያጠናቅቅ በተከሳሹ ላይ የተጠቀሱ የአቃቤ ህግ የማስረጃ ዝርዝሮችን በተመለከተ እንደገለጸው፣ ተከሳሹ የተጠቀሰበት ማስረጃ የሰነድ ማስረጃ ብቻ መሆኑ ተገልጹዋል፡፡
ተከሳሹ ከግንቦት 11 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው የችሎት ቀጠሮ በጠዋት እንዲቀርብ የሚል ቢሆንም የእስር ቤቱ አስተዳደር ‹‹ጥቁር ልብስ ለብሰህ ፍርድ ቤት መሄድ አትችልም›› በሚል ጠዋት ሳያቀርቡት ከቆዩ በኋላ ከሰዓት ሊያቀርቡት ችለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ የክስ መቃወሚያን ለመቀበል ለሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡- EHRP