ታዋቂ የኢትዮጵያ አትሌቶች በፌዴሬሽኑ ላይ ቅሬታ አሰሙ

(አዲስ ሚዲያ)ታዋቂ የኢትዮጵያ አትሌቶች ዛሬ ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት በአዲስ አበባ ስታዲየም በይፋ ባደረጉት ውይይት በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ተወያይተው፤ በጉዳዩ ዙሪያ ከፌዴሬሽኑ እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመወያየት 10 ኮሚቴዎችን ሰይመዋል፡፡ በውይይቱ ላይም አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ አትሌት አሰፋ መዝገቡ፣ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም፣ አትሌት አሰለፈች መርጊያ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ አትሌት ፋንቱ ሜጊሶ፣ አትሌት የማነ ፀጋዬ፣ ኮማንደር አበበ መኮንን እና ሻምበል ቶሎሳን ጨምሮ በርካታ ስመ-ጥር አትሌቶች ተገኝተዋል፡፡

logo-olympic-games

አትሌቶቹ ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. (እ.አ.አ ከነሐሴ 5-21 ቀን 2016 ዓ.ም.) በብራዚል ለሚካሄደው የሪዮ ዲ ጄኔሪዮ ኦሎምፒክ ብቃት ያላቸው አትሌቶች ሊመረጡ እንዳልቻሉ እና አሁንም የ5 ሺህ እና የ10 ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድሮች ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር መስራት እንደሚፈልጉ እና ለማራቶን ውድድር የተመረጡትንም ቢሆን በስነ ልቦና ደረጃ ሊያግዝ የሚችል ብቃት ያለው አሰልጣኝም ሆነ አመራር ስለሌለ በመጪው ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ ልታገኝ የምትችላቸው ድሎች አስጊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አሁን ያለው ፌዴሬሽን በብቃትም በገንዘብ አቅምም እየተዳከመ ምጣቱን እና አስጊ ደረጃ ላይ መገኘቱን በመጠቆም ብዙ የለፉበትና የለፉለት ተቋም እስኪፈርስ ድረስ መጠበቅ እንደሌለባቸው አስታውሷል፡፡ ያለውን ችግር ለመቅረፍና ለመነጋገር ከዚህ ቀደም የአትሌቶች ማኀበር ፕሬዘዳንት የሆነውን አትሌት ስለሺ ስህንን የአትሌቶች ፒቲሽን የተፈረመበት ደብዳቤ ይዞ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ ቢጠይቅም፤ አትሌት ስለሺ አልጠራም በማለቱ ለዛሬው መሰባሰብና ውይይት ምክንያት እንደሆነም ተናግሯል፡፡ አሁን ያለውን ችግርም ለመቅረፍ ከአትሌቶቹ የተውጣጣ ኮሚቴ እንደሚያስፈልግ እና ለዚህም ራሱን ከኮሚቴው አንዱ አድርጎ ዕጩ ማድረጉን በመጠቆም የመጪው ኦሎምፒክ ውጤት አሁን ባለው የፌዴሬሽኑ አሰራር በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ የሴቶች ውድድር ካልሆነ በስተቀር ሀገሪቱ የወርቅ ሜዳሊያ ስለማግኘቷ ጥርጣሬ እንዳለውም ሲናገር ተደምጧል፡፡

በተመሳሳይም አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ ገብረእግዚአብሔር፣ አትሌት ፋንቱ ሜጊሶ፣ አትሌት ዳዊት፣ አትሌት አሰፋ መዝገቡ፣ አትሌት የማነ ፀጋዬ እና መቶ አለቃ መኮንንን ጨምሮ የተለያዩ አትሌቶች በፌዴሬሽኑ እና ተጠሪነቱ ከአትሌቶቹ ይልቅ ለፌዴሬሽኑ በሆነ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኀበር ላይ የነበሩ ብልሹ አሰራሮች እና ቅሬታዎችን ሲያነሱ ተደምጧል፡፡

በተለይ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ጥሩ አቋም ላይ እያለ እና ብቃት እያለው በማራቶን እጩዎች ውስጥ አለመካተቱ ስፖርቱን በሚከታተሉ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ማስነሳቱ ቢታወቅም፤ በታዋቂ አትሌቶችም ዘንድ የቀነኒሳ በቀለ በማራቶኑ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ እንዳይገኝ መደረጉ ተመሳሳይ ቅሬታ እንዳደረባቸው በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ የአትሌት ቀነኒሳ በኦሎምፒኩ ላይ መሳተፍ ውጤት ብቻ ሳይሆን ቀነኒሳ በውድድሩ ላይ መካተቱ በራሱ ለሀገሪቱ ትልቅ ጥቅም እንዳለው በሲድኒ የነበረውን የራሱን እና የደራርቱ ቱሉን ተሞክሮ አስታውሷል፡፡ በጥሩ ብቃት እንዳለና ለኦሎምፒኩም ዝግጁ ሆኖ ሳለ ባለመካተቱ ቀነኒሳም ቅሬታ እንዳደረበት ያልሸሸገው ቀነኒሳ፤ አሁን የተመረጡ ልጆችንም ቢሆን በስነ ልቦናም ሆነ በቴክኒክ ሊያግዝ የሚችል ብቃት ያለው አስልጣኝም ሆነ አመራር ባለመኖሩ ልናግዛቸው ይገባል፤ በበኩሌ አሁን ቢጋብዙኝም በውድድሩ አልገባም ሲል ተደምጧል፡፡

በነበረው ውይይትም በአትሌት ስለሺ ስህን እና በአትሌት መሰረት ደፋር የሚመራው የአትሌቲክ ማኀበር ቢሮም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገለት ያለው በአትሌቲክ ፌዴሬሽን በመሆኑ ነፃ ሆኖ ለአትሌቶቹ ተገቢውን አገልግሎት ሊሰጥ ስላልቻለ አዲስ የአትሌቶች ማኀበርም መቋቋም እንዳለበትም ሐሳብ ተነስቷል፡፡ በተለይ አትሌቶቹን ወክሎ ከሚመለከተው አካል ጋር ለመነጋገ፣ ከ2 ወራት በታች ለቀሩት የኦሎምፒኩ ውድድርም ብቃት ያላቸውና ተገቢ አትሌቶች ተሳትፈው የሚፈለገውን ውጤት ይዘው እንዲመጡ ለማገዝ እና ለአትሌቶቹ መብትና ጥቅም የቆመ ማኀበርንም በተመለከተም ለመነጋገር 10 ኮሚቴዎችን በመምረጥ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

በውድድሩ በ42 የተለያዩ ስፖርት ዘርፎች 206 ያህል የዓለም ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በ5 የስፖርት በተለይም በሩጫ፣ በብስክሌት፣ በቦክስ በዋና እና በቴክ-ዎንዶ ውድድር ዘርፎች ለመሳተፍ ማቀዷን ይፋ ማድረጓ ይታወቃል፡፡ በዚህ ብራዚሉ ሪዮ ዲ ጄኔሪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ 4 የወርቅ፣ 4 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳልያ ለማግኘት ግብ ማስቀመጧን ከኦሎምፒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: