(አዲስ ሚዲያ) የኢትዮጵያ መንግስት በአሜሪካን ህገወጥ የቦንድ ሽያጭ በማድረግ የሰበሰበውን ገንዘብ እንዲመልስ ተወሰነበት። የአሜሪካን የቦንድ ሽያጭና ግዥን የሚቆጣጠረው ኮሚሽን ባቀረበው ክስ መሰረት፤ የኢትዮጵያ መንግስት መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን በአሜሪካን ባልተመዘገበ የቦንድ ሽያጭ የሰበሰበውን 5.8ሚሊዮን ዶላር እና 6 መቶ ሺህ ዶላር ወለድን ጨምሮ በድምሩ 6.45 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍል ተስማምቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. በህገወጥ መንገድ ገንዘቡን ሰብስቦት የነበረው ነዋሪነታቸው በአሜሪካን ሀገር ከሆኑ 3,100 ኢትዮጵያውያን ነበር፡፡ ስለሆነም በቦንድ ግዥ የተሰበሰበው ገንዘብ በሙሉ ከነ ወለዱ እንዲመለስ የተደረገው፤ የአሜሪካን ሴኩዩሪቲ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን (SEC) ህግን ተላልፎ በመገኘቱ መሆኑን የኮሚሽኑ መግለጫ አስታውቋል። የኢትዮጵያ መንግሥትም የአሜሪካን ህግ በመጣስ የቦንድ ሽያጭ ማካሄዱን በማመን፤ የቦንድ ሙሉ ሽያጩን ከነ ወለዱ ለአሜሪካ መንግሥት ለሚመለከተው አካል ለመክፈል መስማማቱን ኮሚሽኑ በዋሸንግተን ዲሲ ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡