ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የቀረበበት ክስ ተሰርዞ በነጻ እንዲሰናበት አመልክቷል

ከሽብር ቡድን አመራሮች ጋር በፌስቡክና በስልክ ግንኙነት በመፍጠር መረጃዎችን አስተላልፏል በሚል የሽብር ክስ የቀረበበት የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ክሱ ተሰርዞለት በነጻ እንዲሰናበት በክስ መቃወሚያው አምልክቷል፡፡

Getachew Shiferaw_Addismedia

ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው ጋዜጠኛ ጌታቸው አራት ገጽ ያለው የክስ መቃወሚያውን ለችሎቱ አስገብቷል፡፡

ተከሳሹ የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀጽ 7(1)ን በመጥቀስ አቃቤ ህግ ያቀረበበት ክስ “በማናቸውም መልኩ በሽብር ተግባር መሳተፍ” የሚለው፣ አንድ ሽብርተኛ ተብሎ የተሰየመን ድርጅት ስም መጥራት፣ የሽብር ድርጅቱ በሚጠቀምበት ሚዲያ መጠቀም ወይም የሽብር ድርጅት አባል ነው የተባለን ሰው ለሽብር ድርጅቱ አንዳችም ፋይዳ በሌለው ነገር ላይ ማነጋገር ሁሉ ይጨምራል በሚል ተለጥጦ መቅረብ እንደሌለበት በመቃወሚያው ላይ አመልክቷል፡፡

ተከሳሽ አቃቤ ህግ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ስለነበሩ ክስተቶች የሽብር ድርጅት አመራር ናቸው ላላቸው ሰዎች መረጃ ማስተላለፍን በሽብር ድርጅቱ ውስጥ በማናቸውም መልኩ መሳተፍ እንደሆነ አድርጎ ማቅረቡ ስህተት ብቻ ሳይሆን ከህጉ አላማም በእጅጉ የራቀ ነው ሲል ተከሳሹ ተቃውሟል፡፡

ስለሆነም የአዋጁን አንቀጽ 7(1) ጠቅሶ ክሱን ማቅረብ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጉ አንቀጽ 112 ላይ በወንጀል ጉዳይ በሚቀርብ ክስ ስለ ወንጀሉ እና የወንጀሉ ሁኔታ ስለሚሰጠው ዝርዝር ወንጀለኛው የፈጸመውን ተግባር ወንጀል ከሚያደርገው ሕግ አነጋገር ጋር የተቀራረበ መሆን አለበት የሚለውን አስገዳጅ ድንጋጌ የሚጥስ በመሆኑ የአዋጁ አንቀጽ መጠቀሱ አግባብ አይደለም ተብሎ ክሱ እንዲሰረዝለት አመልክቷል፡፡
ጋዜጠኛ ጌታቸው በሁለተኛነት ያቀረበው መቃወሚያ የህጋዊነት መርህን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ ህገ-ወጥነቱ በህግ ያልተደነገገን ድርጊት ወይም ግድፈት እንደወንጀል ሊቆጥረውና ቅጣት ሊወስንበት እንደማይገባ በማስታወስ በክሱ ዝርዝር ላይ የተመለከቱ በህግ ወንጀል ናቸው ተብለው ያልተደነገጉ ድርጊቶችን ጠቅሶ ክሱ እንዲሰረዝለት የሚጠይቀውን መቃወሚያ አስገብቷል፡፡

ተከሳሹ በሦስተኝነት ያቀረበው የመቃወሚያ ነጥብ የተከሰሰበትን ወንጀል ለይቶ በማወቅ መልስ ለመስጠት እንዲያስችለው ግልጽ ሊሆኑለት የሚገቡ ነጥቦችን በመጥቀስ ነው፡፡ በዚህ መቃወሚያ ስር ተከሳሹ ከሽብር ቡድኑ ተልዕኮ እንደተቀበለ ከመጠቀሱ በቀር ተልዕኮው ምን እንደሆነ፣ መቼ፣ ከማን እና በምን አይነት መንገድ ተልዕኮውን እንደተቀበለ ከሳሽ ግልጽ እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡ ተከሳሹ ‹‹የሽብር ቡድኑ በሚጠቀምበት ሚዲያ›› በሚል የቀረበበት ክስ በህግ ቋንቋ ምን ማለት እንደሆነም አልተገለጸም ሲል ጠቃውሟል፡፡

በመሆኑም ከሳሽ እነዚህና ሌሎች በመቃወሚያው ላይ የተመለከቱ ነጥቦችን ግልጽ እንዲያደርግ፣ ይህን ማድረግ የማይችል ከሆነ ግን ክሱ ተሰርዞ በነጻ እንዲሰናበት ተከሳሹ ለችሎቱ በመቃወሚያው ላይ አመልክቷል፡፡
ችሎቱ አቃቤ ህግ ተከሳሹ ያቀረበውን የክስ መቃወሚያ ተመልክቶ መልስ እንዲሰጥበት ለመጠባበቅ ለሰኔ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡-EHRP

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: