(አዲስ ሚዲያ) ከሰኔ 27 እስከ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ሊሰጥ የታሰበው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በድጋሚ ተራዘመ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሊሰጥ የነበረው ፈተና መከካከል ሁለት የትምህርት ዓይነቶች ቀድመው በማኀበራዊ ሚዲያ ከነመልሶቻቸው መለቀቃቸውን ተከትሎ እንዲቋረጥ የተደረገው ፈተና ከሰኔ 27 እስከ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ለመስጠት ትምህርት ሚኒስቴር መርሃ ግብሩን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ከተለያዩ አካላት ቅሬታና ተቃውሞ አስከትሎ ነበር ፡፡
በተለይ ከሰኔ 27-30 ቀን 2008 ዓ.ም. መካከል የረመዳን ፆም ፍቺ በዓል ላይ የሚውል ተቃውሞ በመቅረቡ፣ ትምህርት ሚኒስቴርም ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ቅሬታ በመቅረቡ ፈተናው በአንድ ሳምንት ተራዝሞ ከሐምሌ 4-7 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚሰጥ አስታውቋል ፡፡
ቀደም ሲል ግንቦት ሊሰጥ የታሰበውን መርሃ ግብር እንዲቀየር ያስገደዱት የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎችም ከሐምሌ 4 እስከ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚሰጠው አዲሱ መርሃ ግብር ላይ ሌላ ተቃውሞ እንደማያስነሱና ከባለስልጣናቱ ጋር እልህ መጋባቱ አላስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ፣ ተማሪዎች ከሐምሌ 4 እስከ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ተረጋግተው እንዲፈተኑ ጠይቀዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር እና የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች በየበኩላቸው በየአካባቢው ያሉ መምህራን፣ ወላጆች፣ አስተዳደሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ለተማሪዎች እንዲያደርጉላቸው የትብብር ጥያቄ አቅርበዋል፡፡