በሔኖክ ያሬድ
የቡናዋ ገበታ ጅማ ከተማ መሰንበቻውን በጅማ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ቋንቋ ግእዝን የተመለከተ አገር አቀፍ ጉባኤ አስተናግዳ ነበር፡፡
“የግእዝ ቋንቋ ሀብት ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ሦስተኛው ጉባኤ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቋንቋና የጋራ ባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክቶሬት፣ ከብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከልና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው፡፡ በጉባኤው አሥር ወረቀቶች ቀርበውበታል፡፡
“ግእዝን የኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክና ባህል የተጻፈበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ብሔረሰቦች ሊቃውንት በጋራ ያሳደጉትና ያበለጸጉት ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ነው፤” የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ሥርግው ገላው እንደማሳያነት ያቀረቡት ቀደምት የኦሮሞ ሊቃውንት ድርሻን በማሳየት ነበር፡፡
እንደ አፄ ሱስንዮስ ታሪክ ጸሐፊ አዛዥ ጢኖ (አለቃ ተክለሥላሴ)፣ እንደ ዝነኛው የቅኔና መጻሕፍት መምህር አለቃ ገብረሥላሴ ክንፉ፣ እንደ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ታሪክ ጸሐፊ አለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ፣ እንደ ዝነኛው የቅኔና መጻሕፍት መምህር መምህር ጥበቡ ገሜና ሌሎችም በርካታ የኦሮሞ ሊቃውንት ለግእዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ያደረጉትን አስተዋጽኦ ዶ/ር ሥርግው አስታውሰዋል፡፡
አዛዥ ጢኖ የጻፉት የአፄ ሱስንዮስ (1597-1625) ዜና መዋዕል ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ ከተጻፉት ዜና መዋዕሎች በብዛትም (የአፄ ሠርፀ ድንግልን ሳይጨምር) ሆነ በጥራት ከሁሉም የተሻለ ነው ብለውታል አጥኚው፡፡
ዶ/ር ሥርግው በማሳያነት ያቀረቡት ሌላው ሊቅ አለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ ከታሪክ ጸሐፊነታቸው በተጨማሪ በሠዓሊነትም ይታወቃሉ፡፡ በ1860 ዓ.ም. አካባቢ ወለጋ ኩታይ [ጉድሩ] ውስጥ የተወለዱት አለቃ ተክለኢየሱስ የጎጃም ንጉሥ ተክለሃይማኖት ታሪክ ከመጻፋቸውም ሌላ በ1961 ዓ.ም. የልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን የአውሮፓ ጉብኝትና የዚህ ጉብኝት ተሳታፊ በነበሩት በራስ ኃይሉ አለመኖር ምክንያት በደብረ ማርቆስ ከተማ የተፈጠረውን ግርግር አካትተው የጻፉት ይጠቀሳል፡፡
የግእዝ ቋንቋ በአፍ መፍቻነት ያገለግል በነበረበት ጊዜ እንደማንኛውም ቋንቋ ባህላዊ ዘፈን ሲዘፈንበት የቆየ መሆኑን ያመለከቱት ሌላው ጥናት አቅራቢ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ሙሉቀን አንዱዓለም ናቸው፡፡ ‹‹ማሕሌተ ገንቦ›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናታቸው እንዳመለከቱት፣ ማሕሌተ ገንቦ የሚባለው የግእዝ ዘፈን ከጥንት ጀምሮ ሲዘፈን የመጣ የዘፈን ዓይነት ነው፡፡ ሰይህ ዓይነት ዘፈን የሚዘፈነው በአሁኑ ሰዓት በቤተ ክህነት ሰዎች ሲሆን ዘፈኑ የሚከናወንባቸው ዐውዶችም የተለያዩ ናቸው፡፡ በዋናነት ሠርግን፣ ማኅበርን፣ የዓመት በዓልን፣ ክርስትናን፣ በአጠቃላይ ካህናቱ በሚጠሩባቸው የደስታ ድግሶች ሁሉ ይከናወናሉ፡፡
የማሕሌተ ገንቦ ዘፈኖች በአሁኑ ሰዓት የሚዘፈኑት ለካህናት ሆነው የሚዘፈኑባቸው ዐውዶችም ሠርግ፣ የዓመት በዓላት፣ ክርስትና፣ ማኅበር ወዘተ. ቢሆኑም ለዚህ ጥናት የቀረቡት የሠርግ ግጥሞች ናቸው፡፡ በማሳያነት ከቀረቡት መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡
‹‹ዝ ጠላ ከመ ወይን ጣእሙ፤ እስኪ ድግሙ ድግሙ እስኪ ድግሙ
ይህ ጠላ ጣዕሙ እንደ ወይን ነው፡፡ እስኪ ድገሙ፤ እስኪ ድገሙ፡፡
እመይቴ ጥሩ ዓይነት እጅሽን ይባርከው መልሶ መልሶ፣
ያደረግሽው ጠላ በማር ተለውሶ፣
ቁርጥማት አይንካው ጥሩዬ እጅሽን፣ ይህንን ጠላና ጠጅ ያረገውን፣
ይህን ጠላና ጠጅ የጠጣችሁ ኹሉ፣
ጥሩ ዓይነት ጥሩ ዓይነት እጡብ ድንቅ በሉ››
እንደ ዶ/ር ሙሉቀን ማብራሪያ፣ ይህም በኢትዮጵያ ባህል የደገሰውን ሲበሉለት፤ የወለደውን ሲስሙለት ባለቤቱ በጣም ደስተኛ ስለሚሆን የማስደሰት ኃይሉ ከፍተኛ ነው፡፡ መልእክቱም የሚጠጣው ጠላ እጅግ ተወዳጅ በሚሆንበት ጊዜ ደጋግመው እንዲጠጡ ጥያቄ የሚያቀርቡበትና ጠላውን የሚያደንቁበት ስንኝ ነው፡፡
ከሴትዮዋ ስም ጋር በማስተባበር ዓይነቱ ጥሩ እንደሆነ አመስጥረውበታል፡፡ ይህ ስንኝ በሐዲስ ዓለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍም ተጠቅሶ ይገኛል፡፡
‹‹ወይቤላ ንዒ ከመ ንትዋነይ››
የዚህ ስንኝ ትርጉምም፡- ሙሽራው ሙሽሪትን እንጫወት ዘንድ ነዪ አላት፡፡ ለማለት ነው፡፡
ብዙውን ጊዜ የማሕሌተ ገንቦ ግጥሞች ደራሲያቸው ስለማይታወቅና በምሁራን የማይደረሱ የሕዝብ በመሆናቸው እንደ ቅኔ ጠንካራ ሕግ የላቸውም፡፡ በግእዙ ስንኝ ላይ ያለውን ስንመለከት ባለቤቱ (ጠሪውም ተጠሪዋም) በግልጥ አልተቀመጡም፡፡ ሲፈልግ የአማርኛ፣ ሲፈልግ የግእዝ ወይም ደግሞ እያቀላቀለ ግጥሞችን ያስገባል፡ በምሳሌነት የሚከተለውን አጥኚው አሳይተዋል፡- ‹‹ወይቤላ ንዒ ከመ ንትዋነይ፡፡
ተማሪ ተማሪ ተማሪ ቢሉሽ፤
ከጉድጓድ የወጣ ገብስ አይምሰልሽ፤
መደረቢያው ካባ መጠምጠሚያው ሻሽ፤
ወይቤላ ንዒ ከመ ንትዋነይ፡፡
ተማሪውና ሙሽራዋ በሚጋቡበት ጊዜ ሙሽራዋ የቄስ ተማሪ ስታገባ ቅር እንዳይላት በካባ፣ በሻሽ የተንቆጠቆጠ ምሁር እንጂ ከጉድጓድ እንደ ወጣ ገብስ የተናቀ አይደለም ለማለት ነው ሲሉ አጥኚው አብራርተዋል፡፡
በዚህ ጥናት ውስጥ ኅብረተሰቡ አብሮ በግእዝ ይዘፍን እንደነበረ፤ ቋንቋውም እንደማንኛውም ቋንቋ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ለዓለማዊ ዘፈንም አገልግሎት ይሰጥ እንደነበረና የዜማው ሁኔታም ሲታይ የራሱ የሆን ውበት ቢኖረውም ከቅዱስ ያሬድ ዜማ አጠርና ፈጠን ያለ ምት እንዳለውና የኅብረተሰብን የአኗኗር ሁኔታ የሚዳስሱ ማኅበራዊ ግጥሞች በመሆናቸው ማሕሌተ ገንቦ በደምብ ሊጠና ይገባል የሚል ምክር አዘል መልእክት ጥናት አቅራቢው አቅርበዋል፡፡
በሦስተኛው ጉባኤ ከቀረቡት ጥናቶች መካከል የዝዋይ ሐይቅ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ቅርሶችን የዳሰሰ፣ ግእዝ ለአማርኛ የፍልስፍና ቃላት ያደረገው አስተዋጽዖ፣ በግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ስለሚገኘው የሥነ ፈለክ ትምህርት፣ እውቀት እንደ ሕንጻ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ፍልስፍና እና የግእዝ ግሶች ሥነ ድምፅ የሚተነትን ሶፍትዌር ለመሥራት የተደረገውን ጥረት አመልካች ጥናቶች ይገኙበታል፡፡
ከአዲስ አበባ ደቡብ ምዕራብ 346 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኘውና ጉባኤውን ባስተናገደው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ አነጋገር፣ በግእዝ ቋንቋ የተከማቹ የመረጃ ሀብቶች ለአገሪቱም ይሁን ለጠቅላላው የሰው ልጆች በርካታ ጥቅም ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ዕውቀቶች ያዘሉ ናቸው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ እነኚህን በርካታ ዕውቀቶች አውጥቶ ለዘመናዊው የኑሮ ሥርዓት ጥቅም ላይ ለማዋልም ይሁን ለቋንቋዎቻችን ዕድገትና ልማት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በሚመለከታቸው የመንግሥትም ይሁን ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት በመዋቅር፣ በአደረጃጀትና በስትራቴጂ የሚሠራ አካል እምብዛም እንደማይታይ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ፍቅሬ፣ ከአገሪቱ ይልቅ ምዕራባውያን ከቋንቋውና ቋንቋው ከያዘው መረጃ ተጠቃሚ ለመሆን ለበርካታ ዓመታት በቋንቋው ላይ ጥናት ከማከናወናቸው ባሻገር፣ በዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ ተመራማሪዎችንና አማካሪዎችን በማፍራት ራሳቸውን የቻሉ የግእዝ የትምህርት ክፍሎች ከፍተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም፣ የግእዝ ቋንቋ በውስጡ አምቆ የያዛቸውን የሕክምና፣ የምህንድስና፣ የሥነፈለክ፣ የሥነትምህርትና የኪነጥበብ ትሩፋት የሚጣጣሙበት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ለወደፊቱ ለአገር ዕድገት መሠረታዊ የሆኑ ዕውቀቶች እየተመረመሩ ከዘርፉ የሚገኘውን አገራዊ ጥቅም የሚያድግበት እንደሚሆን ተስፋቸው መሆኑን ሳይናገሩ አላለፉም፡፡
በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ፣ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችና መረጃዎች የሕክምና ጥበብ ምንጭና የባህላዊ መድኃኒቶች መሠረት የሚጠቁሙ፣ የነገሥታት አስተዳደር፣ የሕጋዊ የዳኝነት ሥርዓት፣ የሕዝቦች የመቻቻልና የመደጋገፍ ጥበብና ሥርዓት፣ እንዲሁም የዘመን አቆጣጠር መነሻና መሠረት ምንጭ መሆኑ ያመለክታሉ ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ጮሻ፣ ይህም የግእዝ ቋንቋ የሥራ፣ የመግባቢያና የመተዳደሪያ ቋንቋ እንደነበረ ያመለክታል ብለዋል፡፡ የግእዝ ጉባኤ መካሄዱ ትክክለኛ መረጃ በማድረስ ግንዛቤውን ለማሳደግ ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸውም አቶ አብርሃም ተናግረዋል፡፡
ሃቻምና በአክሱም የተጀመረው የግእዝ ጉባኤ፣ አምና ሁለተኛውን ጉባኤ በባሕር ዳር ማከናወኑ ይታወሳል፡፡ በዘንድሮው ጉባኤ ማጠቃለያ በተደረገው ውይይት በሦስቱ ጉባኤዎች ግንዛቤን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሥራ መሠራቱ ተመልክቷል፡፡ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ሳይንስና ሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ ዲን ዶ/ር ደጀኔ ገመቹ፣ ጉባኤ ከማዘጋጀት ባለፈ ለወደፊት ምን መሠራት እንደሚኖርበት የሚጠቁም ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ከሌሎችም የሚውጣጣ ግብረ ኃይል መቋቋም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ለየት ያለ ሐሳብ ያነሱት ዶ/ር ሙሉቀን በሦስት ዓመት ውስጥ ብዙ ውጤት ለማየት የመጓጓት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፣ ነገር ግን ኅብረተሰቡ በደንብ የተረዳው ስላልሆነ ሰፊ የማስገንዘቢያና የቅስቀሳ ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡
‹‹ለተወሰነ ቡድን ከሚሰጥ ሁሉም እንደባለቤት መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር መፍጠር አለበት፤ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር እንደተካሄደው ዓይነት ሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ከገቡበት ውጤት ሊመጣ ይችላል፡፡ ወደታችም ሁለተኛ ደረጃ መለስተኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም መውረድ አለበት፡፡ ተተኪውን ትውልድ ማስተማር አገር በቀሉን ዕውቀት ለማስተላለፍ ያስችላልና፡፡››
በዓለም አቀፍ ደረጃ ግእዝን የሚመለከቱ እስከ አሥር የሚደርሱ ጆርናሎች በየዓመቱ እንደሚወጡ ያመለከቱት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ የቋንቋ ባለሙያና የጉባኤው አስተባባሪ አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው ናቸው፡፡ ግእዝን የመመርመር አስፈላጊነትና ጠቀሜታ እንዲህ አመላከቱት፡፡
‹‹የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግእዝን ለምን አተኩሮ ያጠናል? እኛስ ለምንድን ነው የማናጠናው? ጥያቄ መሆን ያበት ይኼ ነው፡፡ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ዕውቀት እናምጣ ካልን ከሩቅ ከባሕር ማዶ ከምናመጣቸው ዕውቀቶች ይልቅ፣ ከባህላችን ጋር ተሰናስለው የተፈጠሩ በግእዝ የተጻፉ ሀብቶች አሉን፡፡ እነዚህን ጥንታዊ ዕውቀቶች ፈልፍለን አውጥተን፣ ለዛሬው ኑሮ ሥርዓታችን የመጠቀምና ያለመጠቀም ምርጫ ነው፡፡ ይጠቅመናል ካልን እንመርምረው፣ እንፈትሸው እናውጣው፣ አይጠቅመንም ካልን እንተወው፣ ስለዚህ መጥቀም አለመጥቀሙን ለማወቅ በመስኩ ለተሰማራን የግንዛቤ ሥራ ያስፈልጋል፡፡››
አንዱ ጉባኤተኛም በሦስቱ ዓመታት በአክሱም፣ በባሕርዳርና በጅማ የተካሄዱትን ሦስቱን የግእዝ አዝመራ ጉባኤዎች አያይዘው፣ ‹‹ዓይን ቅንድብን ያየበት›› መድረክ ነው ሲሉ አወድሰውታል፡፡
ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ