በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኘው ጎንደር ከተማ፤ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት ጀምሮ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 ያላነሱ ዜጎች መገደላቸው ተጠቆመ፡፡ መረጃዎች እንደሚመለክቱት ከሆኑ፤ 10 ያህል ንፁሃን ዜጎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ ርምጃ መገደላቸውን ተከትሎ፤ ህዝቡ በወሰደው የአፀፋ እርምጃ 9 የፌደራል ፖሊስ እና 1 የመከላከያ ሰራዊት አባል ተገድለዋል፡፡
በስፍረው የሚገኙ የዓይን እማኞች በበኩላቸው የተገደሉ ሶወች ቁጥር ከተጠቀሰው እንደሚልቅ ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ በግጭቱ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ እስካሁን ከገለልተኛ አካልም ሆነ ከመንግሥት የተሰጠ ማረጋገጫ የለም፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በህዝቡ መካከል በተፈጠረ ግጭት በጎንደር ለሁለት ተከታተይ ቀናት የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደሌሎች አጎራባች ከተሞች መዛመቱ ተሰምቷል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞውም ሐሙስ ወደ ዳባርቅ ከተማ የተዛመተ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ወደ ሳንጃ ወረዳ እና ወደ ሌሎች አጎራባች ከተሞችና ወረዳዎች መዛመቱ እየተነገረ ነው፡፡
በተፈጠረው ግጭትም የሰው ህይወትን ጨምሮ የህወሃት እና የደጋፊው ናቸው የተባሉ ንብረቶች መውደምንም አስከትሏል፡፡
የግጭቱ መንስኤ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የአማራ ማንነትና ተያያዥ መብታቶቻችን ይከበሩልን የሚል ጥያቄን ለትግራይ ክልላዊ መስተዳደርና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲያቀርቡ የነበሩ ተወካይ ኮሚቴዎችን ከሚኖሩበት ጎንደር ከተማ የትግራይ ክልልና የፌደራሉ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና የደህንነት አባላት ለማፈን እና ለማሰር በወሰዱት የኃይል እርምጃ በተፈጠረ አለመግባባት መሆኑ ይታወቃል፡፡
በተለይ ከወልቃይት የአማራ ማንነት ተወካይ ኮሚቴዎች መካከል ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፤ ሊያግቷቸው የመጡ የፀጥታ ኃይሎችን “ህጋዊ ከሆናችሁ በቀን መምጣት ትችላላችሁ፤ ካልሆነ በሌሊት እኔ እጄን ለማንም አልሰጥም” ማለታቸውን ተከትሎ በተፈጠረው አለመግባባት፤ ህዝቡ የመንግሥት ኃይሎችን የሌሊት እገታና ሌሎች 4 የኮሚቴ አባላትን እስርና እገታ በመቃወም ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት እንደተፈጠረ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
በጎንደር በተፈጠረው አለመረጋጋት የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የአሜሪካና የእንግሊዝ መንግሥታት ዜጎቻቸው ወደጎንደርና አቅራቢያው ከመሄድ እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል፡፡ እስራኤል በበኩሏ በጎንደር የሚገኙ 6 ሺህ ቤተ እስራኤላውያንን እና በስፍራው የሚገኙ በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ ተወካዮችን ደህንነት በተመለከተ ከፍተኛ ቁጥጥር ወደሚደረግበት ስፍራ ጥበቃ እያደረገችላቸው መሆኑን የኢየሩሳሌም ፖስት ዘገባ አመልክቷል፡፡
በጎንደር ግጭቱ ለጊዜው የተረጋጋ ቢመስልም፤ አሁንም በአካባቢው በመንግሥትና በህዝቡ መካከል ከፍተኛ ውጥረት መኖሩ እየተገለፀ ነው፡፡