በታሪክ አዱኛ
በኢትዮጵያ ድንበር ስለሚገኙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ኤርትራውያን ስደተኞች እንቅስቃሴ ለኤርትራ መንግስት መረጃ ያቀበሉ ዘጠኝ ግለሰቦች በፅኑ እስራት ተቀጡ።
ተከሳሾቹ 1ኛ ካሃሳ መስፍን፣ 2ኛ አብደላ ኢብራሂም፣ 3ኛ ልኡል መሃሪ፣ 4ኛ ፍስሃይ ተክለገብረስላሴ፣ 5ኛ ጎይቶም ይደጎ ተስፋይ፣ 6ኛ ጎበዘይ ገብረስላሴ፣ 7ኛ ገብረሚካኤል ገብረማርያም፣ 8ኛ ብርሃኔ ምረጽ ይልማ እና 9ኛ ትኩህ ንጉሴ ገብረ መድን ይባላሉ።
ከ1ኛ እስከ 5ኛ ያሉ ተከሳሾች የኤርትራ ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ ከ6ኛ እስከ 9ኛ ያሉ ተከሳሾች ደግሞ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ተከሳሾቹ ከጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም እስከ 2006 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ከኤርትራ መንግስት የመረጃ ሰራተኞች ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት በመፍጠር በኢትዮጵያ ድንበር የሚገኙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የኤርትራ ስደተኞች እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለኤርትራ መንግስት አቀብለዋል ይላል የአቃቤ ህግ ክስ።
በተጨማሪም 2ኛ ተከሳሽ በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም አራት ኤፍዋን ቦምቦችን በአካባቢው ለሚገኙ ግለሰቦች ለመሸጥ ሲዘጋጅ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በተመሳሳይ 8ኛ ተከሳሽም የመሳሪያ ጥይቶችን እና አምስት ቦምቦችን ሸሽጎ መያዙንም ክሱ ያስረዳል።
በዚህም መሰረት አቃቤ ህግ የሃገሪቱን ሚስጥራዊ መረጃ በማቀበል እና ስለላ ወንጀል ክስ መስረቶባቸዋል።
ተከሳሾቹ ድርጊቱን ክደው የተከራከሩ ቢሆንም አቃቤ ህግ የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ኤጀንሲ የሰነድ ማስረጃና የሰው ምስክር አቅርቦ አሰምቷል።
የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎትም ተከሳሾቹን ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
ችሎቱ ከ7ኛ እና ከ8ኛ ተከሳሾች ውጪ ያሉትን ተከሳሾች በ3 አመት ከ4 ወር እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
7ኛ ተከሳሽ የደም ግፊት ህመምተኛ መሆኑን በማስረጃ በማቅረቡ አንድ ማቅለያ ተይዞለት በሶስት አመት ጽኑ እስራት ሲቀጣ፥ 8ኛ ተከሳሸ ደግሞ በአራት አመት ከስድስት ወር እስራትና በ500 ብር እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
በተከሳሾቹ እጅ ላይ የተያዙ ቦምቦች ለመንግስት ገቢ እንዲሆኑ ፍርድ ቤቱ አዟል።
በአጠቃላይ ሁሉም ተከሳሾች ለአምስት አመት ከማንኛውም ህዝባዊ መብታችው እንዲታገዱ ችሎቱ ወስኗል።
ምንጭ፡- ፋናቢሲ (የሐምሌ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ዘገባ), http://www.fanabc.com/index.php/news/item/17450