(አዲስ ሚዲያ) ዛሬ እሁድ ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ መዳረሻውን በጎንደር ፋሲለደስ መስቀል አደባባይ ያደረገ ታላቅ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ፡፡ የተቃውሞ ሰልፉ ዋነኛ ምክንያት ባለፈው ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. የማዕከላዊ መንግሥት የወልቃይት አማራ ማንነት መብት ጥያቄ አንሺ ኮሚቴ አባላት ከሚኖሩበት ጎንደር ከተማ በሌሊት አፍኖ ወስዶ በማሰሩ፣ ከኮሚቴ አባላት መካከልም ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እቤታቸው ሊያፍኑ የሄዱትን የፀጥታ አካላት ህጋዊ ከሆናችሁ በቀን መምጣት ትችላላችሁ፣ በሌሊት ህገወጥነት በሚል በተፈጠረ አለመግባባት የ11 የፅጥታ ኃይሎች እና 3 ሲቪሎች መገደላቸው ይታወቃል፡፡ ይህንንም ተከትሎ መንግሥት የወልቃይት አማራ ማንነት መብት ጥያቄ አቅራቢዎችን እና የፀጥታ ኃይሉ ላይ የአፀፋ ርምጃ የወሰዱትን ጨምሮ የመንግሥትን ርምጃ በማውገዝ እና ተቃውሞ ያቀረቡ የአካባቢውን ህዝብ ወንጀለኛ አድርጉ በሚዲያ በማቅረቡ የተቆጣው ህዝብ፤ ተቃውሞውን በአደባባይ ለማቅረብ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ በመደረጉ ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲወጣ እንዳደረገው ከአስተባባሪዎቹ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከጎንደር ፋሲለደስ ከተማ በተጨማሪ በደቡብ ጎንደር በእስቴ ወረዳ መካነ ኢየሱስ ከተማ፣በምዕራብ በለሳ እና ማክሰኝት ከተማ ተመሳሳይ ጥያቄ መነሻ ያደረገ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉ ታውቋል፡፡ በተለይ በጎንደሩ ሰልፍ የተለያዩ የኃይማኖት አባቶች በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸውን የዓይን እማኞች አረጋግጠዋል፡፡
በዛሬው ተቃውሞ ሰልፍም የተለያዩ መፈክሮች የተደመጡ ሲሆን፤ በዋናነትም የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ሕገ-መንገሥታዊ መብት ነው፣ የሻዕብያ ተላላኪ ህወሃት እንጂ ወልቃይት አይደለም፣ በግፍ የታሰሩ የወልቃይት አማራ ማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በአስቸኳይ ይፈቱ፣…የሚሉትን ጨምሮ በርካታ መፈክሮች እንደተሰሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተቃውሞ፤ ታሪክ ምስክር ነው ወልቃይት አማራ ነው ፣ አማራ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉአላዊነት የተዋደቀ ታላቅ አርበኛ ሕዝብ ነው ፣ ዘረኝነትን አጥብቀን እናወግዛለን ፣ የትግራይን ሕዝብ እናከብራለን፤የህወሓትን አፋኝ የአገዛዝ ፖሊሲ አጥብቀን እናወግዛለን፣አማራነት ይከበር፣ በኦሮሞ እህት ወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል አጥብቀን እንቃወማለን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት ይፈልጋል፣ በኦሮሚያ የሚደረገው በወንድምና እህቶቻችን ላይ ግድያ ይቁም፣ ኢቢሲና ሌሎች መንግስታዊ ሚዲያዎች የጎንደርንና አካባቢውን ህዝብ ይቅርታ ይጠይቁ የሚሉ መሪ ቃሎች ተደምጠዋል፡፡
በተጨማሪም የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ እስኪመለስ ድረስ ትግሉ ይቀጥላል፣አማራነት ወንጀል አይደለም፣ የትግራይ ወሰን ተከዜ ነው፣ ወልቃይት የአማራ ነው ፣ የሐብታሙ አያሌዉ ከአገር የመዉጣት እግድ በአስቸኳይ ይነሳለት፣ ዜጎችን በፖለቲካ አመለካከታቸዉ ማሰርና ማሰቃየት ይቁም፣ በፖለቲካ አመለካከታቸዉ የታሰሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአስቸኳይ ይፈቱ እና የህወሓት የበላይነት ይቁም የሚሉ መፈክሮች ጎልተው ተሰምተዋል፡፡
ይህ ህዝባዊ ተቃውሞ ከሳምንት በፊት እውቅና ተጠይቆ በመንግሥት ተከልክሎ የነበረ ሲሆን፤ በድጋሚ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ቢገባም፤ መንግሥት ለህዝባዊ የተቃውሞ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና አለመስጠቱን ከማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ጋር በኢቢሲ እና ኤፍቢሲ ቢያሳውቅም ህዝቡን ለተቃውሞ ከመውጣት ማገድ አልቻለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት ህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ እውቅና መንፈጉን በስሩ ባለ መገናኛ ብዙኃን ከመግለፁ በተጨማሪ በጎንደር ከፍተኛ የመከላከያ፣ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና የከተማው ሚሊሻ አባላት በበብዛት በከተማው እንዲሰፍሩ መደረጉ ታውቋል፡፡
ተቃውሞ ምንም እንኳ የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄን መነሻ ያድርግ እንጂ፤ ለዓመታት በአማራ ማኀበረሰብ ላይ በመንግሥት በተለይም በህወሓት/ኢህአዴግ አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያየ የኢትዮጵያ ክፍል እየተፈፀመ ያለውን የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ የመብት ጥሰት ተባብሶ መቀጠሉ አንዱ የተቃውሞ አካል መሆኑን የሰልፉ ታዳሚዎች ሲያስተጋቡ ተስተውሏል፡፡
በነበረው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍም፤ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያስከትል በሰላም መጠናቀቁን የተሳታፊዎችን ጨምሮ ዓይን እማኞች እውቅና የነፈገው የመንግሥት አካል አስታውቀዋል፡፡ በሰልፉ ላይም በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን በ25 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በብዛት ሲውለበለብ ታይቷል፡፡