ዘጠነኛ ወሩን ባስቆጠረው የኦሮሚያ ህዝባዊ ተቃውሞ፤ የመንግሥት የግድያ ርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል

(አዲስ ሚዲያ) በኦሮሚያ ክልል ዘጠነኛ ወሩን ያስቆጠረው ህዝባዊ ሰላማዊ ተቃውሞ ላይ መንግሥት እየወሰደ ያለው የግድያ ርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉ ታውቋል፡፡ ዛሬ ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ አወዳይ ከተማ በነበረው ህዝባዊ ሰላማዊ ተቃውሞ 6 ሰዎች በልዩ አልሞ ተኳሽ የፀጥታ ኃይል ሲገደሉ፤ በዊልቸር የሚንቀሳቀስ አካል ጉዳተኛን ጨምሮ 20 ያህሉ መቁሰላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በፀጥታ ኃይሉ ተኩስ የቆሰሉ ሰዎችም በሐረር እና ድሬዳዋ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

Aweday rally
በተመሳሳይም በሐረማያ ህዝባዊ ተቃውሞ መቀስቀሱ የተጠቆመ ሲሆን፤ በተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ታዳሚው ላይ በመንግሥት በተወሰደ ርምጃ ጉዳት መድረሱ ቢነገርም እስካሁን በዝርዝር ለማወቅ አልተቻለም፡፡ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በህዝቡ ላይ የወሰዱትን የኃይል ርምጃ ተከትሎ በተለይ የአወዳይ ከተማ ነዋሪ ከአዲስ አበባ ሐረር እና ጅግጅጋ መንገድን ሙሉ ለሙሉ ዘግቶ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ በዚህ በተገባደደው ሳምንት በምዕራብ አርሲ እና ምዕራብ ሐረርጌን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ የወረዳ ከተሞች ጭምር የተለያዩ ህዝባዊ ተቃውሞች መደረጋቸውና ይህንንም ተከትሎ በቅርቡ ከአዳማ ዩኒቨርስቲ የተመረቀ ተማሪን ጨምሮ ሌሎች ንፁሃን ዜጎችም በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን በመግለፅ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ባለፈው ህዳር 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ጊኒጪ ከተማ ዳግም በተቀሰቀሰው የኦሮሚያ ህዝባዊ ተቃውሞ እስካሁን ከ500 በላይ ንፁሃን ዜጎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን እና በርካቶችም ቆስለው ህክምና ሲከታተሉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ ዘጠነኛ ወሩን ባስቆጠረው በዚህ ህዝባዊ ተቃውሞ ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች እንደታሰሩ የመብት አራማጆች ያስታወቁ ሲሆን፤ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የተለያዩ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞችም ለእስር ተዳርገዋል፡፡

አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በቃሊቲ እና ቂሊንጦ ወህኒ ቤቶች የሚከገኙ የተለያዩ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች በወህኒ ቤቱ አስተዳደርና በሌሎች የፍትህ አካላት እየተፈፀመባቸው ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወም ላለፉት 10 ቀናት የርሃብ አድማ በመምታቸው ራሳቸውን ስተው በጉሉኮዝ እገዛ እንደነበሩ ፍርድ ቤት ከቀረባ አቤቱታ መረዳት ተችሏል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: