በኢትዮጵያ በሁለት ቀናት ብቻ በተቀሰቀሰው የፀረ ጭቆና አገዛዝ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ 132 ዜጎች ተገደሉ

(አዲስ ሚዲያ) በኢትዮጵያ ትናንት ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. እና ዛሬ ነሐሴ 01 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ እና አማራ ክልል በተቀሰቀሰው የፀረ ጭቆና ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል ርምጃ ህፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ንፁሃን ዜጎች ተገደሉ፡፡ በተለይ እንደ መብት አራማጆች እና የአካባቢው ምንጮች መረጃ ከሆነ በሁለቱ ቀን የኦሮሚያ እና አማራ ክልል የፀረ ጭቆና አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ 132 ንፁሃን ዜጎች መገደላቸው ተጠቁሟል፡፡

በተለይ እንደ መብት አራማጆች መረጃ ከሆነ፤መነሻውን የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን በማድረግ ወደ ጠቃላይ ሀገራዊ ይዘት የስርዓት ለውጥ ጥያቄ ያደገው የኦሮሞ ተቃውሞ ትናንት ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል ባሉ ከተሞች አጠቃላይ በተጠራው የረ ጭቆና አገዛዝ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ህፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ 67 ያህል ዜጎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ ወታደራዊ ርምጃ ሲገደሉ፤ ከ500 ያላነሱ በፅኑ ቆስለው በክምና ላይ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት በነበረው የኦሮሚያ ክልል እና የአዲስ አበባ ተቃውሞ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ዜጎች መታሰራቸውም ተጠቁሟል፡፡

Oromo Protest, Adama

በትናንትናው ተቃውሞ በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ግድያ ከተፈፀመባቸው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች መካከል በምዕራብ አርሲ አሳሳ፣ በምስራቅ ሐረርጌ አወዳይ እና ሐረማያ እንዲሁም በምስራቅ ወለቃ ነቀምት ከተሞች ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በነበረው የኦሮሚያ ተቃውሞም የህወሓት መንግሥት በቃን፣ የኦሮሞን ህዝብ መግደል ይቁም፣ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ ይፈቱ፣አሸባሪ አይደለንም፣ አማራ የእኛ ነው፣ የጎንደር አማራዎችን መግደል ይቁም፣ የወልቃይት ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ ነው፣ወያኔ ሌባ፣…የሚሉ መፈክሮች ተሰምተዋል፡፡ በነበሩ የተቃውሞ ሰልፍ ከተሞች እና አካባቢዎች በርካታ ሰዎች መሳተፋቸውን ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዘገባ፣ ማኀበራዊ ሚዲያ እና ከተለያዩ አካባቢዎች ያገኘናቸው የዓይን እማኞች መረጃ ማወቅ ተችሏል፡፡

በተመሳሳይም በአማራ ክልል በተለይም በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦር ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በተጠራው የፀረ ጭቆና አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ ላይ መንግሥት በወሰደው ወታደራዊ የኃይል ርምጃ ከ6 ያላነሱ ሰዎች ወዲያው ሲገደሉ በርካቶች በመቁሰላቸው፣ በሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ ወረዳዎች እና በደቡብ ጎንደር ጋይንት ጨምሮ የተለያዩ ወረዳቸዎች ነዋሪዎች በመቆጣት በድንገት የተቃውሞ ሰለፍ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ መነሻውን የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ በማድረግ ወደ አጠቃላይ የስርዓት ለውጥ ጥያቄ ያደገው የአማራ ተቃውሞን ተከትሎ መንግሥት ከደብረ ታቦር በተጨማሪ የተቃውሞ ሰልፎች በነበሩበት ስፍራዎች ሁሉ ወታደራዊ የኃይል ርምጃ በመወሰዱ የህዝቡ ቁጣ ተባብሱ የህወሓት ደጋፊና ተባባሪ ናቸው የተባሉ የንግድ ተቋማት፣ የመንግሥት ተሸከርካሪዎች እና ተቋማት ላይ እንዲሁም በጎንደር አዘዞ የሚገኘውን የመከላከያ ወታደራዊ ካምፕ ከጥቅም ውጭ ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡

በሰሜን ጎንደር ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ በሰሜን ጎንደር ሳንጃ፣ ቆላ ድባ፣ ዳባት፣ አርማጭሆ፣…በመሳሰሉ ቦታዎች በመንግሥት ወታደሮች እና በህዝቡ መካከል ውጊያ መኖሩን እና የመንግሥት ወታደሮችን እና ከህዝቡም በርካታ ሰዎች መሞታቸውን እና መቁሰላቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ነሐሴ 01 ቀን 2008 ዓ.ም. በባህርዳር ከተማ በነበረው የአማራ የፀረ ጭቆና ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ከ30 ያላነሱ ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ታውቋል፡፡ በአማራ ክልል ዛሬ የተገደሉ 30 ያህል እና ትናንት ደብረ ታቦር ከተገደሉ 6ቱ በተጨማሪ ሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች በተደረገ የትናንት እና የዛሬ ተቃውሞ 29 ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተጠቁሟል፡፡ ህዝቡም በባህርዳር የተለያዩ ህዝባዊ ተቋማት ሰንደቅ ላይ የብአዴን እና በኢህአዴግ የፀደቀውን የፌደራሉን ሰንደቅ ዓላማ በማውረድ የቀድሞውን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቅሉ እና ሲያውለበልቡ ተስተውሏል፡፡ በአጠቃላይ በሁለቱ ቀን የአማራ ክልል ተቃውሞ 65 ያህል ዜች ሲገደሉ፤ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ዜጎችም መቁሰላቸውን እና የህክምና ርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን የዓይን እማኞች አረጋግጠዋል፡፡

AmharaProtest, Bahirdar

በተለይ በደብረ ታቦር እና ባህርዳር በተደረገው የአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ፤ ወልቃይት የአማራ እንጂ የትግሬ አይደለም፣ ወልቃይት አማራ ነው፣ ለሱዳን የተሸጠው መሬታችን ይመለስ፣ የታሰሩት ይፈቱ፣ በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ የሚደረገው ግድያ ይቁም፣ በቀለ ገርባ መሪያችን እንጂ አሸባሪ አይደለም፣ ኢትዮጵያዊነት አሸባሪነት አይደለም፣በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ አንደራደርም፣ወያኔ ሌባ፣አንዳርጋቸው ጽጌ መሪያችን እንጂ አሸባሪ አይደለም፣ የህወሓት አገዛዝ በቃን፣ ግድያ ይቁም፣….የሚሉ መፈክሮች ተሰምተዋል፡፡

በኦሮሚያ እና አማራ ክልል እየተካሄደ ባለው የፀረ ጭቆና አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ በርካታ መረጃዎች በመታፈናቸው በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ ወታደረዊ የኃይል ርምጃ የተገደሉ እና የቆሰሉ ዜጎች ቁጥር ከተጠቀሰው ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል፡፡

በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል በነበሩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በጠፋው የሰው ህይወት እና በወደሙ ንብረቶች ዙሪያ እስካሁን ከገለልተኛ አካል የተጣራ ይፋ ማብራሪያም ሆነ መግለጫ የለም፡፡ ይሁን እንጂ በሁለቱም ክልሎች ባሉ በርካታ ወረዳዎችና ከተሞች ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ አለመረጋጋቱ እንደቀጠሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

Leave a comment