ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com
መሬት ለኢትዮጵያውያን የሕልውና ጉዳይ ነው። አገሪቱ ከመንግሥት ስርዓት ጋር ከተዋወቅችበት ከክ.ል.በ. 2545 ጀምሮ ለነገሥታቱም ይሁን ለቀሪው ዜጋ መሬት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነበር። የመሬቶቹ ባለቤትነትም ከመደበኛው ከነዋሪው ይልቅ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የገዥው መደብ አባላት እና አጋሮቻቸው እንጂ የአራሹ ሆኖ አያውቅም ነበር። ይህ መሬት ለየአካባቢው የጭፍራ አለቆችም ሆነ ለመኳንንቱ የርስበርስ መቃቃርና ግጭት ዋነኛ ምክንያት ነበር። ይህ ሁሉ ታሪክ በሀገሪቱ ዘመናዊ የመንግሥት ስርዓት መሥራች በነበሩት ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ አማካኝነት በተወሰነ ደረጃ ለውጥ የታየበት ቢሆንም፤ ሕጋዊና ሁሉንዐቀፍ አልነበረም።
በተለይ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ከመኳንንቱ በተጨማሪ በርካታ ሰዎች መሬትን ለማግኘት ከቤተክርስቲያን ይጠጉም ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣው ኋላ ቀር የመሬት ይዞታ ፊውዳላዊ ስርዓት በዐፄ ቴዎድሮስ ስላልተወደደ፣ በዜጎች መካከል ከመሬት ጋር በተያያዘ የነበረው የገዥና ተገዥ ስሜት ያበቃ ዘንድ የመኳንንቱን እና በክሕነት ሥም በየቤተክርስቲያኑ ተጠግተው በርካታ መሬቶችን በመያዝ ገበሬውን ያንገላቱ የነበሩ ባላባቶች ሁሉ አብዛኛው መሬቶቻቸው እየተወሰደ መሬት ለሌለውና ሲያርስ ለነበረው እንዲከፋፈል፤ በቤተከርስቲያንም የሚያገለግሉ ካሕናት ቁጥር ውስን እንዲሆን እና ቀሪዎቹ ወደ ግብርና ሥራ እንዲገቡ አዘዙ። ይህ ሁሉ የነበረው በዛው በጎንደርና አቅራቢ አጎራባች አካባቢ በነበሩት ወሎ፣ ጎጃምና ትግራይ እንጂ በሌላ የአገሪቱ አካባቢ በገዥ ሥም ባሉ የጎበዝ አለቆች የተለመደው የመሬት ብዝበዛ ሲያከናወን ነበር። የተጠቀሱ ቦታዎችም ቢሆኑ የተሳካ ወጥ የመሬት ክፍፍልና አዋጅ ተፈፃሚ አልሆነም፤ ምክንያቱም የነበረው ስርዓት የተረጋጋና በሰነድ የታገዘ አልነበረም።
በመጨረሻም በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1966 ዓ.ም. በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ የዜጎች በተለይም የገበሬዎች የመሬት ባለቤትነት መብት ይረጋገጥ ዘንድ በይፋ ጥያቄ መቅረብ ጀመረ። ከዓመት በኋላም ለዓመታት የሕዝቡ ጥያቄ የነበረው የመሬት ባለቤትነት መብት ከዘውዳዊ ስርዓት ስንብት ጋር አብሮ ተበሰረ። ይህ የመሬት ባለቤትነት መብት በተለይም የ“መሬት ላራሹ” መብት ጥያቄ የካቲት 25 ቀን 1967 በዘመነ ደርግ ምላሽ አገኘ። ያ ወቅት ለኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ከፋች ነበር። ምክንያቱም ለረጅም ዘመናት መሬት የኢትዮጵያውን የመብትም የሕልውና ጥያቄ ነበርና። ያ አዋጅም ሆነ የተማሪዎች ጥያቄ ትኩረት የእርሻ መሬት ላይ እንጂ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ በነጻነት በእንሰሳት እርባታ የሚተዳደሩትን በተመለከተ ነበር ለማለት አያስደፍርም። ምክንያቱም ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ በእንስሳት እርባታ ይተዳደሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን መሬታቸውን ማንም ከልካይና የሚቀማ ወይም የባለቤት መብት የነፈጋቸው አካል አልነበረም። በተለይ አርብቶ አደሮች የመሬት እና የውኃ ሀብትን በሚመለከት በአነስተኛ ደረጃ እርስበርስ ከሚኖራቸው አለመግባባት በስተቀር የሚንቀሳቀሱበት ቦታ ሁሉ በነጻነት የሚጠቀሙና የባለቤትነት መብቱም ቢሆን ቢበዛ በጎሳ ይሆን እንጂ እንደ እርሻው መሬት በመኳንንቱና በመንደር የጎበዝ አለቆች ባለቤትነት የሚተዳደር አልነበረም።
ዛሬ ግን ሁሉም ነገር ተቀይሯል። የካቲት 25 ቀን 1967 የታወጀው የመሬት ላራሹም ሆነ የመሬት ባለቤተነት መብት ከሕዳር 1987 ጀምሮ በዘመነ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ ተሽሯል። የመሬት ባለቤትነት በእርሻ፣ በእንስሳ እርባታ እና በከተማ ኑሮ የሚተዳደረውን ሁሉ መብት ነው የቀማው። ምክንያቱም የግለሰብ የመሬት ባለቤትነት መብት መነጠቁን 4ኛው እንደሆነ በሚነገርለት የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀፅ በግልጽ አረጋግጧል። በዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ‹የንብረት መብት› በሚለው ሥር ንዑስ አንቀፅ 3 “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት እና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው። መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው” ይላል።
እዚሁ አንቀፅ ላይ በንዑስ አንቀፅ 6 የመሬት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ‹ለግል ባለሀብቶች በሕግ በሚወሰን ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል› ይላል። በንዑስ አንቀፅ 4-5 “የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመነቀል መብታቸው የተከበረ ነው። የኢትዮጵያ ዘላኖች ለግጦሽም ሆነ ለእርሻ የሚጠቀሙበት መሬት በነጻ የማግኘት፣ የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብት አላቸው። ዝርዝር አፈፃፀሙ በሕግ ይወሰናል” ይላል።
በመጀመሪያ ደረጃ ሕገ መንግሥቱም ሆነ ሕጉን ያወጡት እና ያፀደቁት እንዲሁም አገሪቱን እየመሩ ያሉ አካላት ሊመልሱት ያልቻሉት፤ ነገር ግን ሊመልሱ የሚገባቸው በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል። ከነዚህም መካከል፦
‹መንግሥት እና ሕዝብ የሚባለው ማነው የሚለው ግልጽ አይደለም። ሌላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚል የቃላት ክምር ልዩነታቸውና አንድነታቸው (ካለ) ምንድነው? እነሱስ እነማን ናቸው? በማንስ ይወከላሉ፣ መብቶቻቸውና ግዴታቸውስ? የሚሉ ጥያቄች እስካሁን በየትኛውም ሕዝባዊ መድረክም ሆነ የመንግሥት ሕጋዊ መዝገበ ቃላት ፍቺም ሆነ ትርጉም ያልተሰጣቸው፤ ግን ደግሞ መልስ የሚያሻቸው ናቸው። ምክንያቱም በድፍኑ የቃላት ድርደራ ከመሆን በዘለለ ለሕዝቡ በሚገባ መልኩ በግልጽ የተቀመጠ ትርጉም የለውም።
ሌላው መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ… የጋራ ንብረት ነው ይልና ወረድ ብሎ ደግሞ መንግሥት ለግል ባለሀብቶች በሕግ በሚወሰን ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል ይላል። ይህ የሚያሳየው የማይሸጥ የማይለወጥ የተባለው መሬት መንግሥት መሬት ቸርቻሪ እንዲሆን መብት ሰጥቶታል። አሁን ባለው በሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ መንግሥት የሚለውም ትርጉም የሚያስፈልገው ዐብይ ጉዳይ ነው። በአንቀፅ 40 (7-8) ላይ ደግሞ ዜጎች የግል ንብረት ባለቤትነት መብት ያላቸው በመሬቱ ላይ በሚገነቡትና በቋሚነት ለሚያሻሽሉት ቁስ እንጂ መሬቱ ላይ የባለቤትነት መብት እንደሌላቸው ያመለክታል። ይህም ከቦታው በግድ የሚፈናቀል ሰው ካሳ እንኳ ቢያስፈልገው፤ በመሬቱ ሳይሆን መሬቱ ላይ ባለው የተጠቃሚነት መብት ባፈራው ንብረት ብቻ መሆኑን ያመለክታል።
የመሬት ባለቤትነት መብት ያለመኖር ያስከተለው ችግር
በርግጥ ሕገ መንግሥቱ ሥራ ላይ ባያውላቸውም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲና ሰብኣዊ መብት ድንጋጌዎችን ያካተተ ቢሆን ግልጽ ያልሆኑ፣ ጥያቄ የሚያስነሱ በርካታ ግግር ጉዳዮችንም ይዟል። ይበልጥ ግን የገዥውን ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. በተለይም የሕ.ወ.ሓ.ት.ን የፖለቲካ ፕሮግራምና ፍላጎት በስፋት ይገኝበታል። ለዚህም ይመስላል፤ ሕገ መንግሥቱ ከተወሰኑ አንቀፆች (ላለፉት 21 ዓመታት ሥራ ላይ ያልዋሉ) ዓለምዐቀፍ ድንጋጌዎች በስተቀር የሕ.ወ.ሓ.ት./ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. የፖለቲካ ፕሮግራምና ፍላጎት የሰፈረበት ሰነድ ነው የሚል ጥያቄ የሚነሳው። በተደጋጋሚ ከሚነሱ ጥቄዎችና ቅሬታዎች መካከል የመሬት ጉዳይ ዋነኛው ነው።
በተለይ ሕ.ወ.ሓ.ት. መሬትን በተመለከተ የሚከተለው የፖለቲካ ፕሮግራም (ፖሊሲ) እና ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረው አንድ ነው። ከሕ.ወ.ሓ.ት. ውጭ ያሉ ሌሎቹ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. አባላት (ብ.አ.ዴ.ን.፣ ኦ.ሕ.ዴ.ድ. እና ደ.ኢ.ሕ.ዴ.ን.) የተሰጣቸውን ከማስፈፀም በቀር የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ተመሳሳይ ከማድረግ ውጭ ሥልጣኑም ሆነ ሞራሉ ያላቸው አይመስልም። አጋር ድርጅቶች የተባሉት የጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሶማሌ፣ አፋር እና ሐረሪ ክልል ፓርቲዎች ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.ን. ከማጀብና የሚለውን ከመቀበል ውጭ በየትኛውም አገራዊ ጉዳይ ላይ የመወሰን፣ የመጠየቅም ሆነ ላሉበት ማኅበረሰብ መብትና ጥቅም የመቆም ሕልውናም ሆነ አቅም የላቸውም። ምክንያቱም አጋር እንጂ የገዥው ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. አባል ስላልሆኑ የተሰጣቸውን ሥራ ከማከናወን ባለፈ በፖሊሲም ሆነ በፖለቲካ ፕሮግራማቸው የተለየና የራሳቸውን ነገር ይዘው መቅረብ አይችሉም። በዚህም ምክንያት ከመሬት ባለቤትነት መብት ጋር በተያያዘ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው አልቀረም።
በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በፌደራሉ መንግሥት ፍላጎትና ሥልጣን ሰፋፊ ለም የእርሻ መሬቶች ከገበሬዎቹ በግድ ተነጥቀው ለባለሀብቶች እንዲተላለፉ ተደርገዋል። ከባለሀብቱ በተጨማሪ ስርዓቱ ለሚከተለው መንግሥታዊ ባለሀብትነት (state capitalism) ትግበራ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ከገበሬዎች ነጥቋል። ይሁን እንጂ ከገበሬዎች ያለምንም አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ (Environmental and social impact assessment) ሰፋፊ ለም መሬታቸው ወደ መንግሥታዊና ግል ባለሀብቶች በመተላለፉ አንዳቸውም ፕሮጀክቶች ውጤታማ አልሆኑም። ይልቁንም ያለበቂ ምክክር፣ ካሣና ምትክ ቦታ የተፈናቀሉ በርካታ ገበሬዎች ዛሬም ድረስ ሕይወታቸውን በጉስቁልና እንዲመሩ አስገድዷቸዋል። ከገበሬዎች ማኅበራዊ ችግር በተጨማሪ በአካባቢያዊ የአየር ጠባይ እና የአየር ንብረት ላይ የሚኖረው ጉዳት አገሪቱ በቀላሉ የምታካክሰው አይደለም። ይህ ሁሉ በሕገ መንግሥቱ የሰፈረው የመሬት ባለቤትነት መብትና ስርዓቱ የሚከተለው የመሬት ፖሊስ ምክንያት የተፈጠረ ችግር ነው።
በሰንጠረዡ ላይ እንደሚታየው በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ እና ቤንች ማጂ ዞን አካባቢ ለስኳር ፕሮጀክት መንግሥት የወሰደውን 335,000 ሔክታር መሬት፣ የወልቃይት፣ የከሰም፣ የተንዳሆ ሰፋፊ እርሻዎችን፣ 2,000 ሔክታር እና ከዛ በታች ስርዓቱ የኔ ለሚላቸው ሰዎች የሰጠውን ሳያካትት ነው። መሬቱ ለግል ባለሀብቶች የተላለፈው ከ30-50 ዓመት በሚቆይ ኪራይ ነው። በዚህም ምክንያት በአንድ ሔክታር በዓመት ከ14-135 ብር የሊዝ ኪራይ የተላለፉና መንግሥት በነጻ የወሰዳቸው መሬቶች ላይ የኖሩ ዜጎች ያለ በቂ ምክክር፣ ካሣና ምትክ ቦታ ተፈናቅለዋል። በተለይ በጋምቤላ ክልል ብቻ 225 ሺሕ ዜጎች ሲፈናቀሉ፣ ከ8-10 ሺሕ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ደግሞ አገር ጥለው ሲሰደዱ፤ ከ424 ያላነሱ ተገድለዋል። በተመሳሳይ በደቡብ ክልል በሚገኘው ደቡብ ኦሞ ዞን 200 ሺሕ ያህል ዜጎች ተፈናቅለዋል።
መንግሥት ለስኳር ልማት፣ ለማዳበሪያ ፋብሪካና ተያያዥ ግንባታዎች ልማት በሚል የወሰዳቸው ሰፋፊ ለም የእርሻ መሬቶችና ለግል ባለሀብቶች ከተላለፉት ውስጥ ለአገሪቱም ሆነ ለዜጎች ያመጡት ጥቅም የለም። ከጥቅማቸው ይልቅ በተለይ በምዕራብና ደቡብ ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ደኖችና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። ይህም ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ካስከተለው ችግር በተጨማሪ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እና አካባቢ ጥበቃ ላይ ያስከተለው ጉዳት ቀላል የሚባል አይደለም። እዚህ ላይ በቅርቡ የገባበት ያልታወቀውን 77 ቢሊዮን ብር የስኳር ልማት ፕሮጀክት ገንዘብ እና የኢሉ አባቦራ ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ የደን ጭፍጨፋን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።
ሌላው ችግር ባለሀብቶች ውጤታማ መሆን ባልቻሉበት መሬት ላይ የተጠቀሟቸው ኬሚካሎች በተፈጥሮ ሀብት ላይ በተለይም በአፈሩ፣ በውሃውና በአካባቢው አየር ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደቀላል የሚታይ አይደለም። ገበሬው መሬቱን በሚመለከት ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎችም ሆኑ ቅሬታዎች ከመንግሥት ወገን የሚሰጠው መልስ “መሬት የመንግሥት ነው፤ ወደህ ሳይሆን ተገደህ ትነሳለህ” የሚል ሲሆን፤ ያለበቂ ካሳና ምትክ ቦታ ከቀዬያቸው መፈናቀላቸውን የተቃወሙ ደግሞ የእስርና ግድያ ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይሄ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የመሬት ሕጉና ፖሊሲው ካስከተሏቸው ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
በከተማው ያለው የመሬት ችግር ከገጠሩ እጅጉን የባሰ ሲሆን፣ ሕዝቡ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የስርዓቱ ጥገኛ እንዲሆን ካስገደዱት ነገሮች መካከል የመሬት ሕጉና ፖሊሲው ዋነኞቹ ናቸው።
‹መሬት አይሸጥም አይለወጥም›፣ ‹የመሬት ፖሊሲው የሚቀየረው በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መቃብር ላይ ነው›… የሚሉ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መፈክሮች ይበልጥ የሚሰሙት በከተማ ነው። ምንም እንኳ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ቢባልም የአገሪቱን የከተማ መሬቶች እንደጉሊት ንግድ በአደባባይ የሚቸረችረው ደግሞ ራሱ መንግሥት መሆኑን ላስተዋለ፣ መሬትን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውና የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ፖሊሲ እርስበርስ ሲጋጭ ይታየዋል። ከዛም አልፎ የሕጉና የፖሊሲው ዓላማ እንዲሁ በቀላሉ እንደተራ ነገር በትዝብት የሚያልፍ ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱም መሬት ለኢትዮጵያውን መነሻ ካፒታል ብቻ ሳይሆን፣ የሕልውና ጉዳይም ነው። ነገር ግን አሁን የመሬት ጉዳይ ሌላ አብዮት የሚናፍቅ ጉዳይ የሆነ ይመስላል። አለበለዚያ በተለይ ሰፋፊ ለም የእርሻ መሬት ያለባቸው አካባቢዎች፣ በከተማ የሚኖሩ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች እንደሰው የመቆጠራቸውም ጉዳይ ጥያቄ የሚገባ ይመስላል። ምክንያቱም በከተሞች ያለው የመሬት የሊዝ ጨረታ ዋጋ እንኳን በወር ደመወዝ በተቋማት ተቀጥሮ የሚተዳደር ቀርቶ በቂ ገንዘብ አለው የሚባለውን ነጋዴውንም ቢሆን እጅግ የሚፈታተን ጉዳይ ሆኗል። ይህ ታቅዶ፣ ዓላማና ግብ ኖሮት የሚፈፀም ያልተጻፈ ፖሊሲ አካል እንጂ በድንገት እየተከናወነ ያለ የሚመስለው ካለ ተሳስቷል።
ከሊዝ ጨረታ ውጭ አዲሱ ትውልድም ሆነ ከዚህ በፊት የራሳቸው መኖሪያ ቤት የሌላቸው ዜጎች የከተማ መኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ የማግኘት ዕድላቸው ሙሉ ለሙሉ ከስሟል። በዚህ ምትክ መንግሥት ለፖለቲካ ፍጆታ የሚጠቀምበትን ኮንዶሚኒየም ቤት ደስ ባለው ሰዐትና ራሱ በተመነው ዋጋ ለዓመታት በተስፋ በመጠበቅ የከተሜው ነዋሪ ግዴታ መሆን ከጀመረ እነሆ 10 ዓመት አልፎታል።
በተለይ ከሊዝ አዋጅ በተያያዘ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ 721/2004 መሠረት አይደለም መሬት በሊዝ ጨረታ መግዛት በውርስ ያገኘው የቤተሰብ ንብረትም ሆነ በቀድሞ ስርዓት ሠርቶ የቤት ባለቤት የነበረ ሰው መንግሥት በፈለገው ጊዜ እንደሚያስነሳው፣ ካሣውን የሚተምነው ለተሠራው ቤት ጣሪያና ግድግዳ እንጂ ለመሬቱ እንዳልሆነ በግልጽ አስቀምጦታል።
በተለይ ከከተማ ቦታ ይዞታ ጋር በተያያዘ ቤት ያለአግባብ የፈረሰበት ወይም መብቱን የተነጠቀ ማንኛውም ግለሰብ በከተማ አስተዳደሮቹ ውሳኔ ቅር ቢሰኝ እንኳ ወደፍርድ ቤት ሄዶ አቤቱታ ማቅረብ አይችልም። ምክንያቱም የከተማን ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ 721/2004 መሠረት፤ ከተማ አስተዳደሩ 5 አባላት ያሉት ራሱ ፖለቲከኛው የመረጠውና የሾመው የጉባዔ አባላት አቋቁሞ እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል። ለዚህም በአንቀፅ 30 (8-9) “ጉባዔው ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ በመደበኛው የፍትሐብሔር ሥነ ስርዓት ሕግ አይመራም። ሆኖም በክልሉ ወይም በከተማ አስተዳደሩ በሚወሰን የተቀላጠፈ ሥነ ስርዓት ይመራል። የጉባዔው አባላት የሥራ ዘመን በክልሉ ወይም በከተማ አስተዳደሩ ይወሰናል” በሚል ያስቀመጠውን መረዳት ይቻላል።
በዚህ የሊዝ አዋጅ መሠረት፤ አንድ የከተማ አስተዳደር አካል የሆነና በፖለቲካ የተሾመ ሰው ከመሬት ይዞታ መፈናቀልና መብት ጋር በተያያዘ የትኛውንም በደል ወይም ጥፋት ቢፈፅም፤ ጉዳዩን የሚያየው ጥፋት የፈፀመው የአስተዳደር አካል የሾመው ሌላ የባለሥልጣናት ስብስብ “ጉባዔ” መሆኑ ችግሩን የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል። ይህም መሬት የስርዓቱ የፖለቲካ መቆመሪያ መሣሪያ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ምናልባት ቤት ንብረት ኖሯቸው መንግሥት በፈለገው ሰዐት ለፈለገው ግለሰብ በስጦታም ይሁን በሊዝ ጨረታ መስጠት ቢፈልግ፤ ከይዞታዬ አልነሳም፣ የካሣ ክፍያውም ሆነ የተሰጠኝ ምትክ ቦታ (ዕድለኛ ሆኖ ከተሰጠው) በቂ አይደለም ቢል፣ አስተዳደሩ የፈለገውን ቤት በፖሊስ ኃይል እንዲፈርስ ማድረግ እንዲችል ሥልጣን ሰጥቶታል።
የመሬት ባለቤትነት መብት ችግር መፍትሔ
የመሬትና የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት የተለያዩ መፍትሔዎችን ማንሳት ይቻላል።
ሕገመንግሥቱ አንቀፅ 40 ላይ የዜጎችን የመሬት ንብረት ባለቤትነት መብትን የሚነጥቁ ድንጋጌዎች መሻሻል አለባቸው። የሚሻሻሉት ድንጋጌዎችም በማያሻማ መልኩ በግልጽ መቀመጥ አለባቸው። በተለይም መንግሥት፣ ሕዝብ፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚሉ የቃላት ድርድሮች ልዩነታቸውና አንድነታቸው (ካላቸው) በግልጽ መቀመጥና መለየት አላስፈላጊ ድግግሞሽ ወይም የትርጉም አቻ ያላቸው ቃላት መወገድ አለባቸው። በመቀጠልም መሬት በነዋሪዎች ይዞታ ሥር ያለ የከተማም ሆነ የገጠር መሬት የንብረት ባለቤትነቱ ለራሱ ለግለሰቡ መሰጠት አለበት። መንግሥትም ሆነ የግል ባለሀብቶች የነዋሪዎቹን መሬት ለተለያየ ፕሮጀክቶች ቢፈልጉ በወቅቱ የመሬትና ተያያዥ የንብረት ዋጋ በቀጥታ ከግለሰቡ ጋር ተደራድረው መግዛት አለባቸው። በዚህም ነዋሪው መሬቱን እንደካፒታል በመጠቀም ይንከባከባል፣ ያለማል፣ ቢሸጥ እንኳ ምትክ ቦታ ገዝቶ ቀሪውን ገንዘብ እንደችሎታው የፈለገውን መጠነኛም ሆነ ዝቅተኛ ኢንቨስትመንት ማካሄድ ይችላል። ለዚህ ደግሞ በንብረቱ ላይ ራሱ እንዲወስን ሙሉ ሥልጣኑ ሊኖረው ይገባል።
በሕዝብ የተያዙ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬቶች የንብረት ባለቤትነቱ የአካባቢው ነዋሪ ሕዝብ መሆን አለበት። የአካባቢው ነዋሪ ሕዝብ ሲፈልግ ለልጆቹ መዝናኛ አሊያም ለግጦሽም ሆነ ለሚፈልገው የልማት ፕሮጀክት ማዋል ይችላል። ምናልባት የአካባቢውን ክፍት መሬት መንግሥት ወይም የግል ባለሀብት የሚፈልገው ከሆነ በወቅቱ የመሬት ገበያ ዋጋ ከአካባቢው ነዋሪ ማኅበረሰብ ጋር ተደርድሮ መግዛት ይችላል። መሬቱን የሸጠው የአካባቢው ማኅበረሰብም ገንዘቡን ወደሌላ የገቢ ምንጭ እንዲቀይሩ መንግሥት በነጻ የማማከርና የሙያ ድጋፍ ማድረግ ይችላል፤ ካልሆነ ራሱ ማኅበረሰብ በባለሙያ አስጠንቶ የመረጠውን ሥራ ማከናወን እንዲችል መደረግ አለበት።
በግለሰብም ሆነ በማኅበረሰብ ያልተያዙ መሬቶች የንብረት ባለቤትነት መብቱ ለመንግሥት ቢሆን፤ መንግሥት ለግል ባለሀብቶችም ሆነ ለተለያዩ ማኅበራዊ ተቋማት ግንባታ ወይም ለመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች ማዋል ከፈለገ ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ ለሕዝብ ይፋ ተደርጎ ጥቅም ላይ መዋል አለበት። ነገር ግን ጥቅም ላይ የሚውሉ መሬቶች መጪውን ትውልድ ደኅንነትና የተሻለ ሕይወት ከግምት ያስገባ ሆኖ፣ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነጻ በሆነ መልኩ ባለሙያዎች የአካባቢ ጥበቃና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናትና ምክር ቢያደርጉ፣ ሕዝቡ በሥራው ላይ በዕውቀት፣ በገንዘብም ሆነ በጉልበት ተሳታፊ እንዲሆን፤ ካልሆነ የሞራል ድጋፍ እንዲሰጥ መመቻቸት አለበት።
የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ መሻር ወይም መሻሻል አለበት። ምክንያቱም አዋጁ የግለሰብ የመሬት ንብረት ባለቤትነትን መብት ከመንጠቁ በተጨማሪ መንግሥት ከመደበኛው ሥራው ውጭ የመሬት ቸርቻሪ፣ ካድሬዎችን የሥልጣን መባለጊያ እና የሙስና ምንጭ፣ ለስርዓቱ የመጨቆኛ መሣሪያ፣ ሕዝቡን ደግሞ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጥገኛ እንዲሆን አስችሎታልና።
ሰፋፊ ለም የእርሻ መሬቶችን በርካሽ ዋጋ ለውጭ ባለሀብት መስጠት የሚያስከትለውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ (የአገር ውስጥ የባንክ ብድር ወስደው ስለማይከፍሉ)፣ የማኅበራዊ እና የአካባቢ ጥበቃ ችግር ለመቅረፍ የአገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ላይ ትኩረት መደረግ አለበት። በተለይ በአገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ የግብርና ሳይንስና ተያያዥ ባለሙያዎች በራሳቸው ፈቃድና ተነሳሽነት ተደራጅተው ዘመናዊ የግብርና ሥራን እንዲጀምሩ የባንክ ብድርን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች ቢደረግላቸው። ምክንያቱም የአገር ውስጥ ባለሙያዎች በግብርና ምርትና ንግድ ዘርፍ ቢሰማሩ፣ የአገሪቱን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ በተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠርም ሆነ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት እንዲሁም ፕሮጀክቱን በሚያከናውኗቸው አካባቢ ያሉ ማኅበረሰብን ሕይወት ለማሻሻል እጅግ የተሻሉ ናቸው።
የከተማ ቦታን በሚመለከት መንግሥት ከመሬት ችርቻሮ ወጥቶ የመንግሥትን ሥራ ብቻ እንዲሠራ ቢደረግ፤ የከተማ ነዋሪዎች ራሳቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን በሚፈልጉት የሙያ ማኅበርም ሆነ መሥሪያ ቤት ወይም ተቋም ዘመናዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ሠርተው እንዲኖሩ መደረግ አለበት። መሬትም ከሊዝ ነጻ ቢመቻችና የመኖሪያ ቤት ግንባታን ሊያግዝ የሚችል በረጅም ጊዜ የሚከፈል የባንክ ስርዓትና ብድር ቢመቻች፣ መንግሥት ግንባታዎቹ የከተማውን ደረጃ በጠበቀ መልኩ አካል ጉዳተኞችን እና የአደጋ ጊዜ መከላከልን ታሳቢ ያደረጉ ግንባታዎች እንዲከናወኑ ወጥነት ያለው መመሪያ ቢያዘጋጅና መሠረተ ልማቶችን በማመቻቸት ብቻ ቢሳተፍ አሁን ያለውን እና ከዚህ በኋላ የሚኖረውን የቤት ችግር ለመቅረፍ ይረዳል። ከዛ በተጨማሪ በግላቸው ቤት መሥራት ለሚፈልጉና ለሚችሉ መንግሥት የግንባታ ደረጃዎችን በማውጣትና በተመጣጣኝ ዋጋ ነጻ መሬት ቢያቀርብ፣ መንግሥት ነጻ መሬት ማቅረብ ካልቻለ፣ ግለሰቦቹ ከሌሎች ነባር ነዋሪ ከሆኑ የመሬት ባለቤቶች ራሳቸው በቀጥታ ተደራድረው ገዝተው እንዲገነቡና እንዲኖሩ ቢደረግ ሁለቱም አካላት ተጠቃሚ ይሆናሉ።
መንግሥትም ከዜጎች በሚሰበስበው ግብርና በዜጎች ሥም ከሚያገኘው ብድርና ዕርዳታ የመሠረተ ልማትና ማኅበራዊ ተቋማትን በመገንባት ብቻ እንዲሳተፍ መደረግ አለበት። በግላቸውም ሆነ በማኅበር ተደራጅተው መሥራት ለማይችሉ በመንግሥት ድጎማ እንደየአቅማቸው እንዲደራጁና እንዲመዘገቡ በማድረግ ለግል የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በጨረታ እንዲሠሩ ቢደረግ፣ የሚሠሩ ግንባታዎች ደረጃ ላይም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ቢደረግ፣ የግል የመኖሪያ ቤት ግንባታ ተቋራጭ ድርጅቶች (ሪል ኢስቴቶችም) መሬት በመጠኛ ዋጋ እንዲያገኙ መደረግ አለበት። ድርጅቶቹም በወቅቱ ተመጣጣኝ የገበያ ዋጋ ለቤት ፈላጊዎች እንዲያስተላለፉ ቢደረግ፤ ለዚህም የቤት ግንባታን ብቻ ለማገዝና ለመደጎም የሚችል የባንክ ተቋምና ስርዓት ቢመሠረት ያለውን የቤት ችግር በቶሎ መቅረፍ ይቻላል። መንግሥትም የመኖሪያ ቤት ችግርን የፖለቲካ ፍጆት ከማድረግ ያግደዋል፤ የመንግሥት ግዴታ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት በግልፅ እንዲሰፍን ያግዛል የሚል እምነት አለኝ።
በአዲስ አበባ አራዳ ፒያሳን ጨምሮ ከ10 ዓመት በላይ ታጥረው ምንም ዓይነት ግንባታ ያልተከናወነባቸው በርካታ ቦታዎች እያሉ የአቅማቸውን ያህል በከተማ ጥጋጥግ ጎጆ ቀይሰው የሚኖሩ ዜጎችን ክረምት ጠብቆ ለጎዳና ሕይወት መዳረግ በየትኛውም መመዘኛ ተገቢ ሊሆን አይችልም። ቢቻል በክረምት መኖሪያ ቤት አጥተው ለጎዳና ሕይወት የሚዳረጉትን መታደግ ሲገባ፤ በአዲስ አበባ ቦሌ ቡልቡላ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ በሁለት ወረዳዎች ብቻ 20 እና 30 ሺሕ ነዋሪዎችን ማፈናቀል ከሰብኣዊ መብትም ሆነ ከሞራል አንፃር የሚያስኬድ አይደለም። መንግሥት እየወሰደ ያለው ኃላፊነት የጎደለውን ተግባር ቆም ብሎ ማሰብ አለበት። ቤቶቻቸው ሕገ-ወጥ እንኳ ቢሆን ያለምትክ ቦታና ካሣ እንዲሁም ክረምት ጠብቆ ማፈናቀል የተሳሳተው የመሬት ፖሊሲ ውጤት መሆኑ መታወቅ አለበት።
ስርዓቱን ብቻ አምነው የሕዝቡን የመሬት ባለቤት መብትና ጥቅም ወደጎን በመተው የመሬት ቅርምቱ ላይ የሚሳተፉ የግል ባለሀብቶች ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው። የስርዓት ለውጥ ቢኖርም ሆነ ያለው ስርዓት ቢቀጥል የሕዝቡ መብትና ጥቅም እስካልተጠበቀ ድረስ መዋዕለ ነዋያቸውን አፍሰሰው ለሚሠሩት ኢንቨስትመንት ዋስትና እንደሌላቸው መረዳት አለባቸው። ምክንያቱም ብዙ የተገፋ ሕዝብ በአንድ ሌሊት ተነስቶ የራሱን እርምጃ የማይወስድበት ምክንያት የለም። ስለዚህ ቢቻል በቀጥታ ከነዋሪው ካልሆነ የሕዝቡ መብትና ጥቅም መረጋገጡን ሳያረጋግጡ ሕዝብ በተፈናቀለበት የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት ላይ ገንዘባቸውን ከመበተን ይልቅ ሕዝቡን ባሳተፈ፣ አሊያም የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ፕሮጀክት ስለመተግበራቸው ቀድመው ቢገነዘቡ ይመከራል።
መንግሥት አሁን ከሚከተለው የመንገድ የተለየ መሻሻልም ሆነ የሕዝብን መብትና ጥቅም ታሳቢ ያደረገ ለውጥ ማድረግ ካቃተው ወይንም የመንግሥትን ሚና እና ግዴታ መለየት ከተሳነው ሥልጣኑን ለሕዝብ ማስረከብ ብቸኛው አማራጭ መሆን አለበት። አለበለዚያ አሁን በሚከተለው መንገድ የሚቀጥል ከሆነ ስርዓት በሕዝባዊ ኃይል መፍረስ ብቻ ሳይሆን አገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ በመምራት ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል መታሰብ አለበት።
የመሬት ሕጉም ሆነ ፖሊሲው መሻሻል አለበት፤ ካልሆነ ግን መንግሥት ገበሬዎችንም ሆነ የከተማ ነዋሪዎችን ማፈናቀሉ ይቀጥላል። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ አለመረጋጋትን ይፈጥራል። ለዚህ ማሳያ ደግሞ በኦሮሚያ ያለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ በአዲስ አበባ እንደክፉ ጠላት ክረምት ጠብቆ እየፈረሱ ያሉ መኖሪያ ቤቶችን ተከትሎ የሚፈጠረው ቅራኔ ምናልባት ቀኑን እንደነብይ መተንበይ ቢያስቸግርም፤ ወደሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ተዛምቶ አዲስ የመሬት ባለቤትነት አብዮት ሊፈጠር ይችላል። ያኔ እንደዛሬው እየሳቁና እያስገደዱ፣ እንዳፈረሱና እንዳፈናቀሉ መቀጠል ላይቀል ይችላል። ምክንያቱም የመሬት ጉዳይ ለስርዓቱ የሥልጣኑ መሠረት እንደሆነ ቢታወቅም፣ ለሕዝብ ደግሞ የመኖርና ያለመኖር የኅልውና ጉዳይ ነው።