በጎንደር የሰላማዊ ሰው ግድያ የቀጠለ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠርቷል

(አዲስ ሚዲያ) ዛሬ ነሐሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ መንግሥት ሰላማዊ ዜጎችን ተኩሶ 1 ወጣት መግደሉን ተከትሎ ዳግም ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሷል፡፡ በሌላ የከተማዋ አካባቢም በተመሳሳይ መልኩ በመንግሥት በተወሰደ ወታደራዊ የኃይል ርምጃ የቆሰሉ እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡ እንደ መብት አራማጆች ከሆነ፤ ነጭ ለብሰው በመንቀሳቀሳቸው ብቻ ዛሬ በጎንደር የተገደሉ ዜጎች ቁጥር 4 ደርሷል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ከተገደለው አንድ ሰላማዊ ዜጋ በስተቀር ሌሎች ጉዳቶችን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

የዓይን እማኞች እንደተናገሩት፤ዛሬ ግድያው የተፈፀመው የጎንደር ህዝብ በመንግሥት ቀጥተኛ ትዕዛዝ በግፍ የተገደሉባቸውን ሰላማዊ ሰዎችን ለመዘከር ነጭ የመልበስ መርሃ ግብርን ተከትሎ ነጭ ለብሶ ሲንቀሳቀስ የነበረ ወጣት በድብደባ ሲገደል፣ ሌሎች 3 ሰላማዊ ዜጎች ደግሞ ከወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ጋብ ብሎ የነበረው የጎንደር ህዝባዊ ተቃውሞ ዳግም ተቀስቅሷል፡፡
ህዝቡም ዛሬ  በግፍ የተገደለ ወጣት አስከሬን በአደባባይ ይዞ በመዞር ተቃውሞውን እያሰማ ይገኛል፡፡ ጎንደር ባለፈው ሳምንት እሁድ ጀምሮ ለ3 ቀናት ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

Gonder Amhara Protest

በከተማው ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄን ተከትሎ መንግሥት አስተባባሪ የኮሚቴ አባለት ላይ የወሰደውን የኃይል ርምጃ ተከትሎ በነበሩት የፀረ አገዛዝ የህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች በመቀጠላቸው ስጋት የገባው መንግሥት፤ በርካታ የታጠቁ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ እና የፌደራል ልዩ የፀጥታ ኃይሎችን በከተማው ማስፈሩ ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና፤ በኦሮሚያ እስካሁንም ድረስ የቀጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ትናንት ነሐሴ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ደንቢዶሎ አንድ ሰላማዊ ወጣት በመንግሽት አልሞ ተኳሾች መገደሉ የታወቀ ሲሆን፤ በምስራቅ ሷ ዝዋይ ከተማ እቤቱ የነበረ አንድስ ሰላማዊ ዘጋም በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ወታደራዊ ርምጃ መገደሉ ታውቋል፡፡

ለነገ ጠዋት በአዲስ አበባ መዳረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገና ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተጋበዘበት ህዝባዊ ታላቅ  የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቷል፡፡የተቃውሞ ሰልፉ ዋነኛ ዓላማ፤ መንግሥት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚወስደውን ግድያ ህዝቡ በተለይም በኦሮሚያና በአማራ ክልል ተቃውሞው የቀጠለ ሲሆን፤ መንግሥት በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ግድያና የፀረ አገዛዝ ተቃውሞ፤ ነገ እሁድ ጠዋት ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ታላቅ  የተባለለት የተቃውሞ ሰልፍ መዘጋጀቱን የተቃውሞ አስተባባሪዎችና የመብት አራማጆች አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በሀገር ቤት እየጠፈፀመ ያለውን የመንግሥት ግድያ፣ እስራትና አገዛዝ ድርጊትን በመቃወም በተለያዩ የአሜሪካ፣ አውሮፓ እና አፍሪካ ሀገሮችና ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞ እያደረጉ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

መንግሥት ሰላማዊ ዜጎችን በአደባባይ መግደሉ እንዳሳሰበው በመጠቆም ምርመራ ማድረግ እንደሚፈልግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቢያስታውቅም አገዛዙ የመንግሥታቱ ድርጅትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራን እንደማይቀበልና ከላከው ምላሽ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ጉዳዩ ያሳሰባቸው የአሜሪካና የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት መንግሥት እየፈፀመ ያለውን ግድያ በማውገዝ ጉዳዩን በጥብቅ እየተከታተሉት እንደሆነ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

ከህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት በወሰደውና እየወሰደ ባለው ወታደራዊ የኃይል ርምጃ በኦሮሚያ ክልል በነበሩት ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ከ500 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ሲገደሉ፤ ሁለተኛ ወሩን ባስቆጠረው የአማራ ክልል ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ደግሞ ከ100 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: