ብስራት ወልደሚካኤል
(አዲስ ሚዲያ)የወልቃይት የአማራ ማንነት መብት ጥያቄን መነሻ አድርጎ በጎንደር ፋሲል ከተማ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ፤ የተለያዩ የሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ወረዳና ከተሞችን ጨምሮ ወደ ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም እንዲሁም ወደ ሰሜን ወሎ መቄት እና ሸዋ ሮቢት መስፋፋቱን እማኞች ለአዲስ ሚዲያ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ነሐሴ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ከተማ፣ ነሐሴ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ቡሬ ወምበራ ወረዳ ቡሬ ከተማ የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር በተለያዩ ወረዳዎች እና ከተሞች ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ተቃውሞዎች እና የመንግሥት የኃይል ርምጃዎችም የቀጠሉ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
በጎንደር፣ ባህርዳር እና ደብረማርቆስ ከተሞች ከቤት ያለመውጣት ተከታታይ ህዝባዊ ተቃውሞች የተደረጉ ሲሆን ከነሐሴ 22-25 ቀን 2008 ዓ.ም. ደግሞ በተመሳሳይ ምልኩ በደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር ከተማ ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ እንደሚደረግ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በአማራ ክልል ባሉ ሰሞንኛ ተቃውሞች በተለይ በማክሰኝት፡በገደብዬ፡በእንፍራንዝ፣ በአብደራፊ፣ በአርማጭሆ፣ በፍኖተ ሰላም፡ቡሬ፡ ጅጋ እና ማንኩሳ በተባሉ ወረዳዎች ህዝባዊ ተቃውሞዎች የበረቱባቸው መሆኑን ያገኘነው መረጃ አመልክቷል፡፡ በነኚህ ስፍራዎች የነበሩ ተቃውሞች መካከልም የተወሰኑ በማኀበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጩ መዋላቸውን ለመታዘብ ተችሏል፡፡
በነበሩ የአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞች ሁለት ሰላማዊ ሰዎች በመንግሥት መገደላቸው የተጠቆሙ ሲሆን፤ በተለይ በሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ ወረዳዎች በነበሩ ተቃውሞች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በኦሮሚያ ክልልም ህዝባዊ የፀረ አገዛዝ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞች የቀጠሉ ሲሆን፤ በዚህም በምዕራብ ሐረርጌ መሰላ ወረዳ በሚገኙ ዋልተሲስ እና ጎሮ በተባሉ መንደሮች በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ አራት ሰላማዊ ዜጎች በመንግሥት በተወሰደ የኃይል ርምጃ መገደላቸው ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገሪቱ ያለውን የመንግሥትን ግድያ፣ እስርና እና አፋና በመቃወማቸው በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ለእስር የተዳረጉ የፖለቲካ እስረኞች በተለይም እነ አቶ በቀለ ገርባ በሀገሪቱ ከነሐሴ 19-21 ቀን 2008 ዓ.ም. ብሔራዊ የሀዘን ቀን በሚል ታስቦ እንዲውል ያደረጉት ጥሪ ከወዲሁ በተለያዩ ደጋፊዎቻቸው ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ታውቋል፡፡
የመንግሥት የኃይል ርምጅና ግፍ በመቃወም በሚደረግ ብሔራዊ የሀዘን ቀንም ፀጉር መላጨት፣ ጥቁር ልብስ መልበስ፣ ጥቁር ባንድራ(ጨርቅ) ማውለብለብ፣ ሻማ ማብራት፣ በተቃውሞ ትግሉ የተገደሉ ሰላማዊ ዜጎች ቤተሰቦችን መጎብኘት እና ተሰብስቦ ህዝባዊ ውይይት በማካሄድ እንዲተገበር ጥሪ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ባሉ ዜጎች ከወዲሁ ተግባራዊ መደሩ የሚያመለክቱ የተለያዩ ምስሎች በማኀበራዊ ሚዲያዎች ላይ መሰራጨታቸውን ማየት ተችሏል፡፡
በኦሮሚያ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ካለው የፖለቲካና ማኀበራዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ከጳጉሜ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የኢኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞችም እንደሚተገበሩ የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች እና የመብት አራማጆች ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞው ምን ላይ እንደሚያተኩር በዝርዝር የተቀመጠ ነገር ባይኖርም፤ ወደፊት ይፋ እንደሚደረግ የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡
በታቀደው መሰረት በኦሮሚያ የኢኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ መንግሥት በክፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ይጠበቃል፡፡ በተለይም መንግሥት ከክልሉ በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪና የሀገሪቱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆኑት እንደ ቡና፣ የጫት፣ የአበባ፣ የቁም እንሰሳትና፣ የቆዳና ሌጦ እንዲሁም የምግብ ነክ የሆኑ የብግርና ምርቶች እንዲሁም ወርቅና የመሳሰሉ የማዕድን ሃብቶች ከክልሉ እንዳይወጡና ወደ ማዕከላዊም ሆነ የክልሉ ገበያ ንግድ ላይ የማይውሉ ከሆነ ምን አልባትም በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ፈተና በመንግሥት ላይ ሊደርስ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የኢኮኖሚ ተኮር ህዝባዊ ተቃውሞ በቀጣይ ወደሌሎች ክልሎች በተለይም አማራ እና ደቡብ ክልል የሚዛመት ከሆነ ደግሞ የመንግሥት 90% የገቢ ምንጭ በማድረቅ ስርዓቱን ሙሉ ለሙሉ አደጋ ላይ እንደሚጥለው ይገመታል፡፡ በተለይ ኦሮሚያ እና አማራ ክልል ብቻ የሀገሪቱን 54% የሆነውን ህዝብ ቁጥር እንደሚሸፍኑ እና ከ65% የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪና የገቢ ምንጭም መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ከባለፈው ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ የተቀጣጠለው የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ መላው ኦሮሚያ ክልልን በማዳረስ፤ ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ አማራ ክልል ተዛምቷል፡፡ በሁለቱም ክልሎች ዘገባው እስከተጠናቀረበት ድረስ ህዝባዊ ተቃውሞዎቹ በተለያዩ ወረዳዎችና ከተሞች ቀጥሏል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በሁለቱም ክልሎች ባሉ የተለያዩ ቦታዎች መደበኛ የመንግሥት ስራን ጨምሮ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋቶች እየታዩ ነው፡፡
አስረኛ ወሩን ባስቀጠረው ህዝባዊ ተቃውሞ በሁለቱም ክልሎች ከ650 በላይ ሰላማዊ ዜጎች በመንግሥት በተወሰደ የኃይል ርምጃ ሲገደሉ፣ ከ 1,250 ያላነሱ ዜጎች ቆስለው በግምት ከ35,000 በላይ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ እና የቆሰሉ ሰዎች በተለያየ ጊዜ ስማቸውና ምስላቸው በሰፊው በማኀበራዊ ሚዲያ እየተገለፀ ይገኛል፡፡ በሁለቱም የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ህዝባዊ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ የወጣው ህዝብ አንዱ ለሌላው በተለያዩ ጊዜና ቦታ ያሳዩት የርስ በርስ አጋርነት፤ መንግሥትን ከፍተኛ ድንጋጤ ላይ እንደጣለው ባለስልጣናቱ በስራቸው ባሉ መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ የተደመጡ ሲሆን፤ በዚህም ስጋት እንዳደረባቸው ባለስልጣናቱና ደጋፊዎቻቸው በይፋ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎችና ከሚሰነዝሯቸው አስተያየቶች መረዳት ተችሏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ ፤የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ”የጋራ ልማት የተቀናጀ ማስተር ፕላን” በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ገበሬዎች የሚያፈናቅልና ለጎዳና ህይወት የሚዳርግ ነው በሚል ቀደም ሲል የነበረውን ተቃው ከዓመት በኋላ በማገርሸት በምዕራብ ሸዋ ጊንጪ ከተማ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በአማራ ክልል ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት መብት ጥያቄ ህዝባዊ ወኪሌ ኮሚቴ አባላት ላይ መንግሥት በሌሊት በመኖሪያቸው አካባቢ የፀጥታ ኃይሎችን በመላክ የኃይል ርምጃ መውሰዱን ተከትሎ በጎንደር ከተማ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
መንግሥት በወሰደው የኃይል ርምጃ ስለደረሱ አጠቃላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች በተመለከተ በመንግሥት ጉዳዩን ለመሸፋፈን ከመሞከር በዘለለ ትክክለኛውን ቁጥርና የጉዳት መጠለን ለመናገር አልደፈረም፡፡ ቀደም ሲል ሀገር በቀል በሆነው የሰብዓዊ መብት ጉባዔ (ሰመጉ) እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች (HRW) አማካኝነት በተወሰኑ ወረዳዎችና አካባቢዎች የተደረጉ ምርመራዎች ይፋ ከመደረጋቸው በስተቀር አጠቃላይ በደረሱ የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳቶች የተደረገ ምርመራም ሆነ ሪፖርት የለም፡፡ ይህን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ምት ኮሚሽን ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲደረግ በይፋ ጥያቄ ቢያቀርብም በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት በበኩሉ የመንግሥታቱን ድርጅት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡