(አዲስ ሚዲያ)ዛሬ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. አዲስ አበባ አቃቂ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ከ25 ያላነሱ እስረኞች መሞታቸው ተጠቆመ፡፡ በጥበቃ ላይ የነበሩ ወታደሮችም ከእሳቱ ለማለጥ የሞከሩ እስረኞች ላይ ሲተኩሱ እንደነበር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ከቃጠሎው በፊት በነበረው ተኩስ ምን ያህል እስረኞች ላይ ጉዳት እንደደረሰ እስካሁን ማረጋገጥ ባይቻልም፤ በነጋታው ጠዋት በነበረው የእሳት አደጋ ከ25 ያላነሱ ሰዎች መሞታቸውን ከቅዱስ ጳውሎስ፣ ሜክሲኮ በሚገኘው ፖሊስ ፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ እና የካቲት 12 ሆስፒታል ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቃጠሎው ጉዳት የደረሰባቸውና በህይወት የተረፉትም አብዛኞቹ ፖሊስ ሆስፒታልና የካቲት 12 ሆስፒታል በጥበቃ ስር ሆነው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
በወህኒ ቤቱ ታስረው ከሚገኙት መካከል ስመጥር እና ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸው በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ያሉበት ሲሆን በተለይም፤ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ፖለቲከኞች፣ የመብት አራማጆች እና ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት ይታወቃል፡፡
በያዝነው 2008 ዓ.ም. ብቻ ከአዲስ አበባ አቃቂ ከሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት በተጨማሪ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች የሚገኙባቸው ጎንደር፣ አምቦና ደብረ ታቦር ወህኒ ቤት በተመሳሳይ መልኩ የእሳት አደጋ ሰለባ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ በነበሩ አደጋዎች መንስኤ እና ጉዳትን በተመለከተ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም ከመግለፅ መቆጠቡ ይታወቃል፡፡
በተለይ የአቃቂ ቂሊንጦውን እሳት ቃጠሎ ተከትሎ በርካታ የታሳሪ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች እና ደጋፊዎች ስጋት እንዳደረባቸው በተለያየ መድረክ ከመግለፅ በተጨማሪ በአዲስ አበባና አጎራባች አካባቢ ያሉ ሰዎች የቤተሰቦቻቸውን ደህንነት ለማጣራት ሙከራ ቢያደርጉም በወህኒ ቤቱ አስተዳደር እንዳልተፈቀደ ተረጋግጧል፡፡ በወህኒ ቤቱ የታሰሩ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ከተለያዩ የክልል ከተሞች የመጡ ሰዎችም ወደ እስር ቤቱ ግቢም ሆነ ከግቢ ውጭ በቅርብ ርቀት እንዳይጠጉ በመከልከላቸው ወደየመጡበት መመለሳቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
በአደጋው የደረሰውን ጉዳትና ምክንያት በተመለከተ የወህኒ ቤቱ አስተዳደርም ሆነ መንግሥት እስካሁን የሰጡት መረጃ የለም፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ ሰዎች አደጋው በመንግሥት ሆን ተብሎ የተቀነባበረና የፖለቲካ እስረኞችን ለመጉዳት የታሰበ የገዥው ስርዓት የተለመደ ስልት እንደሆነ የሚገልፁ ቢኖሩም፤ ስለ አደጋውና አጠቃላይ መረጃ ከገለልተኛ አካልም ሆነ ከመንግሥት ለማወቅ አልተቻለም፡፡