አቤል ዋበላ
ሁለት ተከታታይ ደመራዎችን ያበራኹት ቂሊንጦ ዞን አንድ ነበር፡፡ በእስር ቤት ሀይማኖታዊ እና ብሔራዊ በዓላት እንደሁኔታው እንደአቅሚቲ ይከበራሉ፡፡ ዛሬ በዚህች አጭር ማስታወሻ ላጫውታችኹ የወደድኩት በዚያ ካሳለፍኳቸው በዓላት አንዱ የሆነውን የ2007 ዓ.ም. የደመራ በዓል ነው፡፡
ቂሊንጦ ያለው እስረኛ በሙሉ ያልተፈረደበት የቀጠሮ እስረኛ ነው፡፡ ያው ሁሉም እንደሚያውቀው ፍርድ ቤቱ ማስረጃዎችን መርምሮ ውሳኔ እስኪሰጥ አመታት መፍጀቱ የተለመደ ነው፡፡ ስለዚህ በእስር ቤቱ አመታትን ያሳለፉ ሲኒየር የቀጠሮ እስረኞችን ማግኘት የተለመደ ነው፡፡ አምና ለበዓል የተደረገው ዘንዶሮ እንዳይቀርባቸው እስረኞቹ ኮሚቴ አቋቁመው ተፍ ተፍ ይላሉ፡፡ በመዋጮም በጨረታም ብር ይሰበስባሉ፡፡ ከውጭ ተገዝተው የሚመጡ ዕቃዎችን እንዲያስገቡ የማረሚያ ቤቱን ኃላፊዎች እንዲማልዱ ትልልቅ ሰዎች ተመልምለው ይላካሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ በሙስና የተከሰሱ ሰዎች በማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ዘንድ ተሰሚነት ስለሚኖራቸው የሚላኩት እነርሱ ናችው፡፡ እነርሱም ተስማምተው ደጅ ከጠኑ፣ ከቦጨቁትም በጥቂቱ ዘግነው ስለሚሰጡ በስኬት ይመለሳሉ፡፡
በዚያ አመት ማረሚያ ቤቱ ለደመራ ታስበው የተገዙ ችቦዎችን አላስገባም በማለቱ እስረኛው ሲያጉረመርም ትዝ ይለኛል፡፡ አንዳንዱ እስረኛ እስር ቤት መሆኑን ይዘነጋዋል፡፡ እስኪ አላስገባም ይበሉና እንተያያለን በማለት ሲዝቱ ሳይ ግርም አለኝ፡፡ ጸብ ቢነሳ ወዴት መሮጥ እንዳለብኝ ማሰቤ አልቀረም፡፡ በዚያን ወቅት ከማዕከላዊ ከመጣኹ ገና ሁለት ወሬ ስለነበር የእስረኛውን ስነ ልቦና ስላልተረዳው አንድ ግርግር እንዳይፈጠር መስጋቴ አልቀረም፡፡ እየቆየው ስሄድ ባዶ ጉራ እንደሆነች ገባኝ፡፡
በኋላ ምልጃው ከውጭ የመጣውን ባያሰገባም የማረሚያ ቤቱ ውጨኛው ግቢው ውስጥ ከሚገኙ ዛፎች የሚነድ ነገር ተሰብስቦ ደመራው እንዲዘጋጅ የሚፈቅድ ይሁንታን አስገኘ፡፡ የተወሰኑ ልጆች ተመርጠው ከኛ ዞን ወጥተው የሚነድ ነገር ለመልቀም ከአጃቢ ፖሊስ ጋር ወደዋናው ጊቢ ወጡ፡፡
መስከረም ከክረምቱ ብዙም ያልተለየ ስለሆነ ብዙም ያልደረቀውን ማገዶ ይዘው መጡ፡፡ ከዚያ ወፈር ያለውን ስር የሌለው ልጅ-እግር ዛፍ መኸል አቁመው ደመራ የሚስል ነገር ሠሩልን፡፡ ቆፍረው ቢቀብሩትም አመሻሽ ደርሶ ሳንሎክሰው እንዳይወድቅ ስጋት ውስጥ ገባን፡፡
በአይነ ቁራኛ ሲጠበቅ ሰዓቱ ደረሰ፡፡ ከእስረኛው መካከል ካህናት እና ዲያቆናት አልታጡም፡፡ ለስርዓተ ጸሎቱም ደመራውንም ለመሎከስ ተዘጋጁ፡፡ ጸሎቱ አብቅቶ ደመራው ጋዝ ተርክፍክፎበት መንደድ ጀመረ፡፡ ወፍራሙም ዲያቆን ከበሮውን አንስቶ ይደቃው ጀመር፡፡
በደመራ ትውፊት ደመራው መሀል ከላይ የአደይ አበባ በመስቀል ቅርጽ የሚታሰርበት ያለው አውራ ነዶ ወዴት እንደሚወድቅ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ ታዳሚው ወዴት እንደሚወድቅ ሳይመለከት አይበተንም፡፡ ከልጅነት ጀምሮ እንዳስተዋልኩት ደመራው ወዴትም ይውደቅ ወዴት አመቱ የደስታ ነው፤ አመቱ የሰላም እና የብልጽግና ነው፤ የሚል በጎ በጎ ምኞት ይሰነዘራል እንጂ ወደሰሜን ከወደቀ ሀዘን ወደደቡብ ከወደቀ ደስታ የሚል የተደነገገ አሉታዊ ትርጓሜውም፡፡ የኛም ደመራ ለዚህ ወግ በቅታ ወዴት እንደምትወድቅ መጠበቅ ጀመርን፡፡ እስረኛውም ወደመውጫው በር ወድቆለት አመቱ የፍቺ ዓመት ነው እያለ ለማሳለፍ ተዘጋጅቷል፡፡ የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶችም ወዴት ይወደቅ ብቻ ቶሎ ይውደቅና ቆጥረውና ቆልፈውብን ለመሄድ ጓግተዋል፡፡
ቢጠበቅ ቢጠበቅ ወደታች በጥልቀት ይቅበሩት አልያም እንጨቱ እርጥብ ስለሆነ ብቻ ባልታወቀ ምክንያት ሳይወድቅ ቆየ፡፡ በዙሪያው ያለው ርብራብ ተቃጥሎ ወደአመድነት ተለውጧል፡፡ ከመሬት ትንሽ ከፍያለው ወደባቱ አከባቢ እሳት እንደበላው ያስታውቃል፡፡ ዲያቆኑም ደክሞት መዝሙር መምራቱን አቁሟል፤ ፖሊሶቹ እየተቁነጠነጡ ነው፤ ደመራው አልወደቀም፡፡ ሁሉም ሰው ግራ ገብቶት ትውፊቱን ላለመተው በግርምት ይተያያል፡፡
አንድ መላኩ የሚባል በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥሮ የገባ እስረኛ አለ፡፡ ፍርድ ቤቱ መታመሙን እርግጠኛ ባይሆንም የአእምሮ ህመምተኛ ሆኗል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲሶርደር እንዳለበት በግልጽ ያስታውቃል፡፡ ዝርዝሩን ለባለሙያዎች እንተወው፡፡ ቆሻሻ ሲያነሳ እና ሲጥል ነው የሚውለው፡፡ ሰው ሰለማይተናኮል እስረኛው ሁሉ ወዳጁ ነው፡፡ የተደራጀ ነገር ባያወራም ከመታሰሩ በፊት ኮሚክ ነገር እንደነበር ያስታውቃል፡፡ አንዳንዴ ሲለው እንግሊዘኛ ይሞካክራል ይሄን ጊዜ እስረኛው “ፓ! መሌ እኮ የተማረ ነው” ብሎ ያደንቀዋል:: ብቻ ምን አለፋቹኽ መሌ ራሱ ተረኩ ብዙ ነው፡፡
የመሌን ታሪክ መጥቀሴ አለነገር አይደለም፡፡ በዚያ ቀን እስረኛው እና ፖሊሱ ተፋጥጦ ትውፊት ላለማፍረስ የደመራውን በራሱ መውደቅ ሲጠባበቅ የመሌን ትኩረት ይስባል፡፡ መዝሙር የለ፤ እንቅስቃሴ የለ ፡፡ የሚስቅ የሚጫወት ሰውም አይታይም፡፡ ሰው ሁሉ ያን በእሳት የተበላ እንጨት በጉጉት ይመለከታል፡፡ መሌ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው? ቀጥ ብሎ ሄደና ደመራውን አንዴ በእርግጫ ሲለው በአፍጢሙ ድፍት አለ፡፡ መጻኢውን ጊዜ ለመተንበይ የፈለጉ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ቢናደዱም አብዛኛው እስረኛ ፖሊሶቹን ጨምሮ በሳቅ እያውካካ የበዐሉ ፍጻሜ ሆነ፡፡
ዛሬ እቤቴ ቁጭ ብዬ ሳስብ ያ በእሳት ተበልቶ ሳይወድቅ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የቆየ እንጨት የወያኔ መንግስት ይመስለኛል፡፡ (At least metaphorically) እንደመሌ ያለ በካልቾ ብሎ እስኪያደባያው ድረስ የሚጠብቅ ይመስለኛል፡፡ የመሌን ድርሻ የሚወስድ ማን ይሆን?