ብርሃኑ ፈቃደ
– ፖለቲካዊ አለመግባባቶች በምክክር እንዲፈቱና ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የመንግሥት የቤት ሥራ መሆኑን አሳሰቡ
– ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር በአገሪቱ ጉዳይ ተነጋገሩ
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ የገቡት የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በፖለቲካ መስክ ለተቃዋሚዎችም ሆነ ለሲቪክ ማኅበራት ሰፊ ዕድል እንዲሰጥ ጠየቁ፡፡ የፖለቲካ አለመግባባቶች በውይይትና በምክክር እንዲፈቱም አሳሰቡ፡፡
መርከል ማክሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንደተናገሩት፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መደመጥ አለባቸው፡፡ ሲቻልም በተወካዮች ምክር ቤት ጭምር እንዲሳተፉ በማድረግ ድምፃቸው እንዲሰማ፣ ውይይትና ክርክር እንዲያደርጉ መንገዱን ማመቻቸት ይገባል፡፡
‹‹መነጋገር በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በተነጋገርንበት ወቅት ገልጫለሁ፡፡ የሲቪክ ተቋማትን ማሳተፍና በጠረጴዛው ዙሪያ እንዲገኙ መጋበዝ ይገባል፡፡ ጥሩ ትምህርት ቤቶች ሠርታችኋል፡፡ ከጎበኘኋቸው የአፍሪካ አገሮች ይልቅ እዚህ ብዙ ጥሩ ነገሮች ተሠርተዋል፡፡ ነገር ግን ለወጣቶች ሥራ መፍጠር ካልቻላችሁ የተሠራው ሁሉ ምንም ትርጉም አይኖረውም፤›› ያሉት መራሒተ መንግሥት መርከል፣ ‹‹ከአገሪቱ ግማሽ ያህሉ ሕዝብ በወጣቶች የተገነባ ነው፡፡ ወጣቶች ደግሞ ስሜታቸውን ባገኙት መንገድ መግለጽ ይፈልጋሉ፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎችና በሌሎችም የሚሰማቸውን ለመግለጽ ይፈልጋሉ፡፡ ቅሬታውቸውን ሲገልጹም ትዕግሥት ላይኖራቸው ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ በውይይትና በመነጋገር ጥሩ የመፍትሔ ሐሳቦች እንደሚመነጩ ሲመክሩም፣ በአገራቸው የፖለቲካ ሥርዓት በውይይትና በመነጋገር አብዛኞቹ ለውጦች እንደሚመነጩ አብራርተዋል፡፡ በዚህም አገር የቱንም ያህል አስቸጋሪና ከባድ ቢሆን በመነጋገር ችግሮችን መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡
መንግሥት እንዲህ ያሉ አሳሳቢ ችግሮችን ለመፍታት ወጣቶችን በኢኮኖሚ መስክ በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንደሆኑ ከማድረግ ባሻገር፣ ነፃ ሚዲያም ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ህልውና ወሳኝ እንደሆነ በመግለጽ መንግሥት ትኩረትም ቦታም እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
‹‹ዴሞክራሲያችን እንጭጭና ያልጠነከረ በመሆኑ በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ በየፈርጁ ያሉብንን ችግሮች ከማመን ተቆጥበን አናውቅም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በአገሪቱ ይበልጥ የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያሰፉ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ከመራሒተ መንግሥት መርከል ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት አስታውቀዋል፡፡ አሳታፊና ለበርካቶች ዕድል የሚፈጥሩ፣ ለሲቪክ ማኅበራትም ቦታ የሚሰጡ ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ጠቁመዋል፡፡ በምርጫ ሥርዓቱ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉም አስታውቀዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ የመርከል ማብራሪያዎች በአብዛኛው በፓርላማው በፕሬዚዳንቱ ከቀረበው የመንግሥት የሥራ ዕቅድ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ነበሩ፡፡
ወጣቶች ሥራ በማጣት በዚህም ሳቢያ በተፈጠረባቸው መከፋትና ተስፋ መቁረጥ መንግሥት ላይ ተቃውሞ ማሰማታቸው ተገቢ እንደሆነ ያመኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት የተነሳበትን ተቃውሞ ትክክለኛ መሆኑን እንደሚቀበልም አስታውቀዋል፡፡ ከ15 ሚሊዮን ያላነሱ ወጣቶች በሥራ ፍለጋና በትምህርት ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ መንግሥት የሥራ ዕድሎችን በሚፈለገው መጠን ማሟላት እንዳልቻለ አምነዋል፡፡
ይሁንና ተቀባይነት ያላቸውን ተቃውሞች ተገን በማድረግ የተከሰቱት ብጥብጦችና ንብረት የማውደም ዕርምጃዎች ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል፡፡ በርካታ ፋብሪካዎች፣ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የገነቧቸው ኢንዱስትሪዎችና ሀብቶች መቃጠላቸውን በመግለጽ፣ እንዲህ ያሉትን ብጥብጦች ጉዳት ያስከተሉት ‹‹ከውጭ ጠላቶች›› ጋር የሚያብሩና ‹‹መሣሪያ የታጠቁ›› አካላት ናቸው በማለት በአገሪቱ የተቀጣጠለውን ፖለቲካዊ ቀውስ ለማብረድ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገግ በኋላም በአገሪቱ አንድም ብጥብጥ እንዳልተከሰተ ጠቁመዋ፡፡
የተከሰቱትን ግጭቶችና ብጥብጦች ለመቆጣጠር የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት ዕርምጃ ተመጣጣኝነትን በሚመለከት ተጠይቀውም፣ ‹‹መሣሪያ ካነገቱ ታጣቂዎች ጋር መነጋገር የሚቻለው በመሣሪያ ብቻ ነው፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ይሁንና የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት ዕርምጃ ተመጣጣኝ ስለመሆኑና ከሚፈቀድላቸው በላይ ኃይል ስለመጠቀማቸው ምርመራ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡
በተከሰተው ቀውስ ምክንያት የሟቾች ቁጥር ከ500 በላይ ስለመድረሱ የተጠየቁት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ግጭቶቹን የሚያባብሱት የታጠቁ ሰዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሟቾችን ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅበው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩንም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እያጣራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከሰቱ ግጭቶች የሟቾች ቁጥር 190 ያህል እንደደረሰ፣ ከዚህም ቀደም በተከሰተው ግጭት በኦሮሚያ 178 ሰዎች፣ በአማራ ክልል ደግሞ 120 ሰዎች መሞታቸውን ኮሚሽኑ ይፋ እንዳደረገ በመጥቀስ ከጀርመን ጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የተቀሰቀሱ ግጭቶችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች የሚወስዷቸው ዕርምጃዎች ተመጣጣኝነት ላይ የሚነሱትን ክሶች መነሻ በማድረግም፣ መንግሥታቸው የጀርመንን ድጋፍ እንደሚሻና ሥልጠና እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡ ብጥብጥን ለመቆጣጠርና ግጭቶች ደም አፋሳሽ ከመሆናቸው በፊት በሠለጠነ መንገድ ለመቆጣጠር የፀጥታ ኃይላቸውን ጀርመን እንድታሠለጥንላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ የተቀበሉት መርከል፣ ድጋፍ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱ መሪዎች በተሰጠው መግለጫ ወቅት መራሒተ መንግሥት መርከል ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ስለሚያደርጉት ውይይት አጀንዳ ምንም ዓይነት ማብራሪያ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች በፀጥታና በደኅንነት ጉዳዮች፣ ስደተኞችን በተመለከቱ ተግባራትና በሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በሁለትዮሽ ውይይታቸው ወቅት መነጋገራቸው ታውቋል፡፡
ጀርመን በኢትዮጵያ መንግሥት አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ የተቃዋሚ ቡድኖች መካከል እንደ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ያሉት የሚገኙባት እንደመሆኗ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለቱ መሪዎች ተነጋግረው እንደሆነ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ፣ መሪዎቹ እንዲህ ባሉ ነጥቦች ላይ በተናጠል እንዳልተነጋገሩ ገልጸዋል፡፡
መራሒተ መንግሥት መርከል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉትን ውይይት አጠናቀው፣ በጀርመን ድጋፍ በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባውንና በቀድሞው የታንዛኒያ መሪ ጁሊየስ ኔሬሬ ስም የተሰየመውን የፀጥታና የደኅንነት መሥሪያ ቤት መርቀዋል፡፡ ስድስት ያህል የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግረው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከመራሒተ መንግሥት መርከል ጋር በአገሪቱ በተካሄዱ ተቃውሞዎችና የመንግሥት ምላሽ፣ በነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡
አገሪቱ በወሳኝና አሳሳቢ ጊዜ ላይ እንዳምትገኝ የገለጹት ዶ/ር መረራ መንግሥት እንደወትሮው ‹‹የተቀባባና የተሽሞነሞነ መግለጫውን›› ትቶ ትክክለኛ ለውጥ በአፋጣኝ እንዲያመጣ፣ የሚደረጉ ለውጦችም ወደፊት በታሳቢነት ሳይሆን አሁኑኑ ሊደረጉ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ አንገላ መርከል የአገሪቱ ተቃዋሚዎች፣ ሲቪክ ማኅበራትና ሌሎችም የሚገኙበትን ሁኔታ እንደሚገነዘቡና በሚደርስባቸው ጫናም ሐዘኔታ እንዳደረባቸው ዶ/ር መረራ ገልጸዋል፡፡
አንገላ መርከል ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ወደፊት እንደሚጠብቁ የገለጹት ዶ/ር መረራ፣ እሳቸውን ጨምሮ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን፣ የሴቶች ማኅበራት ተወካዮች በተገኙበት ከመራሒተ መንግሥት መርከል ጋር መነጋገራቸው በማውሳት ሪፖረተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡