የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የሰላማዊ ዜጎች እስር ቢኖርም፤ በአንዳንድ ቦታዎች አሁንም ተቃውሞች እንደቀጠሉ ናቸው

(አዲስ ሚዲያ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓም ተግባራዊ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች በጅምላ እየታሰሩ ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል እስሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ በቅርብ ርቀት የምትገኘው ሰበታ ከተማ ብቻ ከ አንድ ሺህ በላይ ተጠርጣሪ ናቸው ያላቸውን ነዋሪዎችን ማሰሩን ራሱ መንግሥት ያስታወቀ ሲሆን፤ በሌሎችም የኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከተሞችና ወረዳዎችም በተመሳሳይ መልኩ እስሩ መቀጠሉን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን እና ጎንደር ዞን መንግሥት የነዋሪዎቹን ትጥቅ ለማስፈታት ወደ ወረዳዎች እና ገጠር ቀበሌዎች የፀጥታ ኃይሉን ቢያሰማራም ከህዝቡ የአፀፋ ርምጃ በመወሰዱ በርካታ ወታደሮችና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ህዝባዊ ተቃውሞው ከተጀመረበት ቀን አንስቶ የመንግሥት የፀረ አገዛዝና ጭቆና ተቃውሞ እንደቀጠለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በአፋር ክልልም እንዲሁ የሰላማዊ ዜጎች እስሩ የቀጠለ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በአፋርኛ በማዜም የምትታወቀው ድምፃዊት መፈራ መሐመድ ላሌን ጨምሮ አስር ሰላማዊ ዜጎች በአሳይታ ከተማ መታሰራቸው ታውቋል፡፡

ethiopian-singer-mefera-mohmmed

ድምፃዊት መፈራ መሐመድ ላሌ

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያ ትግበራ ላይ መንግሥት እንደ ኢሳት፣ ኦ.ኤም.ኤን. የመሳሰሉ መገናኛ ብዙኃን መከታተልና መረጃ መለዋወ ላይ መመሪያው እገዳ ጥሏል፡፡ በተጨማሪ ያልተፈቀደ ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ፣ ለህዝብ አገልግሎት አለመስጠት፣ በትምህርትና በስፖርት ማዘውተሪያ አድማ ማድረግ በክልከላው ተካተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር የመንግሥትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትግበራባለመቀበል በድጋሚ ለ3ኛ ጊዜ ከቤት ያለመውጣት አድማ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ አስቀድሞ በኢትዮጵያ የመንግሥትን በደልና ብልሹ አሰራር ለመቃወምና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ  ቀድሞም ቢሆን ለዓመታት ፈፅሞ የተከለከሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

መንግሥት ከህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ዓመት ያህል ያለማቋረጥ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቀጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማርገብ በሚል ባለፈው መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ተግባራዊ የሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ኢንተርኔትን በተለይም ማኀበራዊ ሚዲያ፣ በውጭ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተዘጋጅተው ለህዝቡ አማራጭ የመረጃ ምንጭ በመሆን እያገለገሉ ያሉ እንደ ኢሳት፣ ኦ ኤም ኤን ያሉ መገናኛ ብዙኃን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዳይሰራጩ ከማፈን በተጨማሪ ህዝቡም መረጃ መለዋወጥና መስማትም እንደሌለበት በአዋጁ መከልከሉ ይታወሳል፡፡

አዋጁን ተከትሎ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ክልል ኮንሶ ፣ ጋሞ ጎዳ ዞን፣ በአፋርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል (ኦጋዴን) የተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች በመዘዋወር ድንገት ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ የተለያዩ የወርቅ ጌጣጌጦችን፣ ገንዘብ፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ ከመወስድ በተጨማሪ ጠርጥረንሃል ያሉትን ሰው ያለምንም ፍርድ ቤት ማዘዣ እየደበደቡ በመውሰድ ወዳልታወቀ ስፍራ እንደሚያስሯቸው ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ምክንያት ከወትሮ በተለየ መልኩ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ ነዋሪው በፍርሃት ድባብ ውስጥ እንደሚገኙ በመጠቆም በማኀበራዊና ንግድ እንቅስቃሴዎች ላይም አለመረጋጋቶች እንደሚስተዋሉ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

መንግሥትበአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት አፈና እና ቁጥጥሩን አጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ ዋነኞቹ የህዝባዊ ተቃውሞ አስተባባሪዎች መካከል የአማራ ተጋድሎና የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች ከመንግሥት ርምጃ ጋር ተመጣጣኝ ሊሆን የሚችል አዳዲስ የትግል ስልቶችንም በቅርቡ ሊጀምሩ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡ በተለይ በውጭ የሚኖሩ የመንግሥትን አገዛዝ የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያን በስልጣን ላይ ካለው ገዥው ስርዓት ለውጥ በኋላ በኢትዮጵያ ሊመሰረት ስለሚገባው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ትግበራ በቪዥን ኢትዮጵያ እና በኦሮሞ ማኀበረሰብዓለም አቀፍ የህግ ባለሙያዎች ማኀበር አስተባባሪነት ከወዲሁ በሰሜን አሜሪካ ዋሸንግተን ዲሲ  እበእንግሊዝ ለንደን ምክክር መጀመራቸው ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: