‹‹እሰነጥቅሃለሁ ተብያለሁ›› አቶ በቀለ ገርባ
በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ለእስር ተዳርገው የሽብር ክስ የቀረበባቸው የኦፌኮ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ከሦስት ወራት በኋላ እንደገና ወደ ችሎት ሲመለሱ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ቀጠሮ በመያዝ የነበር ቢሆንም፣ በእስር የሚገኙበት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ተጠርጣሪዎችን አሟልቶ ባለማቅረቡ ምክንያት ምስክሮቹ ሳይሰሙ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ህዳር 2 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት ላይ እንደተመለከተው በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ከተካተቱት ተጠርጣሪዎች (22 ሰዎች) መካከል 5ቱን ማረሚያ ቤቱ አላቀረባቸውም፡፡ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ህዳር 2 ቀን 2009 ዓ.ም ለፍርድ ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸው ‹4ቱ ተጠርጣሪዎች በቂሊንጦ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ አደጋ ተከትሎ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ተወስደው ስላልተመለሱ› ማቅረብ አልቻለም፡፡ ማረሚያ ቤቱ ሸዋሮቢት እንደሚገኙ ያመለከታቸው ተጠርጣሪዎች ገላና ነጋሪ፣ ገመቹ ሻንቆ፣ ደረጀ መርጋ እና ቶምሳ አብዲሳ ናቸው፡፡
ሆኖም ግን ማረሚያ ቤቱ በስም ጠቅሶ ሸዋሮቢት ስለሆኑ ማቅረብ አለመቻሉን ከጠቀሰው ሌላ አንድ ተጠርጣሪ ችሎት አለመገኘቱን በማጣራት ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪውን ለምን እንዳላቀረበ የማርሚያ ቤቱን ተወካይ ጠይቋል፡፡ ሆኖም የዕለቱ ጉዳይ አስፈጻሚ ምክትል ሰርጀንት ዘውዱ ወልደማርያም ተጠርጣሪው በእርግጥ የት እንደሚገኝ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ ይህ የት እንዳለ ያልታወቀው ተጠርጣሪ ጭምሳ አብዲሳ ይባላል፡፡
በዛሬው የችሎት ውሎ ተጠርጣሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ጠበቆችም ተሟልተው አለመቅረባቸው ታውቋል፡፡ የብዙዎቹ ተጠርጣሪዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ ወንድሙ ኢብሳ አልቀረቡም፡፡ ተከሳሾችም ጠበቃቸው ከቀጠሮ በፊት ደንበኞቻቸውን ለማነጋገር ወደቂሊንጦ ሄደው ማግኘት እንደማይችሉ ተነገሯቸው መመለሳቸውን ከማወቃቸው ውጭ በዛሬው ችሎት ለምን እንዳልቀረቡ እንደማያውቁ ለችሎቱ ተናግረዋል፡፡ በችሎት የቀረቡት ሌሎች ጠበቆችም ቢሆን ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ደንበኞቻቸውን በነጻነት ስለጉዳያቸው ለማነጋገር እንዳይችሉ እንቅፋት እየፈጠረባቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ችሎቱ ዛሬ የተሰየመው የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት መሆኑን በመጥቀስ አቃቤ ህግ ከአጠቃላይ 42 ምስክሮቹ መካከል አምስቱ መቅረባቸውን በመግለጽ ምስክሮቹ ቀርበው እንዲሰሙለት ጠይቋል፡፡ ሆኖም ግን ተከሳሾቹ ሁሉም ተሟልተው ባልተገኙበት ሁኔታ ምስክር ሊሰማ እንደማይገባ ጠቅሰው ተቃውመዋል፡፡ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ በጋራ የቀረበባቸው ፍሬ ነገር ስላለ በተናጠል ምስክሮች ቢደመጡ መብታችንን ይነካል በሚል በጠበቆቻቸው አማካኝነት አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል አቶ በቀለ ገርባ አሁን ጉዳያቸውን እየየ የሚገኘው ችሎት በክስ መቃወሚያቸው ላይ ጉዳያቸው በፌደራል ፍርድ ቤት ሳይሆን በኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች ሊታይ ይገባል በሚል ያነሱትን ህገ-መንግስታዊ የመብት ጥያቄ በጣሰ መልኩ ሐምሌ 25 ቀን 2008 ዓ.ም መቃወሚያቸውን ውድቅ ማድረጉን በማስታወስ፣ በፍርድ ቤቱ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ስላላቸው ችሎት ቀርበው ክርክር ለማድረግ እንደማይፈልጉ ቀደም ብለውም ገልተጸው እንደነበር ጠቅሰው በዛሬው ችሎት ላይም ፖሊስ በጉልበት እየደበደበ እንዳቀረባቸው አስረድተዋል፡፡
አቶ በቀለ ሌሎችንም ተከሳሾች በመወከል እንዳስረዱት ከዚህም በኋላ ችሎት የሚቀርቡ ከሆነ ተገደው እየቀረቡ እንዳሉ ችሎቱ እንዲያውቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ያደረገባቸውንና በክስ መቃወሚያ የጠቀሱትን ይህንኑ የህገ-መንግስት ጉዳይ ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው ወደ ፌደሬሽን ምርድ ቤት የመውሰድ ሀሳብ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡
ፖሊስ በጉልበት መኪና ውስጥ ካስገባን በኋላ ‹‹እሰነጥቅሃለሁ›› የሚል ዛቻ እንደደረሰባቸው፣ ይህን የተናገረውን ፖሊስ ችሎት ፊት ጠቁመው በማሳየት ጭምር ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህን ዛቻ ያደረሰውን ፖሊስ ችሎቱ አንድም ጥያቄ ሳያቀርብለት አልፎታል፡፡
በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎ ያልቀረቡ ተከሳሾችን ማረሚያ ቤት እንዲያቀርብ፣ 7ኛ ተከሳሽ ጭምሳ አብዲሳን ማረሚያ ቤት ለምን እንዳላቀረባቸው ምክንያት እንዲያስረዳ እንዲሁም የኦሮምኛና ስዋህሊ ቋንቋዎች አስተርጓሚዎች እንዲመደቡ ትዕዛዝ በመስጠት ተከሳሾቹ ተሟልተው ሲቀርቡ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለህዳር 6 ፍርድ 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤት ማንኛውም ተከሳሽ በቀጠሮው ዕለት የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አክብሮ መገኘት እንዳለበትም ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
በዛሬው የችሎት ውሎ የኦሮምኛ ቋንቋ አስተርጓሚ ችሎቱ ባለማቅረቡ ከተከሳሾች መካከል አቶ በቀለ ገርባ በአጋዥነት ሲያስተረጉሙ ውለዋል፡፡ የዛሬውን ችሎት ከተከሳሽ ቤተሰቦች በተጨማሪ የዲፕሎማቲክ ኮሚኒቲ ተወካዮችና ጋዜጠኞች ተከታትለውታል፡፡
ምንጭ፡- EHRP.