ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ የአንድ ዓመት እስር እና 1,500 ብር ቅጣት ተፈረደበት

ኢትዮ ምህዳር ጋዜጣም 10ሺህ ብር ቅጣት ተፈረደበት

getachew-worku

(አዲስ ሚዲያ) ዛሬ ህዳር 6 ቀን 2009 ዓ.ም.  የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 6ኛ ወንጀል በዋለው ችሎት የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ መስራች እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ አንድ ዓመት እስራትና 1,500 ብር ቅጣት ተፈረደበት፡፡ ከጋዜጠኛው በተጨማሪ ድርጅቱ ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣም የ10 ሺህ ብር ቅጣት ተፈርዶበታል፡፡

ጋዜጠኛው እና ጋዜጣው ላይ የዛሬ ፍርድ ውሳኔ የተላለፈው አዲስ አበባ መንበረ ጵጵስና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ ተፈፀመ የተባለውን ሙስና የሚያጋልጥ ዜና በጋዜጣው መሰራጨቱን ተከትሎ፤ የደብሩ እና የቤተክህነቱ ኃላፊዎች ”በጋዜጣው ስማችን ጠፍቷል” በሚል በመሰረቱት ክስለ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከፍርድ ቤቱ ቅጣት ውሳኔ በኋላም ጋዜጠኛው በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ አዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ በሚገኘው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት የእስር ቅጣቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ መታሰሩ ታውቋል፡፡ በችሎቱ ላይ ከወዳጆቹ እና ጋዜጠኞች በተጨማሪ ከሳሾቹ ካህናት እና የደብሩ ኃላፊዎች ተገኝተው እንደነበር የተጠቆመ ሲሆን፤ ጋዜጠኛውም በመጨረሻ ”እውነት ትመነምናለች እንጂ አትጠፋም፤እውነቱ አንድ ቀን ይወጣል፡፡ ይህ ፍርድ የተፈረደብኝ ጋዜጣውን ለመዝጋት ታቅዶ ነው፡፡” ማለቱ ተሰምቷል፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ቀደም ሲል ሐዋሳ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ላይ የተፈፀሙ የሙስና መረጃዎችን በጋዜጣው ለህዝብ በማድረሱ ተከሶ ከፍተኛ መጉላላት፣ እስርና እንግልት እንዲሁም በባልደረባው ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው በአዲስ አበባ መንበረ ጵጵስና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈፀመ ሙስና የሚያጋልጥ ዜና በቂ መረጃ እንዳለው ለፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ ቢያሳውቅም፤ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ጋዜጠኛው ለቀጣይ አንድ ዓመት በእስር ቅጣት እንዲያሳልፍ በመወሰኑ ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ለንባብ ይበቃ የነበረው ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ህትመትም እንደማይቀጥል መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ከኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት በተጨማሪ በመንግሥት እውቅና የተነፈገውና በ2004 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መብትና ጥቅም እንዲሁም በፕሬስ ነፃነት ዙሪያ ለመስራት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ጠቅላላ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ እንደነበርም ይታወቃል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: