በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች፣ የመብት አራማጆች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባለትን ጨምሮ የበርካታ ዜጎች እስር አሁንም እንደቀጠለ ነው

የኢትዮጵያ መንግሥት የተነሳበት ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ባወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋዜጠኞችን፣ የመብት አራማጆችን፣ የማኀበራዊ ገፅ አምደኞችን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባለትን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን ማሰሩን ቀጥሏል፡፡

በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈፀም እንደተቋቋመ የተነገረለት ኮማንድ ፖስት ጠረጠርኳቸው ያላቸውን ዜጎች ሁሉ እያሰረ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት ጋዜጠኛ አናኒያ ሶሪ፣ ጋዜጠኛ አሊያስ ገብሩ፣ ጋዜጠኛ አብዱ ገዳ፣ የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ምክትል የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት እና ከዚህ ቀደም ከአንድ ዓመት በላይ በመንግሥት ታስረው በነፃ የተሰናበቱት አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና የማኀበራዊ ሚዲያ አምደኛው ኢዩኤል ፍስሃ መታሰራቸው ታውቋል፡፡

elias-anania-and-daniel

እንደ አሜሪካ ደምፅ ሬዲዮ ዘገባ ከሆነ፤ ሰማያዊው ፓርቲ እስካሁን 23 አባላቶቹና ከ80 በላይ ደጋፊዎቹ እንደታሰሩበት አስታውቋል፡፡የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክረሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) እና የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሕብረት በርካታ አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው መታሰራቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
መንግሥት ህዝባዊ አመፁን ለመቆጣጠርና ለማረጋጋት ብሎ በሰየመው ኮማንድ ፖስት ከሳምንት በፊት የታሰረው ጋዜጠኛ እና የዞን 9 ብሎገር በፈቃዱ ኃይሉን ጨምሮ ከ11,600 በላይ ዜጎችን ማሰሩን ቢያምንም፤ የመብት አራማጆችና የመንግሥት ተቃዋሚዎች በበኩላቸው የታሰሩ ሰላማዊ ዜጎች ቁጥር መንግሥት ካመነው ከ3 እጥፍ በላይ እንደሚልቅ ሲናገሩ ይስተዋላል፡፡

እንደ አካባቢ ምንጮች እና የመብት አራማጆች ከሆነ፤ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ያሉ የተለያዩ ወረዳዎች የመንግሥትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የኃይል ርምጃ በመቃወም የአፀፋ መልስ እየሰጡ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ቀላል የማይባል የመንግሥት ወታደራዊ ኃይሎች ከፍተኛ ጥቃት እንደተሰነዘረባቸውና ከገበሬዎችም የተጎዱ እንዳሉ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

በተለይ በአማራ ክልል የፀረ አገዛዝ ጭቆና ህዝባዊ ተቃውሞ ከተጀመረበት ሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አሁንም ድረስ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈፀመው ግድያ፣ እስርና የአካል ማጉደል ድርጊት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ ፤ ድርጊቱን የተቃወሙ የአካባቢው ነዋሪዎች አካባቢያቸውን እና መኖሪያ ቤታቸውን ጥለው በመሄድ ለአፀፋ መልስ መገደዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ከባለፈው ዓመት ህዳር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ዛሬም ድረስ እንዳልቆመ የሚነገርለትን የፀረ አገዛዝ ህዝባዊ ተቃውሞ መንስኤው የመንግሥት ሹማምንት ስልጣናቸውን ለግል ጥቅማቸው በማዋል የተፈጠረ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው በሚል ከዚህ በፊት ከነበሩት 30 ሚኒስትሮች መካከል 21 የቀድሞ ሚኒስትሮችን፣ ሁለት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረጎችን እና በሚኒስትርነት ማዕረግ የነበሩ በርካታ አማካሪዎችን አሰናብቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከዛሬ ሶስት ሳምንት በፊት፤ ለህዝባዊ ተቃውሞና ለተፈጠረው ችግር ተገቢውን ምላሽ ይሰጣሉ በሚል 21 አዳዲስ ሚኒስትሮችን በመሾም ከነባር 9 ሚኒስትሮች ጋር እንዲሰሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ ማድረጋቸው ይታወሰል፡፡ ምክር ቤቱ ሙሉ ለሙሉ የገዥው የኢህአዴግ ፓርቲ ተወካዮች ብቻ የተሞላ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኃላ በተወሰነ መልኩ የተረጋጋ ሁኔታ እንተፈጠረ መንግሥት ቢናገርም አሁንም በተለይ በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች እና ከተሞች ህዝባዊ የፀረ አገዛዝ ተቃውሞዎች የቀጠሉ መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡ ፡

ምንም እንኳ ህዝባዊ ተቃውሞ የተፈጠረው በራሱ በመንግሥት ብልሹ በሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሆነ ራሱ መንግሥት ቢያምንም፤ በፀጥታ ኃይሎች በሚወሰድ የኃይል ርምጃ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈፀመው ግድያ፣ እስርና እንግልት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ቀጥሏል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: