ቀደም ባሉ ቀናት በዋለው ችሎት በጊዜ እጥረት ምክንያት መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ባለመቻሉ ታህሳስ 26 ቀን 209 ዓ. ም. ተቀጥሮ ነበር። ዮናታን ተስፋዬ እንዲከላከሉለት ከዘረዘራቸው የሰው ምስክሮች ከአንዱ (ዶ/ር መረራ ጉዲና) በስተቀር የተቀሩት መከላከያ ምስክሮች መቅረባቸውን የዮናታን ጠበቃ የሆኑት አቶ ሽብሩ በለጠ ለችሎት አሳውቀዋል፡፡ መከላከያ ምስክሮች መሰማት ከመጀመራቸው በፊት አቶ ዮናታን የራሱን የምስክርነት ቃል አቅርቧል፡፡
ዮናታን ተስፋዬ
“በፌስቡክ አካውንቴ እፅፍ የነበረው ሃሳቤን ለመካፈል ፈቃደኛ ለሆኑት ጓደኞቼ ብቻ ነው፡፡ ህዝብ ቀስቅሷል የሚባለው ነገር የማይመስል ነገር ነው፡፡ እድሉን አግኘቼ እንኳን ለህዝብ ደርሶ ቢሆን የሽብርን ድርጊት የሚያበረታታ አይደለም የፃፍኩት ነገር፡፡ በሃገሪቷ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገልፁ እና የሚዳስሱ ናቸው፡፡ እንዚህን ሃሳቦች ከጓደኞቼ ጋር መወያየቴ ሃሳቤን በነፃነት የመግለፅ መብቴን መጠቀሜ ነው፡፡ “ህግ መጨቆኛ መሳሪያ ሲሆን፡ አመፅ የህሊና ህግ ይሆናል፡፡” የሚለው ሃሳብ የተፈጥሮ እና አለም ዓቀፋዊ ህግ ነው፡፡ ማንም ሊቀይረው አይችልም፡፡ የፍልስፍና መርህም ነው፡፡ ምናልባትም ያን የተናገርኩ ጊዜ የሚሰማ አካል ቢኖር ኖሮ ይሄ ሁላ ችግር ባልደረሰም ነበር፡፡ በህዳር 2008 ዓ.ም. አካባቢ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኘው ጭልሞ ጫካ ለባለሃብት ከተሸጠ በኋላ ህብረተሰቡ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ ምናልባትም ጥያቄያቸው በትክክለኛው አግባብ ቢያዝ ተቃውሞው አይስፋፋም ነበር፡፡ እኔም የሚደርሰው ጉዳት እንዲቀንስ የበኩሌን አስተዋፅኦ ማድረግ ነበረብኝ፡፡ መንግስት የህብረተሰቡን ደህንነት መጠበቅ ሲኖርበት በተቃራኒው የመንግስት አካል ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሲያደርስ በተለያየ መንገድ ህዝቡ ራሱን እንዲከላከል የተለያየ ሃሳብ አቅርቤአለሁ፡፡ የአንድ ሰው ህይወት ዋጋ አለው፡፡ እኔ ከመታሰሬ ቀደም ብሎ 62 የዩቨርስቲ ተማሪዎች ተገድለው ነበር፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ነገ ይህችን ዓለም ሊቀይሩ ይችሉ የነበሩ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያምን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት አካላት ችግሩ የተከሰተው በመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን አምነው ይቅርታም የጠየቁበት ጉዳይ ነው። አንድ ሚሊዮን ብር ከሚያወጣ ንብረት ይልቅ የአንድ ሰው ህይወት ዋጋ አለው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሹፌር 20 ተሳፋሪ ይዞ ፍሬን እምቢ ቢለው መኪናውን አጠገቡ የሚገኝ ግንድ ወይም ግንብ አጋጭቶ ቢያቆመው፡ ሹፌሩ መኪናው ላይ በደረሰው አደጋ ሊቀጣ አይገባውም፡፡ በአደባባይ ሰዎች ሲሞቱና ሲገደሉ እነርሱን ዲፌንድ ማድረግ ነበረብኝ፡፡ ይህንንም ሃሳቤን የመግለፅ መብቴን ተጠቅሜ የተለያየ ሃሳብ አቅርቤያለሁ፡፡ ይሄ ጥፋት የሚባል ከሆነ እቀበለዋለሁ፤ ለኔ ክብሬ ነው፡፡ ፍርዱን ከታሪክ እና ከእግዚአብሄር አገኘዋለሁ፡፡” ይህን የምስክርነት ቃሉን ዮናታን ካቀረበ በኋላ የሙያ ምስክርነታቸውን የሚሰጡትን ሶስት ምስክሮች ጠበቃው ዘርዝረዋል፡፡
የህግ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ያእቆብ ኃይለማርያም እና የፍልስፍና መምህሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የሙያ ምስክርነታቸውን የሚሰጡ ሲሆን ዮናታን የፃፈው ፅሁፍ ሃሳብን ከመግለፅ ነፃነት አንፃር እና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ህጎች አንፃር ገደቡን ያለፈ አለመሆኑን እንደሚያስረዱ፤ እንዲሁም ሶስተኛው የሙያ ምስክር ጦማሪ እና የመብት አራማጅ በፍቃዱ ሃይሉ ደግሞ በፌስቡክ በግለሰብ አካውንት የሚለጠፉ ፖስቶች ከመደበኛ ሚዲያ እና ከዜና ድህረገፆች የሚለይበትን እንደሚያስረዳ ጠበቃው አቶ ሽብሩ በጭብጥነት አስመዝግበዋል፡፡ አቃቤ ህግ በሶስቱም የሙያ ምስክሮች ላይ ተቃውሞ እንዳለው ከተናገረ በኋላ ህግን መተርጎም ያለበት ፍርድ ቤት እንደሆነ ከዚህም ካለፈ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ማየት እንዳለበት ጠቅሶ ምስክሮች የፍርድ ቤቱን ሚና መውሰድ ስለሌለባቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምስክሮች [ዶ/ር ያእቆብ እና ዶ/ር ዳኛቸው] መሰማት የለባቸውም በማለት እንዳይሰሙ ሲል ጠይቋል፡፡ በፍቃዱ የሚመሰክርበትን ጭብጥም በተመለከተ ከክሱ ጋር የማይገናኝ ስለሆነ መመስከር የለበትም ብሎ ለችሎቱ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
ጠበቃ አቶ ሽብሩም “አቃቤ ህግ ዮናታንን ወንጀል ሰርቷል ብሎ ምስክር ሲያሰማ የዳኞችን ሚና ወሰደ አልተባለም፡፡ የደንበኛዬ የመከላከል መብት በሰበብ አስባብ ሊጣስ አይገባም፡፡” ብለው ከተናገሩ በኋላ ዶ/ር ያዕቆብ እና ዶ/ር ዳኛቸው ከልምዳቸው እና ከትምህርት ዝግጅታቸው አንፃር የዮናታን ፅሁፍ ከገደብ አለማለፉን በተረዱት መጠን እንደሚያስረዱ፤ በፍቃዱ የሚመሰክረውም ዮናታን የተከሰሰበት የሽብርተኝነት ህግ አንቀፅ 6 በህትመት ደረጃ ስለሚፃፉ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ ፅሁፎች ስለሚል ልዩነቱን እንዲያስረዳ ነው በማለት ምስክሮቹ የሚመሰክሩበትን ጭብጥ አግባብነት አስረድተዋል፡፡ ዳኞችም የግራ ቀኙን ሃሳብ ከሰሙ በኋላ ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ ቃሉ ተመዝኖ መጨረሻ ላይ የሚታወቅ በመሆኑ ምስክሮች እንዲሰሙ ወስነዋል፡፡
በመጀመሪያ ለመመስከር የቀረቡት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ናቸው፡፡ የህግ ምሩቅ መሆናቸውን፣ የህግ አማካሪ እና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህር መሆናቸውን ገልጸው በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል አጣሪ ቡድን አባል ሆነው እንደሰሩ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህግ አማካሪ ሆነው እንደሰሩ ገልፀዋል፡፡ ስለሽብር ወንጀል ምንነት እና ከዮናታን ፅሁፍ ጋር አያይዘው እንዲመልሱ ተጠይቀው፤ “የሽብር ወንጀል አስከፊ ነው፤ ከጦር ወንጀል እና ከዘር ማጥፋት ጋር የሚሰለፍ ነው፡፡ የሽብር ወንጀል ዓለም አቀፍ ወንጀል ነው፡፡ አንድን ሽብር ፈጣሪ የትኛውም ሃገር ቢሄድ የሚጠየቅ ነው የሚሆነው፡፡ በኬኒያ እና ሌሎች የአለማችን ክፍሎች በርካታ ህዝቦች ያለቁበትን ሁኔታዎች በአለም አቀፍ ሁኔታም የሽብር ድርጊት የሚባሉ ናቸው፡፡” ካሉ በኋላ የዮናታንን በፌስቡ ከጓደኞቹ ጋር ለመወያየት የፃፋቸው ሃሳቦች ከጠቀሷቸው አለም አቀፍ የሽብር ድርጊቶች ጋር አንድ ማድረግ የሽብርተኝነት ድርጊትን ማቃለል እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የፀረ ሽብር ህጉ ህገመንግስቱን እና ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀበለቻቸውን ህጎች እንደሚጥስም ተናግረዋል፡፡
ቀጥሎ ለመመስከር የቀረቡት ዶ/ር ዳኛቸው ናቸው፡፡ የህግ ፍልስፍና ትምህርት የተማሩ መሆናቸውን እና መምህር መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ እአአ ከ 1948 ዓ. ም. ጀምሮ የተካሄዱ አራት አለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን በመጥቀስ እነዚህ ድንጋጌዎች ማእከል ያደረጉት የመናገር መብትን መሆኑን እንዲሁም ንግግር በይዘቱ እንደማይፈተሽ እና ማንም ዜጋ ሃሳብ የማዋቀር መብት እንዳለው ድንጋጌዎቹ በግልፅ ያሰፈሩት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል -ዶ/ር ዳኛቸው፡፡ እነዚህን ህጎች ኢትዮጵያ ከመቀበል ባለፈ ከመጀመሪያው ጀምሮ በማርቀቁ ሂደት ተሳታፊም እንደነበረች ገልፀዋል። ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት መኖር ለመንግስት ቅቡልነትን እንደሚያመጣ ዲሞክራሲም የሚለካው በዚህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ፅሁፉን አይቼዋለሁ፡፡ እምነቱን አሳይቷል፡፡ የራስክን አይዲዎሎጂ ፃፍክ ነው የሚለው ክሱ፡፡ እኔ እዚህ ሃገር ከመጣሁ ስምንት አመት ሆኖኛል፡፡ ስምንት አመት ሙሉ የራሴን አይዲዮሎጂ መንግስትን እየተቃወምኩ ስፅፍ ነበር፡፡ አልታሰርኩም፡፡ እሱም መታሰር አልነበረበትም፡፡ ልጁ [ዮናታን] የፃፈው ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ አስተማሪው ብሆን ፅሁፎቹን አይቼ ሲ እና ዲ ልሰጠው እችላለው፡፡ ያ ማለት ግን ወንጀል ሰርቷል ማለት አይደለም፡፡ መንግስት ጥሩ ነው የማለት መብት እንዳለ ሁሉ መንግስት ጥሩ አይደለም የማለት መብትም መኖር አለበት፡፡ ንግግር እና ፅሁፍን በመፍቀድ ከሚመጣው ችግር ንግግር እና ፅሁፍን በመገደብ የሚመጣው ችግር ይበልጣል፡፡” ካሉ በኋላ አቃቤ ህግ ፍርድ ቤት የመመስከር ፍቃድ አሎት ወይ ብሎ ሲጠይቃቸው፡ የትምህርት ዝግጅታቸውን፣ የስራ ልምዳቸውን እና ከዚህ ቀደምም በፍርድ ቤት መስክረው እንደሚያውቁ ገልፀው፤ ፍርድ ቤት ለመመስከር ፍቃድ የት እንደሚሰጥ አላውቅም፤ የሚሰጥ አካል አለ? የት ነው የማገኘው? በማለት በችሎት የነበረውን ሁሉ ፈገግ አሰኝተዋል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ የሙያ ምስክርነቱን የሰጠው ጦማሪ እና አክቲቪስት በፍቃዱ ኃይሉ ነው፡፡ አቶ በፍቃዱ በማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም የመጀመሪያ ዲግሪ እንዳለው፤ በመደበኛ (ህትመት እና ራዲዮ)፣ በማህበራዊ ሚዲያ እና የዜና ድህረገፆች ያለውን ልምድ ተናግሯል፡፡ማህበራዊ ሚዲያን ለመጠቀም እያንዳንዱ ሰው አካውንት ሊኖረው እንደሚገባ፤ የሚፅፉትንም ለማየት ጓደኞች ሊኖሩ እንደሚገቡ፤ መደበኛ ሚዲያ በዋነኝነት ለሽያጭ የሚቀርብ እና ከማህበራዊ ሚዲያ የበለጠ ተደራሾች እንደሚኖሩት፤ የዜና ድረገፅን ለመጠቀም ኢንርኔት አጠቃቀም ከማወቅ በዘለለ የግል አካውንት መፍጠር እንደማያስፈልግ ተናግሯል፡፡ ስለ ግለሰብ ፌስቡክ አካውንት፣ የፌስቡክ ፔጅ እና ፋን ፔጅ ልዩነቶች አስረድቷል፡፡ ዮናታን ስለፃፈው ፅሁፍ ተጠይቆ፤ ፅሁፎቹን እንደሚያውቃቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር እንደመሆኑ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት እና መፃፍ እንደሚወድ ተናግሯል፡፡ በወቅቱ በነበረው ተቃውሞ በመንግስት የተገደሉ ወጣቶችን በመቃወም ሲፅፍ እንደነበር፤ እንዲያውም የወጣቶችን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል እና ለማሸበር ሳይሆን በተቃራኒው የወጣቶችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲታገል እንደነበረ ተናግሯል አቶ በፍቃዱ፡፡
መንግስት ወጣቶችን ይገድላል ወይ ተብሎ ለአቶ በፍቃዱ ከዳኞች ለቀረበለት ጥያቄ፤ የመንግስት ፀጥታ አካላት ወጣቶችን መግደላቸው ዩንቨርሳል ትሩዝ እንደሆነ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው ሪፓርት እንኳን 173 ሰዎች በፀጥታ አካላት መገደላቸው የተገለፀ መሆኑን ገልፇል። ይህን የሙያ ምስክርነት ለመስጠት ፈቃድ እንዳለው አቃቤ ህግ ጠይቆት፤ በአዲስ አበባ መስተዳደር በሚተላለፍ የራዲዮ ፕሮግራም ፕሮዳክሽን ማኔጀር ሆኖ እንሰራ፤ የውይይት የመፅሄት ዋና አዘጋጅ ሆኖ እንደሰራ፤ የሚፅፋቸው ፅሁፎች በአዘጋጅነት ይሰራበት የነበረውን የውይይት ጋዜጣን ጨምሮ የተለያዩ የህትመት ሚዲያዎች ላይ ይታተሙ እንደነበረ፣ ዞን ዘጠኝ የተባለ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚጦምር ቡድን አባል እንደሆነ እና በቅርቡም አዲስ ስታንዳርድ የሚባል የመፅሄት ድረገፅ ላይ ፅሁፍ እንደታተመለት በመግለፅ ልምዱን በአጭሩ አብራርቷል፡፡ ይህም ልምዱ በጉዳዩ ላይ ለመመስከር ብቁ እንደሚያደርገው ተናግሮ፤ “ምስክርነት ለመስጠት ፈቃድ የሚሰጥ አካል የለም” ብሏል።
በመቀጠል የምስክርነት ቃላቸውን የሚሰጡት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቹ እና አቶ በቀለ ገርባ መሆናቸውን የተከሳሽ ጠበቃ አቶ ሽብሩ ተናግረው፤ በህዳር 2008 ዓ. ም. በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አካባቢዎች የጀመረበትን ምክንያት እና የነበረውን ሁኔታ እንደሚያስረዱለት በጭብጥነት አሲዟል።
አቃቤህግ አሁንም በምስክሮቹ ላይ ተቃውሞ እንዳለው ለፍርድ ቤት አሳውቋል። ምስክሮቹ በህግ ጉዳይ ላይ መመስከር እንደማይችሉ እና ተገቢነት የሌለው መሆኑን በመናገር ምስክሮቹ እንዳይመሰክሩ ጠይቋል። የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው ይህን ጉዳይ በተመለከተ የምስክር መስማት ሂደቱ ሲጀምር ተመሳሳይ ጥያቄ አቃቤ ህግ አንስቶ ውሳኔ ተሰጥቶት ያለፈ ጉዳይ መሆኑን በተጨማሪም ምስክሮቹ የፓለቲካ ፓርቲ አመራር እንደመሆናቸው መጠን የሞያውቁትን የሰሙትን እና ያዩትን የሚመሰክሩ መሆናቸውን ገልፀው ምስክሮቹ የሚመሰክሩበትን ጭብጥ አግባብነት አስረድቷል። ዳኞች የግራቀኙን ክርክር አድምጠው የምስክሮቹን የሚመሰክሩበት ጭብጥ ይዘት በኋላ ላይ የሚመዘን በመሆኑ፤ ተከሳሽ እራሱን የመከላከል መብቱን ከመጠበቅ አንፃር ምስክሮቹ ቢሰሙ እንደሚሻል ጠቁመው የምስክሮቹ የመሰማት ሂደት እንዲቀጥል አዘዋል።
በቅድሚያ ለመመስከር የቀረቡት አቶ ሙላቱ ገመቹ ናቸው። አቶ ሙላቱ በ2008 ዓ. ም. ስለተነሳው ኦሮሚያ ስለተነሳው ተቃውሞ መንስኤ ስለሆነው ነገር ሲናገሩ፤ ከ2007 ዓ. ም. ምርጫ በኋላ ተቃውሞ እየበረከተ መምጣቱ፣ በኦፌኮ በኩል ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተነሱትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት ሲደረግ እንደነበረ፣ ህዳር ወር ላይ 2008 ዓ. ም. በጊንጪ ከተማ የከተማው አስተዳደር 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረውን ለመኖሪያ ቤት መስሪያ ወሰዱ መባሉን ተከትሎ ተማሪዎች ተቃውሞ እንደጀመሩ፤ ተማሪዎቹም ትምህርት ቤቱን ማስመለስ መቻላቸውን፤ የከተማው ስታዲየምም በተመሳሳይ መልኩ ተወስዶ ሲከፋፈሉት ተቃውሞ ተነስቶ እንደነበረ፤ የጭልሞ ጫካ ለባለሃብቶች መሸጥ ህዝብ ላይ ቅሬታ እንደፈጠረ እና ተቃውሞ እንደተነሳ፤ በዚህም ሳቢያ ከጊንጪ አካባቢ ብቻ 70 የኦፌኮ አባላት እንደታሰሩባቸው ገልፀዋል። ይሄ በእንዲህ እንዳለም የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተባለው ፕላን ይተግበር መባሉ ብዙ ተቃውሞ ማስነሳቱን ገልፀዋል አቶ ሙላቱ።
ዳኞች ቀጣዩ ምስክር [አቶ በቀለ ገርባ] ጭብጡ ተመሳሳይ ስለሆነ አዲስ ነገር የሚመሰክሩት ከሌላ ባይሰሙ የሚል አስተያየት አቅርበው ነበር፤ ሆኖም ጠበቃ ሽብሩ ቀድመው ከመሰከሩት ምስክር [አቶ ሙላቱ ገመቹ] የተለየ ሚመሰክሩት እንዳለ በመናገራቸው ዳኞችም ባልተመሰከረበት የጭብጥ ሃሳብ ላይ ብቻ እንዲመሰክሩ አዘዋል።
በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ ማስተር ፕላኑን ተቃውመው እና ጭልሞ ጫካ ለግለሰቦች በመሰጠቱ ምክንያት እንጂ ዮናታን በፃፈው ፅሁፍ እንዳልሆነ አቶ በቀለ ገልፀዋል። በተጨማሪም ፅሁፎቹ ህዝቡ ያነሳው ተቃውሞ በሰላማዊ መንገድ እንዲመለስ ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።
የመከላከያ የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ቀርበው የነበሩት አባቱ ቀሲስ ተስፋዬ ረጋሳ፣ ጓደኛው አቶ ኤፍሬም፣ እህቱ ገዳምነሽ እንዲሁም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በእለቱ ችሎት ለመስማት ጊዜ ስላለቀ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ተነግሯቸዋል። በዛሬው ቀን ያልቀረቡት ምስክር ዶ/ር መረራ ጉዲና ያሉበትን ቦታ ጠበቃ ሽብሩ ከገለፁ በኋላ ዳኞች መጥሪያ እንዲደርሳቸው እና ፓሊስ በቀጣይ ቀጠሮ ቀን እንዲያቀርባቸው ትእዛዝ ሰጥተዋል።
ቀሪ መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ለጥር 18 ቀን 2009 ዓ. ም. ቀጠሮ ተይዟል።
ምንጭ፦ EHRP