ውድነህ ዘነብ
በጋምቤላ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ሰርገው እየገቡ በሚገኙ የሙርሌ ጎሳ የታጠቁ ኃይሎች 46 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ፡፡

ጋምቤላ ከጥቃቱ ሰለባዎች በከፊል
ከጋምቤላ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ከጥቅምት 27 እስከ መጋቢት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት የ46 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ 76 ሕፃናት ታፍነው ተወስደዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 143 ከብቶች ተነድተው ተወስደዋል፡፡ 33 ቤቶች ከነንብረታቸው ተቃጥለዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. የተሾሙትና ቀደም ሲል የክልሉ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ኡቶው ኡኮት እንደገለጹት፣ የሙርሌ ታጣቂዎች በክልሉ እያደረሱ የሚገኙት ጥቃት አይሏል፡፡
አቶ ኡቶው ባለፉት አራት ወራት ታፍነው ከተወሰዱ ሕፃናት ስድስቱ ተመልሰዋል ብለዋል፡፡ የተነዱ ከብቶች ግን አልተመለሱም፡፡ ከተገደሉ 46 ዜጎች በተጨማሪ 17 ሰዎች ቆስለዋል ሲሉ አክለዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ኡኩኝ ኦኬሎ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተወሰዱ ሕፃናትን ለማስመለስ ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት እየሠራ ነው፡፡
‹‹አምና የተጀመረው ሕፃናትን ማስመለስና ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፤›› ሲሉ አዲሱ ተሿሚ አቶ ኡኩኝ ገልጸዋል፡፡
በጋምቤላ ክልል የሙርሌ ጎሳ የታጠቁ ኃይሎች የሚያደርሱት ጥቃት አዲስ ባይሆንም፣ ከ2008 ዓ.ም. በኋላ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 2008 ዓ.ም. የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ የታጠቁ ኃይሎች የበርካታ ዜጎችን ሕይወት ከማጥፋት በተጨማሪ፣ ከ100 በላይ ሕፃናትን አፍነው መውሰዳቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ ወቅት የሙርሌ የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሶ ነበር፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት መከላከያ ሠራዊት ዘግይቶም ቢሆን ወደ ደቡብ ሱዳን በመንቀሳቀስ ሕፃናቱን ለማስመለስ ሞክሯል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በቅርብ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፣ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂ ኃይሎች ጥቃት ረዥም ጊዜ ያስቆጠረና ከኋላቀር አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው፡፡
‹‹መንግሥት ይህ ድርጊት መቀጠል የለበትም የሚል ግልጽ አቋም ወስዷል፤›› ያሉት አቶ ሲራጅ፣ ‹‹ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አስቸጋሪ የሆነው አካባቢው ረግራጋማ፣ ጥቅጥቅ ደን ያለበትና ለጉዞ አስቸጋሪ በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ትኩረት የተሰጠው መሆኑን፣ ችግሩን ለመፍታት ድልድዮችና መንገዶች እየተገነቡ መሆኑን አቶ ሲራጅ ገልጸው፣ በአካባቢው መሠረተ ልማት ከተሟላ ጥቃት አድራሾችን መቆጣጠር እንደሚቻል ማስረዳታቸውን የሪፖርተር ዘገባ አመልክቷል።