ብስራት ወልደሚካኤል
ያለምንም የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ ላለፉት 6 ወራት ከቆየ በኋላ ለተጨማሪ 4 ወራት ማራዘሙን ገዥው ስርዓት ይፋ አድርጓል:: ይሄ የሚያሳየው ህወሓት/ኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የማስተዳደር አቅሙ መዳከሙን፥ ህዝባዊ ተቀባይነት ማጣቱን እና ህዝባዊ እምቢተኝነቱ በወታደራዊ እዝ የተዳፈነ ቢመስልም ጭራሽ እንዳልጠፋ ነው የሚነግረን::
በርግጥ የአዋጁ መራዘም የዜጎችን መብት በማፈን እና በመጨቆን ተጨማሪ የመብት ጥሰትን ዕድል የሚከፍት ነው። ይሁን እንጂ ስርዓቱ አዋጁን ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለማፈን የተጠቀመበት ቢሆንም በሌላ በኩል በራሱ ላይ ተጨማሪ የማያባራ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። ምክንያቱም በህዝባዊ የፖለቲካ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ጥያቄ ተቃውሞ ምክንያት አስቸኳይ አዋጅ በታሰሩበት ሀገር ምንም ዓይነት የመብት ዋስትና ስለማይኖር ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ የኢንቨስትመንት፥ የቱሪስት፥የዕርዳታ እና ትብብር እንቅስቃሴዎች በእጅጉ ይቀንሳሉ አሊያም ይቆማሉ::
በዚህም የውጭ ምንዛሪ እና የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይገደባል/ይደክማል:: ምክንያቱም በዜጎች የመብት ጥያቄ ምክንያት በአስቸኳይ አዋጅ ወታደራዊ ዕዝ ውስጥ ባለች ሀገር ውስጥ ምንም የደህንነት ዋስትና ስለማይኖር ደፍሮ መዋዕለ ነዋይ የሚያፈስ ባለሃብትና ጎብኚ አይኖርም:: ይህን ተከትሎ ከዚህ በፊት ሀገር ውስጥ የነበሩ የውጭ ባለሃብቶች በስራቸው የነበሩ ሰራተኞቻቸውን በማሰናበት ጓዛቸውን ጠቅልለው እንዲሄዱ በማድረግ የስራ አጡን ቁጥር በእጅጉ እንዲጨምር ያደርጋል::
በተጨማሪም የንግድ እንቅስቃሴ መዳከም እና የአቅርቦት እንዲሁም የሸቀጦችና መሰረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ የበለጠ እየናረ እንዲሄድ ያደርገዋል:: ይሄ ደግሞ ለህዝባዊ ተቃውሞ ተጨማሪ ጉልበት ይሰጠዋል:: በመላ ሀገሪቱ ችግሮቹን ለመቆጣጠር የሚያስችል የገንዘብም ሆነ ፈቃደኛ የሚሆን የሰው ኃይል አይኖርም:: ስለዚህ የአስችኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም የዜጎችን መብቶችን ከመጨፍለቅ በተጨማሪ የመብት ጥያቄዎች እንዲበራከቱና ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ የስርዓቱን ውድቀት ያፋጥነዋል::
ምናልባት ገዥው ስርዓት የተፈጠረውን የውጭ ምንዛሪ እና የገንዘብ ችግር በጊዜያዊነት ለመቅረፍ ሲባል በሀገሪቱና በዜጎች ላይ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ሌሎች ጎጂ ርምጃዎችንም ሊወስድ ይችላል:: ከነዚህም አንዱ በሀገሪቱ አሉ የሚባሉና እስካሁን በከፊል በሽርክናም ሆነ በሙሉ በሽያጭ ወደግል ያልተላለፉ የመንግሥት/የህዝብ የንግድ ኩባንያዎች እና ተቋማትን ለሽያጭ ሊያቀርብ ይችላል:: በዚህም የደህንነት ዋስትና በሌለበትና በእቸኳይ አዋጅ ወታድራዊ ዕዝ ስር ባለ ሀገር ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ስለምይታወቅ፤ ምናልባት በኢትዮጵያና በቀጠናው ላይ የፖለቲካ የበላይነት ለመያዝ ዙሪያ ጥምጥም ከሚያንዣብቡ የአረብ ባህረ-ሰላጤ ሀገራት በስተቀር የሚደፍር አይኖርም:: ይሄ ደግሞ ለስርዓቱ ተጨማሪ ራስ ምታት ነው::
ስለዚህ ያለው ብቸኛ የመፍትሄ አማራጭ ከተለመደውና ከተሰላቸው የስርዓቱ ኋላ ቀር ብልጣብልጥነት ፖለቲካ አካሄድ በመውጣት፤ የአስችኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት፥ ከትዕቢትና እብሪት በዘለለ የህዝቡን ጥያቄ በተገቢው መንገድ በቀናነት መስማትና መመለስ፥ በግፍ የታሰሩ የህሊና እና የፖለቲካ እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፥ ለህዝብና ለሀገር መብትና ጥቅም ከቆሙ በሀገር ውስጥና በውጭ ካሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ጅርጅቶች/ፓርቲዎች ጋር በገለልተኛ አካላት የሚመራና ገለልተኛ ስፍራ ግልፅ ድርድር ማድረግ ግድ ይላል። እንዲሁም ሐሳብን በነፃት የመግለፅና የፕሬስ ነፃነት ትግበራን ጨምሮ ቢያንስ በሀገሪቱ ሕግ መንግሥት ወረቀት ላይ የሰፈሩ መሰረታዊ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ።
ገዥው ስርዓት የህዝቡን ጥያቄ ወደጎን በመግፋት ወደተለመደው አፈና እና ጭቆና ለመመለስ ጊዜ መግዣ ይሆነኛል በሚል በሌለ ገንዘብና አቅም ወጣቱን በማይጨበጥ ማናባዊ የኢኮኖሚ አብዮት ለማታለል ከመሞከር ይልቅ፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ ተግባራዊ የሚሆን ስምምነት ላይ በመድረስ የወታደራዊ ዕዙን በመደበኛ/ሲቭል አስተዳደር በመመለስ የአፈና የግድያ ተልዕኮ ፈፃሚ እና አስፈፃሚ የደህንነትና ወታደራዊ አካላት ከህገወጥ ድርጊታቸው ታቅበው ወደ መደበኛ ስፍራዎቻቸውና ስራዎቻቸው እንዲመለሱ ማድረግ የተሻሉ አማራጮች ናቸው:: አለበለዚያ አሁን ባለው መንገድ ነገሮች የሚቀጥሉ ከሆነ ችግሮቹ ተባብሰው በመቀጠል የሀገሪቱን እና የህዝቡን ህልውና እና ደህንነት አደጋ ላይ ከመጣል ባለፈ የስርዓቱን ውድቀት ያፋጥነው እንደሆነ እንጂ መፍትሄ ሊሆን አይችልም::