ኢትዮጵያዊው ስመ ጥር ጀግና “የበጋው መብረቅ” አርበኛ ሌተናት ጀነራል ጃጋማ ኬሎ በተወለዱ በ96 ዓመታቸው መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ. ም. ይህችን ዓለም የተሰናበቱ ሲሆን፥ የቀብር ስነ ስረዓታቸውም ዛሬ እሁድ ሚያዝያ 1 ቀን 2009 ዓ. ም. በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን በክብር ተፈፅሟል።
አርበኛው ጃጋማ በ1913 ዓ ም በቀድሞው ሽዋ ጠቅላይ ግዛት በምዕራብ ሸዋ በመጫና ጅባት አውራጃ፥ ጊንጪ ልዩ ስሙ ደንቢ ዮብዲ በሚባል ስፍራ ባላባት ከነበሩት ወላጆቻቸው ከአባታቸው ኬሎ ገሮ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ጠላንዱ ኢናቱ በ1913 ዓ. ም. ተወለዱ። ወላጅ አባታቸውን በሞት ያጡት ጃጋማ ፥ የአድዋውን ሽንፈት ለመበቀል በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን ጣሊያን ከ1928 1933 ዓ ም በኢትዮጵያ ላይ ዳግም ወረራ ባካሄደበት ወቅት ገና የ15 ዓመት ወጣት የነበሩት ጃጋማ፥ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት እና ክብር ለማስጠበቅ አንድ የአጎታቸውን የእጅ የጦር መሳሪያ በመያዝ ሁለት የአጎታቸውን ልጆች አስከትለው ጫካ ገቡ።
ከዚያም ሌሎች ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ወጣቶችን በማሳመንና በማስከተል በዕድሜና በልምድ የሚበልጧቸውን ጨምሮ ያለምንም ሳይንሳዊ ወታደራዊ ስልጠና ከ3000 በላይ አርብኞችን በመምራት ለድል በመብቃት ሀገራቸውን አስከብርዋል።
በአምስቱ ዓመት የጣሊያን ወረራ ወቅት ለፈፀሙት ጀብዱ ከንጉሰ ነገስቱ ከቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ የወርቅ የእጅ ሰዓት እና ከበርጅን የሚባለውን ልዩ ካባ ተሸልመዋል።
ከድል በኋላ በሀገር ውስጥና በአሜሪካ ሳይንሳዊ የሆነውን ዘመናዊ ወታደራዊ ስልጠና እና አስተዳደር ትምህርቶችን በመከታተልም በወቅቱ የሀገሪቱ የመጨረሻ ከፍተኛ ወታደራዊ የሌተናት ጀነራልነት ማዕረግ ላይ ከመድረሳቸው በተጨማሪ፥ የሀገሪቱ የጦር አዛዥ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ጠቅላይ ግዛቶች ሀገረ ገዥ በመሆን አገልግለዋል።