አቶ አሰፋ ጫቦ አረፉ

ዮሐንስ ሞላ

አቶ አሰፋ ጫቦ ከአባቱ ከጫቦ ሣዴ ሃማ ያሬና ከእናቱ ከማቱኬ አጀን ከተራራ አናት ላይ ከሚገኝ ሜዳማ ቦታ ላይ ጨንቻ ከተማ ነው የተወለደው፡፡ከጋሞ ሰንሰለት ተራራዋች አንዱ ጫፍ ላይ የሚገኝ ጠረጴዛ ነው ይላታል ጨንቻን ሲገልጣት ከ2-6ኛ ክፍል እዚያው ጨንቻ የተማረ ሲሆን በዘጠኝ ዓመቱ የጨንቻ ገብርዔል ዲያቆን በመሆንም አገልግሏል በድቁናው ባገኘው ካፒታልም ጥቂት የዶሮና የበግ ግልገል ገዝቶበታል ሐሙስ ሐሙስን እየጠበቀ ኤዞ ገበያ ዶሮና እንቁላል አየነገደ ይውል ነበር ከእነሱም ውስጥ ት/ቤት ድረስ እየተከተሉ ያስቸግሩት የዶሮና የበግ ግልገልም ነበረው እንደፈረንጆቹ pet መሆናቸው ነው፡፡

Assefa Chabo
የ8ኛ ክፍል ትምህርቱን በሻሸመኔ በኃላ ታሪኩን ሲያውቅ ስሙን ካላስቀየርኩ ብሎ ከታገለበት ከአጼ ናኦድ ት/ቤት ከ39 ተማሪዎች አንዱ በመሆን ነበር የተከታተለው የተዋቀረበትን ዋልታና ካስማ ያየበት ቆይታው በጋሞ ውስጥ ካሉ 40 ከሚሆኑ ‹ካዎ›ች አንዱ በሆኑት በዘመዱ በቀኛዝማች ኢሌታሞ ኢቻ ቤት በኖረበት ወቅት ነበር፡፡

ሲገልጻቸውም ‹በኢሌታሞና በሰዋች መሀከል የግንኙነት አጥር የለም፡፡ወግ ሳያበዙ ለህዝብ አሳቢና ተቆርቋሪ ናቸው ነው› የሚላቸው የጋሞ ካዎ የሚፈራ ሳይሆን የሚከበር ነው ይለናል፡፡ ገና በልጅነቱ ለህዝብ በመስራት እርካታ ማግኘት እንደሚቻልም የተገነዘበው በጉሌታ-አንዱሮ ግብር ተቀባይ ተደርጎ በቀኛዝማች ኤሌታሞ ሲመደብ ነው ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከአዲስ አበባ ከኮከበ ጽባህ አቋርጦ ሲቪል አቪዬሺን ተቀጥሮ ባህር ዳር ሄደ፡፡ ‹ሀ› ብሎ የመጀመሪያውን ስራውንና የመጀመሪያ ልጁንም ያገኘው ጎጃም ነበር፡፡ ‹ጎጃሜ ተነቀለ› ብሎ ፖሊስና እርምጃው ላይ ጽፎ ጠፍቶ እስከወጣ ድረስ እዚው ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሕግ ት/ቤት LLB አግኝቶ የተመረቀ ሲሆን በዓለም አቀፍ የህግ ተማሪዋች ውድድር ከውጭ የምስክር ወረቀት ከንጉሱም የወርቅ ኦሜጋ ሰዓት ተሸልሟል፡፡

በ 1960 የህግ ተማሪ ሆኖ በአፍሪካ አዳራሽ የቀድሞ ተማሪዎች ማህበር ስብሰባ ላይ ከመጮህ ጀምሮ ይህው እስከእልፈተ ሞቱ ድረስ ለአገርና ለወገን ዋይታውን አላቋረጠም ነበር ፡፡ በአጠቃላይ የአጥቢያ ፍ/ቤት ጸሐፊ፤የበጅሮንድ ጽ/ቤት ተላላኪና ጸሐፊ የአየር መርማሪ (metrology) የህግ አማካሪ ሆኖ ሰርቷል፡፡በፖለቲካው መስክ ከተማሪዎች ንቅናቄ ባሻገር የሁለት ድርጅቶች መስራችና መሪ ሲሆን ከ 1966-1967 የልጅ እንዳልካቸው አዲሱ ካቢኔና የደርግ አውራጃ አስተዳዳሪ ሆኖ ጋርዱላ ሄዶ ነበር፡፡ በጄኔራል መብራቱ ፍስሃ ታስሮ እስከተባረረ ድረስ የፖለቲካ ድርጅት መስራችና መሪ፤የአውራጃ አስተዳዳሪ የመንግሰትና የባለስልጣን አማካሪ፤የህዝብ ተከራካሪ በመሆን በለውጡ ውስጥ ሰርቶእል፡ ፡

በኃላም በራሱ ከግቢ የመራቅ ጥያቄ አነሳሽነት ‹‹በችሎታው መጠን ሥራ ይሰጠው›› የሚለውን ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ የፈረመበትን ደብዳቤ ይዞ መገናኛ ሚኒስቴር ወረደ፡፡ ከዚያ ነው እንግዲህ በየካቲት 1971 ዓ.ም መጀመሪያ ወደ ደርግ ጽ/ቤት ታፍኖ ተወስዶ ከዚያም በማዕከላዊ ታስሮ ከ 10 ዓመት ከ 6 ወራት ከ 6 ቀናት በኃላ የተፈታው፤ ማዕከላዊ እስር ቤት የሰው ገበያ ነበር ብሎ ሲገልፀው በ10 ዓመት የእስር ዘመኔ ውስጥ ከ100.000ሺ በላይ ሰው አይቼበታለው ይለናል ካያቸውም ውስጥ በባህርይ፣በቁመና፣በአለባበስና በስነምግባራቸው ጥሩ አድርጎ በመጻህፉ ውስጥ ይገልጻቸዋል፡፡

እንደተፈታም የአስኮ ጫማ ሱቅ የነበረበት ፎቅ ላይ የጥብቅናና የንግድ አማካሪ ቢሮ በመክፈት ሙግቱን አስረዝሞ ገንዘብና ጊዜ ከማባከን ይልቅ አስቀድሞ በድርድርና ከፍ/ቤት ውጭ ለመጨረስ ያደረገው ጥረትም ከዚሁ ከራሱ ማንነት የመነጨ ነው፡፡ በሽግግር መንግስቱ የምክር ቤት አባል በመሆንም በ 1983 አርባ ምንጭ ሄዶ ነበር ሁሉም አልሆን ሲለው ያለውዴታ በግድ አሜሪካ በስደተኝነት መጥቶ መኖሩን ጀመረ፡፡

በተፈጥሮው ሰው መጥላት የማይፈልገው አንጋፋው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ቀጥተኛው፣ ብዕረኛው አቶ አሰፋ ጫቦ የ 73 ዓመት ባለዕድሜው የአራት ልጆች አባትና የዘጠኝ ልጆች አያት ነበር ፡፡

‹የትዝታ ፈለግ› በሚል ርዕስ ለንባብ ያበቃውን መጽሐፉን በምናነብበት ወቅት ብዙ ወደማናቃቸው ጊዜያትና ግለሰቦች ከመውሰዱም ሌላ የአጻጻፍ ውበቱ እጅግ ያስደንቃል የባህሪይ አቀራረፅ ችሎታውና የአካባቢ ስዕላዊ መግለጫው ያረካል ‹‹ነፍጠኛ›› ማለት አማራ ብቻ ነው ማለት እምነት እንጂ እውነት አንዳልሆነና ‹‹ነፍጠኛ›› በሚል የሚበጠብጠንን ጥያቄ ለመመለስ ናችሁ የተባልነውን ሳይሆን ውስጣችን ገብተን ሆነን ያለነውን እንድናስተውል ይጎተጉተናል፡፡
ዋታካዳ እንደሚጠሩት ‹‹ጋንታይናው›› ‹ጋትዬ› አሰፋ ጫቦ ዛሬ አብዛኛው እየፈራ እየሸሸ ምክንያቱን በሚደረደርበት ወቅት እሱ ምን አቅብጦኝ ከደርግ ጋር ገጠምኩ; ብሎ አያውቅም አምኖ እንጂ ምናምን ፍለጋ ወይም ሰው ገፍቶት እንዳልገባ በግልጽ አስቀምጦልናል እንዲያውም ‹በመሸ በጠባ ቁጥር በጥሼ የምቀጥለው ማተብ› የለኝም ይል ነበር በንባብ የዳበረ የበሰለ መሆኑን ከማሳየቱም ሌላ ስለ አሜሪካ መምጣትና መኖር ያካፈለው ምክር በቀላሉ የሚታይ አይደልም ስለስደቱ ዓለም ችግርና ውጥንቅጥ ሲጽፍም ስደተኛው በሃብት ድህነትና በአእምሮ ድህነት መሃከል ያለው ልዩነት የጠፋበት መምሰሉን ፍንትው አድርጎ አቅርቧል በአጠቃላይ ጆሮ ጠገብነት ማወቅን አለመተካቱን ያሳውቀናል
ጀግና ፍለጋ ጦር ሜዳ መሪዋች አምባ የፖለቲካ ሰዋች አምባ እንሄዳለን፡፡

ሲገኝ አገር ያውቀዋል ፀሃይ ይሞቀዋል ያልታወቁ በየቤቱ የታጨቁ ተራሰው የሆኑ ያልተሰጣቸውን በመፈጸም የጀግኑ አሉ ይላል ጋሞ ይላል ፤ ጋሞ ግብር ገበረ እንጂ ሥርዓቱን አልገበረም በማለት ጥፋቱን ስህተቱን በማመን መቀበልና ባደባባይ ይቅርታ መጠየቅ የጋሞነት ገላጭ አብሮ የተወለደ የውሰጥ ባህርይ መሆኑን በመተንተን ለየት ስላለው የአገርና የህዝብ አስተዳደር ሥርዓት ሲያጫውተን አንዳንዶቻችን በአገራችን ውስጥ ይህ መኖሩን ባለማወቃችን እንቆጫለን ወደዛሬያችን ለማምጣት በምኞት እንጋልባለን
ሌላው የጋሽ አሰፋ ትልቅነቱ እንደአንዳንዶቹ ፀሃፊዋች በራሱ አራት ነጥብ ዘግቶ እመኑልኝ ሳይለን ያየሁትና የኖርኩት እንጂ ያጠናሁት አይደልም ይላል በትዝታዋቹ ውስጥ እየሾለከ የሁላችንንም ትዝታ የቆሰቆሰውን ያህል ዛሬ በአገራችን ስለተንሰራፋው ሥርዓትም በማዘን እየገለጸ ወደተሻለ እንድንጓዝ ይማፀነናል፡፡

በእስራት ብዛት የህዝብ ነጻነት ታፍኖ የቀረበት ዘመንም አገርም አለመኖሩን በማስረገጥ የጋራ ቤታችን የሚፈለገውን መጠነኛ ጥገና በማካሄድ ፈንታ መናድ የመረጡትን አውግዞአቸዋል፡፡አገራቸውን ባለማወቅ ወይም ለማወቅ ባለመፈለግ ነቀዝ የበላው ቤት እንድትሆን ስለማድረጋቸው በመውቀስ ወደምትፈለገዋ ከስህተቷ ልምድ የቀሰመች አዲሲቷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጽያን እንድንገነባ ይጣራል፡፡

አብርሃም ሊንከን እንዳለውና ጋሽ አሰፋም በመጽሃፉ ላይ እንደጠቀሰው ‹‹ማንንም ያለቂም እንድንመለከት፣ሁሉንም በልግስና እንድናቅፍ፣በሃቅ ላይ እንድንጸና፣አምላክም ይህንን ሐቅ እንድናይ እንዲረዳን እንማጸን፡፡

ጋሽ አሰፋ ጫቦ ያመነበትን እንደተናገረና እንደሰራ ሃገርና ወገኑን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደደከመ አለፈ፡፡ ይህን ታላቅ ሰው በህይወቱ እያለ በጣይቱ የትምህርትና የባህል ማህከል ጋብዘን በማስተናገዳችን ክብር ተሰምቶናል ፡፡ ብዕረⶉቻችን ጀግኖቻችን ጠበብቶቻችን ሳያልፉ ማክበር ግዴታችን መሆኑን እናምናለን፡፡

~ ጣይቱ የባህል ና የትምህርት ማህከል

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: